Sunday, 12 February 2017 00:00

የደራሲነት እብደቶች

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

 መቼም የደራሲነት ውሉና ወጉ ከባልዛክ እስከ ሄሚንግዌይ ወዲህና ወዲያ ነው፡፡ እንዲህ ነው ተብሎ የሚነገርለት አንድ ወጥ ምስል የለውም፡፡ ቢሆንም ግን የተጨበጠ መልስ ማግኘት እንደማንችል እያወቅን እንኳን እንዲህ ብለን እንጠይቅ እስቲ … ‹ደራሲነት ምንድን ነው?›
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ላይ፤ ‹‹በተዓምር የማያምን ደራሲ የተረገመ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ እኔ ደግሞ እላለሁ፡፡ ተዓምር ራሱ ምንድን ነው? በተዓምር የሚያምን የቀለም ሰውስ፣ ከደራሲነት ይልቅ ለሰባኪነት አይቀርብም ይሆን? የሆነ ሆኖ እነዚህን ጥያቄዎች እንጠይቃለን እንጂ የምናልባት መልስ እስኪያመነጩ ድረስ እያሳደድን አንከተላቸውም፡፡ ልናዘነግገው የተነሳንለት የነገር ሐቲታችን ሌላ ነው፡፡ የደራሲነት እብደት ይሉት ቅዠት…
በእኛ አገር የአንድ ዘመን ተጋሪ ፀሐፍት መሐል እንኳን የደራሲነት ወግ ውሉ ወዲህና ወዲያ ነው። ይህን በዚህ ሰሞን ወደ እጄ ገብቶ ላነበው በታደልኩት የሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) የግል የህይወት ታሪክ መፅሐፍ ልታዘብ ችያለሁ። ‹ነበር - ነበር - ነበር› በሚሉ ለዛ ቢስ ሙት ከንቱ ቃላት መካከል የተቸነከሩትን የባለቅኔውን ሽርፍራፊ የህይወት መልኮች እያሰስኩ ስለ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፣ ስለ ባሴ ሃብቴና መሰሎቻቸው አሰብኩ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ቀደምቶቻችን የኖሩት ወለፈንዴነት የተጫነው ኮተታም ኑረት ምንጩ ድርሰት፣ የራሳቸው ተፈጥሮአዊ መሻት፣ ወይስ በሁለቱ መካከል ያለው የልጅነት ተቃርኖ ነው? ብቻ እንጠይቃለን እንጂ አሁንም ቁርጥ ያለ መልስ ፍለጋ አንባዝንም፡፡ ደግሞስ ቁርጥ ያለ መልስ የሚባል ነገር አለ እንዴ?
ይህንን አምናለሁ፡፡ መንጠራወዙ ሁሉ ምንጩ ቁሳዊ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ኪነት ግን የምትፀነሰውም ሆነ የምትበለፅገው በእጦት፣ በጉድለት፣ በሽሽት፣ በንፍገት … ከተሞላ ህይወት ነው፡፡ ኪነት የደራሲነት መክሊታቸውን አምነው ተቀብለው ለሚታገሉ ሁሉ እነዚህን በህይወታቸው ዙሪያ የሚፈጠሩትን ጥቃቅን ለውጦች የሚታዘቡበት የመረዳት ልዕልና ትሰጣቸዋለች፡፡ በነብሳቸው ዙሪያ የሚያደከድኩትን የስንብት ዳናዎች ሳይቀር ለይተው እስኪያውቁት ድረስ ንቃትን ታላብሳቸዋለች። ሆኖም ይህንን መገለጥ ተከትሎ የሚመጣውን አይቀሬ ‹በህይወት የመበርገግ› ስሜት ለመፋለም የሚያስችል ወኔ ልትሰጣቸው አትችልም፡፡ እናም በግዳቸው ደራሲነት የአልበርት ካሙን “አብዘርድ ሄሮ” ሲሲፐስን የመሆን መፍጨርጨር እንደሆነ ተቀብለው እብደቱን ይተዉኑታል፡፡
