Sunday, 12 February 2017 00:00

በሶርያ እስር ቤት 13 ሺህ ሰዎች፣ በስውር በስቅላት ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ተመድ የአገሪቱን ባለስልጣናት በጦር ወንጀል እንዲከስ ተጠይቋል
     የሶርያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎችን በጅምላ በስቅላት ማስገደላቸውን አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2015 በነበሩት አመታት፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባሻር አላሳድ ምክትሎችን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባስተላለፏቸው የግድያ ትዕዛዞች፣ ከአገሪቱ መዲና ደማስቆ በስተሰሜን በሚገኘው ሳይድኒያ የተባለ እስር ቤት ውስጥ ከ13 ሺህ በላይ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስቅላት ተገድለዋል፡፡
በእስር ቤቱ እጅግ ዘግናኝ የግርፋትና የማሰቃየት ተግባራት ይፈጸሙ እንደነበር ያወሳው ተቋሙ፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በእስር ቤቱ በየሳምንቱ በአማካይ እስከ 50 የሚደርሱ ሰዎች በስቅላት ይገደሉ እንደነበር በመጥቀስ፣ ከ2015 በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተገድለዋል ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡
በእስር ቤቱ ታስረው የነበሩ 31 እስረኞችን፣ ከ50 በላይ ባለስልጣናትንና ባለሙያዎችን በማነጋገር ያገኘውን መረጃ መሰረት አድርጎ ሪፖርቱን ማጠናቀሩን የጠቆመው ተቋሙ፤ አብዛኛዎቹ ግድያዎች የተፈጸሙት ከ2 ደቂቃ በላይ በማይዘልቁ የይስሙላ የፍርድ ቤት ክርክሮች በተላለፉ ውሳኔዎች ይሁን እንጂ፣ የግድያዎቹ ትክክለኛ መነሻ በከፍተኛ ባለስልጣናቱ የተላለፉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ናቸው ብሏል፡፡
የሶርያ መንግስት ባለስልጣናት በእስር ቤቱ የፈጸሙት የስቅላት ግድያ ድርጊት በጦር ወንጀለኝነት ያስከስሳቸዋል ያለው ተቋሙ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግና ባለስልጣናቱን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡

Read 1197 times