Sunday, 12 February 2017 00:00

ኦባማ በ12 ዓመታት ከ20 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ አግኝተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በፕሬዚዳንትነት ደመወዝ ካገኙት በደራሲነት ያገኙት በ5 እጥፍ ይበልጣል
     የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ከሴኔት አባልነት እስከ ፕሬዚዳንትነት በፖለቲካው አለም በነበራቸው የ12 አመታት ቆይታ፣ የሚስታቸውን ገቢና ከመጽሃፍት ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ ጨምሮ በድምሩ 20.5 ሚ. ዶላር ማግኘታቸውን ፎርብስ መጽሄት በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡
ኦባማ እና ባለቤታቸው ሚሼል እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2016 ባሉት አመታት፣ ከኩባንያ ቦርድ አባልነት 130 ሺህ ዶላር፣ ከፕሬዚዳንትነት ደመወዝ 3.1 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሴኔት አባልነት ደመወዝ 610 ሺህ ዶላር፣ ከሚስታቸው የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ደመወዝ 760 ሺህ ዶላር፣ ከመጽሃፍት ሽያጭ 15.6 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከተለያዩ ገቢዎች 250 ሺህ ዶላር - በድምሩ 20.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል ተብሏል፡፡
ኦባማ በ12 አመታት ካፈሩት አጠቃላይ ገንዘብ ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆነውን ያገኙት ለንባብ ካበቋቸው መጽሃፍት ሽያጭ ሲሆን፣ ኦዳሲቲ ኦፍ ሆፕ እና ኦፍ ዚ አይ ሲንግ - ኤ ሌተር ቱ ማይ ዶውተርስ ከተሰኙት ሁለት መጽሃፍት ብቻ 8.8 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
ኦባማ በፕሬዚዳንተነት ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ስምንት አመታት ብቻ 10.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 3.1 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ ከመንግስት በደመወዝ መልክ የተከፈላቸው፣ 120 ሺህ ዶላር የሚሆነው ደግሞ ከኢንቨስትመንቶች በትርፍ መልክ ያገኙት እንደሆነ ገልጧል፡፡
በ2009 አመት 5.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኙት ኦባማ፣ በፕሬዚዳንትነት በቆዩባቸው አመታት ገቢያቸው ከአመት አመት እየቀነሰ በመምጣት በ2015 ላይ 450 ሺህ ዶላር መድረሱን ያስታወሰው ፎርብስ፤ ይህም የሆነው የመጽሃፍት ሽያጭ ገቢያቸው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ሰበብ ነው ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማና ባለቤታቸው ሚሽል ኦባማ እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2015 ድረስ ባሉት አስር አመታት ካገኙት አጠቃላይ ገቢ 8 በመቶ ያህሉን ወይም 1.6 ሚሊዮን የሚሆነውን ለበጎ ምግባር ስራ በስጦታ መልክ ማበርከታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1401 times