Sunday, 12 February 2017 00:00

የአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ የጃዝ ኮንሰርት “Keep walking”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮ ጃዝ አባት እየተባለ የሚጠራው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ በጊዮን ሆቴል ከሚገኘው አፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ ክለቡና በ97.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ከሚተላለፈው አፍሪካ ጃዝ መንደር የሬዲዮ ፕሮግራሙ ባለፈ ከአድናቂዎቹ ጋር ፊት ለፊት የሚያገናኘውን “Keep walking” የተሰኘ የጃዝ ኮንሰርት ከለንደኑ “Steps ahead” ባንድ ጋር
የፊታችን አርብ በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ቦል ሩም አዳራሽ ሊያቀርብ መሆኑ ብዙዎችን አስደስቷል። ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል ሰሜን አዳራሽ፣ ከኮንሰርቱ አዘጋጅ የ”ዘሌማን አድቨርታይዚንግ ኮሚዩኒኬሽንና ፕሮዳክሽን” ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ወ/ማሪያም ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሚወዳት አገሩ የመጀመሪያውን የጃዝ ኮንሰርት በማቅረብ ከአድናቂዎቹ ጋር ፊት ለፊት ሊገናኝ መሆኑ እንዳስደሰተው ገልጾ፣ ቀኑን በጉጉት እየጠበቅሁ ነው ብሏል- አርቲስት ሙላቱ፡፡
 
      ላለፉት 52 ዓመታት ኢትዮ ጃዝ በዓለም እንዲታወቅና ተቀባይነት እንዲያገኝ የታገለው ሙላቱ አስታጥቄ፣ በአገሩ ኮንሰርት እንዲያቀርብ ከዓመት በላይ መልፋታቸውንና በህይወት እያለ እውቅናና ሽልማት ለመስጠት ኮንሰርቱን ማዘጋጀታቸውን አቶ ዘላለም ወ/ማሪያም ተናግረዋል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ ሙላቱ ከ10 በላይ ዘፈኖችን እንደሚጫወት የተገለፀ ሲሆን የሸራተኑ ቦልሩም አዳራሽ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እንደሚከፈት ታውቋል፡፡ በዚህ ኮንሰርት ላይ
ለመታደም የኮክቴል ምግብና መጠጥን ጨምሮ 1 ሺ ብር እንደሚያስከፍል አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ከኮንሰርቱ አንድ ቀን በፊት አርቲስት ሙላቱ ከአጃቢዎቹ “ስቴፕስ አሄድ” ባንድ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ጃዝ መንደር ለሙዚቀኞች ወርክሾ
እንዳዘጋጀ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ ወርክሾፕ ላይ ማንኛውም ሙዚቀኛ እንዲሳተፍ ተጋብዟል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አርቲስት ሙላቱ በበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ በመማርና
በማስተማር ስላሳለፈው ጊዜ፣ የአገራችን ሙዚቃ ለአለም የጃዝ ሙዚቃ ስላለው አስተዋጽኦ፣ ወደፊት ስለሚያስበውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡

     በ1960ዎቹ በበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ ነበርክ፡፡ ከ40 ዓመት በኋላ መምህር ሆነህ በርክሌይ ገብተሀል፤ ከዩኒቨርሲቲውም ትልቅ እውቅና አግኝተኻል፡፡ ይህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?
የመጀመሪያው ነገር አንድ ሰው አንድ ህልም አልሞ፣ ያም ህልሙ ተሳክቶ በዓለም አለ የሚባለው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለመማር መታደሉ አንዱና ትልቁን የደስታና የእድለኝነት ስሜት ያስተናገድኩበት ነው፡፡ ሁለተኛው እዚያ መምህር ሆኖ መመለስ በራሱ እንኳን ለእኔ ለአገሬም ኩራት ነው፡፡ ይህን ስሜት ማሰብ ሁለተኛው ነው። ሶስተኛው ይህ ዩኒቨርሲተ ኮሌጅ፤ “For your contribution to the music in the world” በሚል “PHD” ሸልሞኛል፤ ከዚህ በላይ መቼም ደስታ የለም፤ በእውነቱ፡፡ ከዚህ አልፎም በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲም ብዙ ጥናትና ምርምር ሰርቻለሁ። “A Fellow of Harvard University” የተሰኘ ታይትል አለኝ፤ ኤም አይቲም ነበርኩኝ፡፡ ኤም አይቲ - “ማሳቹሴትስ ኦፍ አይቲ” ማለት ነው፤ በዚህ ተቋም በክራር ላይ ጥናት አድርጌያለሁ፤ ያው ክራሩም ይወጣል፡፡
በመላው ዓለም በርካታ የጃዝ ኮንሰርቶችን አቅርበሃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮንሰርት ደረጃ የመጀመሪያህ ነው፡፡ ለምን እስካሁን ዘገየህ?
