Sunday, 12 February 2017 00:00

ፑቲን፤ የሩስያ አየር ሃይል ለጦርነት ዝግጁ እንዲሆን አዘዙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የአገሪቱ ጦር ወረራ ቢፈጸምበት በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት የሚችልበት ወቅታዊ ዝግጁነት እንዳለው የሚያረጋግጥ፣ አፋጣኝ ፍተሻ እንዲደረግና አየር ሃይሉ ለጦርነት ብቁ በሆነ መልኩ እንዲዘጋጅ ድንገተኛ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የአገሪቱን የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን የአገሪቱ የመከላከያ ተቋማትና ወታደሮች ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን ለመገምገም የሚያስችል ምርመራ እንዲደረግ ባለፈው ማክሰኞ ያዘዙ ሲሆን፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ጦሩን ዝግጁ የማድረግ ስራ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፉት ሩስያ ከአንዳንድ የኔቶ አባል አገራትና ከሌሎች የአለማችን ሃያላን አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ውጥረቱ እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው ያለው ዘገባው፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም በቅርቡ የሩስያን ወታደራዊ ዘመቻዎች መኮነናቸውን አስታውሷል፡፡
ሩስያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋንና ዝግጁነቷን እያስፋፋች መምጣቷንና በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2017፣ የጦር ታንኮችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግን ጨምሮ ወታደራዊ አቅሟን ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋፋት አቅዳ እየሰራች እንደምትገኝም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 2329 times