ወዳጄ ሆይ፤ደራሲ ልክ እንደ ሲሲፐስ ነው፡፡ ሲሲፐስ በግሪክ አፈ-ታሪክ መሰረት፤ ከአማልክቱ ጋር በፈጠረው አምባጓሮ በአማልክቱ መንደር ከማይደረስበት ጥልቅ ዝቅታ አንስቶ እስከማይደረስበት የከፍታ ጥግ የማይሸከመውን ድንጋይ እንዲያንከባልል ተፈርዶበታል፡፡ ይኸው ድንጋይ የከፍታው ጥግ በደረሰ ቅፅበት ተመልሶ መንከባለሉ ላይቀር ለዝንተ ዓለም ይውተረተራል። ድርሰት እንዲህ ነው፡፡ ለዓመታት ያንከባለሉት ጥበባዊ ድንጋይ ከእጅ ሲወጣ ባዶ መሆን፤ የመኖር ሕልምን ለመሰነቅ ሲባል እንደገና ወደ ጥልቅ ዝቅታው ወርዶ ሌላ ጥበባዊ ድንጋይን ማንከባለል … እንደገና ባዶ መሆን … እንደገና፣ እንደገና፣ እንደገና … በሌጣ ድግግሞሽ (Bare repetition) የታጀበ አዙሪታዊ ሕይወት፡፡ ሆኖም ሕይወት እኮ እንዲሁ ሌጣ ድግግሞሽ ብቻ አይደለችም፡፡ ድግግሞሹ በርካታ የሚያመረቅዙ የስቃይ መስመሮችን ይዟል። እናም እሱን እስክትዘልቀው የህይወት ምርምር ያስፈልጋል፡፡
“ኦ የደራሲ እውነት ወዴት ነሽ!?” አትበሉ። ደራሲ ምን እውነት አለው፡፡ ደራሲ እውነቱንም ሆነ እብለቱን የሚያዘነግገው ከጊዜ ወንዝ ላይ በእፍኙ በጨለፋት የዘመኑ ስፍር፣ ከእናንተ ህይወት በተናጠቃት ትዝብት እኮ ነው፡፡ እንጂ ደራሲማ የራሱ እውነት ከወዴት አለው? ስካሩ እንኳን የአረቄ ስካር አይደለም፡፡ አይደለም፡፡ ደራሲ ጥምብዝ ብሎ የሚሰክረው በብዕሩ ከሚያገነፍለው የዘመናችሁ ድንግርግር የተረፈው ሁከት ናላውን አዙሮት ነው፡፡
እኔና ሙሉጌታ ተስፋዬ በዘመን ሃዲድ ላይ ለጥቂት ተላልፈናል፡፡ ሆኖም አያ ሙሌ ይህንን የደራሲነት ግርታውን አንዳንዶች እንደሚሉት፤ በአረቄ እየሾፈረ ሌሊቱን ሙሉ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተመላለሰ፣ ተርፎ ያደረውን ነውራችሁን በብዕሩ ይቧጥጥ ነበረ፡፡ አያ ሙሌ፣ ሕይወቱ ከእነ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ባላነሰ ለሰሚ ጥዑም ለዛ ያለው ቢሆንም ራሱን መሸጡን ስላላወቀበት፣ በሞቱ ያልተሰማና ያልተነገረ ግሩም ተረት ሆኗል፡፡ እኔም አለሁ፤ተርፎ ካደረው ነውራችሁ ላይ ቀለም አጥቅሼ ምስል ለመፍጠር ሌሊቱን ሙሉ መንገዶቻችሁን አስሳለሁ፡፡
ከዘመን ነውራችሁ ላይ ጥቀርሻ ወስጄ፣ ንቅሳታችሁን ከንቱ ቃላት መሐል አበድናለሁ። ቢገባችሁ ባይገባችሁ፣ ብታነቡት ባታነቡት ግድ የለኝም፡፡
ምን አለፋህ፤ ደራሲነት እብደት ነው ወዳጄ፡፡ እንደ እኛ ዓይነት የደራሲነት ግርታህን ማስታመም  የማይችል ማህበረሰብ ውስጥ ከሆንክማ አንድያውኑ ሊለይልህ ይችላል፡፡ ታዲያስ አያ ሙሌ “እብድ ነበር” ሲሉ አፋቸውን ሞልተው የሚያቦኩትን ምን ልትላቸው ትችላለህ? ዝም ማለት እንጂ … አንዳንዱ ወደ ኤማሆስ፣ ሌላው ወደ ቀራንዮ ሆኖ መንገዱ --- ይለያይ እንጂ ሁሉም በህይወት ፍዝ ሰሌዳ ላይ ነጥብ ሆኖ፣ ከተፈጠረበት ቅዠት ድንገት ባንኖ፣ በህልውና የሚቀዝፍ ተጓዥ መንገደኛ ነው፡፡ እናም ዝም ብለህ መድረሻህን ማበድ ነው፡፡ እብደቱን ከፈራህ ግን ደራሲነቱ ቢቀርብህ ይሻላል፡፡ ምነው? ብትል፣ ግር መሰኘት፣ ወለፈንዴነት የሌለበት ድርሰት ከዘገባነት አያልፍምና ነው። ኦህ! እንዲያው ድከሙ ብሎን እንጂ ምንስ ቢሆን ከዝምታ የበለጠ የትኛውንም ጥልቅ ሃሳብ ተንትኖ የሚገልፅ ቃል ከወዴት ተገኝቶ! እንዲያው ዝም ይሻላል፡፡ ባይሆን ዝም ብሎ ማበድ!…
(ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 2273 times