 እኔ አገሬን በጣም እወዳለሁ፤ በዓለም ስዞር ኢትዮ ጃዝን ስሰራ፣ አገሩን ባህሏን በሙዚቃ ያላትን ደረጃ እያሳየሁ ነው፡፡ እዚህ ኮንሰርት ያልሰራሁበት ምክንያት የተለያዩ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ አሁን ዘሌማንን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ይህን ኮንሰርት ለማዘጋጀት ከዓመት በላይ ለፍቷል፤ ስፖንሰር ሲፈልግ፣ ሌሎች ሌሎች ውጣ ውረዶችን አልፎ፣በመጨረሻ ተሳክቶ፣ እኔም  በአገሬ ይሄን የመጀመሪያ ኮንሰርት ለመሥራት ስዘጋጅ ቀኑ አልደርስ ብሎኝ እየተጠባበቅሁ ነው፤ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከውጣ ውረዱ ውጭ ምንም ለመዘግየቴ ሌላ ምክንያት የለኝም፡፡
አንድ ባለሙያ በአንድ ዘርፍ ልሂቅ ሲሆን በስሙ የሚቋቋም ፋውንዴሽን፣ ትልቅ ማዕከልና ሌሎችም ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አንተ በዚህ በኩል ምን ያሰብከው ነገር አለ?
እኔ ለዚህ የበቃሁት በማንና ከየት ተነስቼ ነው። የጃዝ ሙዚቃ ሳይንቲስቶች ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ አራቱም የሙዚቃ ቅኝቶች፡- አምባሰል፣ አንቺ ሆዬ፣ ትዝታና ባቲ ትልቅ ናቸው፡፡ በነዚህ ነገሮች ላይ ጥናትና ምርምር መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ ተራሮች በሙዚቃ ቅኝቶች ተሰይመው ይገኛሉ። ቅኝቱ ነው የቀደመው ወይስ ተራራው የሚለው መጠናት አለበት፡፡ ለምሳሌ የቤኒሻንጉሉ “ዙምባራ” የተሰኘ መሳሪያ፣ የደራሼ ብሔረሰብ ለጃዝ ሙዚቃ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ እነዚህን የሙዚቃ ድምፆች እንዴት ፈጠሯቸው የሚለው ተጠንቶ የአገራችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ያላቸው አስተዋፅኦ በግልፅ ታውቆ፣ ማዕከልም ቢከፈት በእነሱ ስም እንጂ በኔ መሰየም የለበትም፤ ፈጣሪዎቹ እነሱው ናቸው፡፡ እኔ በእነዚህ የሙዚቃ ድምፆች መነሻነት ነው ኢትዮ ጃዝን ያሳደግኩት፡፡
ታዲያ ጥናቱን ማን ይጀምረው? ማንስ ያስጀምረው ትላለህ?
እኔ እንደ ኢትዮ ጃዝ አባትነቴ፣ “ኢትዮ ጃዝ” የሚል ፈለግ በዓለም ላይ አስቀምጫለሁ፡፡ ማን ይጀምረው ላልሺው፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ምሁራን በተለያዩ ዘርፎች ላይ በርካታ ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ አይደለም እንዴ? ታዲያ በዚህስ ላይ ቢያተኩሩ ምናለበት፤ ምክንያቱም ሙዚቃ የአንድ አገር መለያና ማንነት ነው፡፡ የአንድ ህዝብ ባህልና መታወቂያ ነው፡፡ ስለዚህ ትኩረት ተደርጎ ምርምርና ጥናቱ መካሄድና ለዚህ የሙዚቃ ዘርፍ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ብሔር ብሔረሰቦች ክብር ማግኘት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡
አንተ በግልህ ኢትዮ ጃዝ በዓለም ላይና በአገራችን በኢትዮጵያም እንዲታወቅ ላለፉት በርካታ አሰርት ዓመታት ስትታገል ቆይተሃል፤ በሬዲዮም ለ12 ዓመታት ገደማ ወደ ህዝቡ እንዲሰርፅ ጥረት እያደረግክ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጥናትና ምርምሩ አልዘገየም ትላለህ?
እኛ እንግዲህ ይሄንን ማሳወቅና ማስረዳት ነው ያለብን፤ በዚህ መስመር ላይ የምንሄዳቸው የተለያዩ አቅጣጫዎች አሉን፡፡ ምርምርና ጥናት ሌላ ነው፤ ማስታወቅና ማስረዳት ሌላ ነው፡፡ ዎርክሾፖችን በመላው ዓለም መስጠትም ሌላ ታሪክ ነው፡፡ አሁን አንቺ የምትጠይቂኝ ጥናትና ምርምር በትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰራ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የባጀት ጥያቄ አለ፡፡ ይህን ለመስራት ስፖንሰር የሚያደርገው ማን ነው? ይሄ ሁሉ በደንብ ታስቦበትና ተዘጋጅቶ መጠናት አለበት፡፡ ኢትዮ ጃዝ በትግሌ፣ በግል ጥረቴና በ52 ዓመት ልፋቴ፣ በዓለም ላይ እዚህ ደረጃ አድርሼዋለሁ፡፡ ጥናትና ምርምሩ ዘግይቷል አልዘገየም፣ የሚለው የሌላ አካል ድርሻ ነው፡፡
የጅማ ልጅ ነህ፡፡ በአገራችን አሉ ከሚባሉት ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶሀል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የሙዚቃ ዲፓርትመንት አቋቁሟል፡፡ ለዲፓርትመንቱ መቋቋም ምክንያቱ አንተ ትሆን?
 የጅማ ልጅ መሆኔ ትክክል ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶኛል እውነት ነው፡፡ ግሩም የሆነ የሙዚቃ ዲፓርትመንት ማቋቋሙንም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ለዲፓርትመንቱ መቋቋም እኔ ምክንያት ልሁን አልሁን በትክክል ላውቅ አልችልም፡፡ ነገር ግን ለሙዚቃ ለሰጡት ክብር ያለኝን አድናቆት ልሸሽግ አልችልም፡፡ ወደፊትም በሙዚቃና በሚሰሩት ስራ ሁሉ አቅሜ በፈቀደና በተቻለኝ መጠን ሙሉ ድጋፌን ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ፤ በዚህም ዙሪያ እየተወያየን ነው፡፡  
የፊታችን አርብ ከሚካሄደው ኮንሰርት ምን አይነት አቀባበል ትጠብቃለህ?
ይሄንን ነገር እስኪመጣ እንጠብቅና ካለፈ በኋላ እናውራበት፤ እስከዚያው ዝም ብሎ መጠበቁ ነው የሚሻለው፡፡  
የህይወት ታሪክህን (ኦቶባዮግራፊ) ለመፃፍ አላሰብክም?
እኔ እንግዲህ በዚህ በሙዚቃው ብዙ ስራዎች አሉኝ፤ መፅሐፍ ለመፃፍ ጥሞና፣ ሰፊ ጊዜና መረጋጋት ያስፈልጋል፤ነገር ግን ዩኒሳ ዩኒርሲቲ (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ) “The Making of Ethio Jazz” በሚል የኔን ታሪክ ፅፈዋል፡፡ ሆሊውድ ውስጥም በዚሁ ርዕስ ፊልም ለመስራት አስበዋል፡፡ በእኔ በኩል ያለውን እንግዲህ የማስብበት ይሆናል፡፡

Read 2669 times