Sunday, 12 February 2017 00:00

“እያዛጉ እስክስታ”

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 “--- ምክኒያታዊና ተያያዥነት ባለው አስተሳሰብ እኩይነትን መልካም አስመስሎ እንደ አብዮት የማስፋፋቱ አቅም ግን የድብርት ተጠቂው እንጂ የእብዱ አይደለም፡፡ ረቂቅ ድብርት ከእብደትም ይከፋል፡፡ “እያነቡ” ሳይሆን … “እያዛጉ” እስክስታ መውረድ ነው ወደ አደጋ እየወሰደን ያለው፡፡”
                        
      ሚላን ኩንዴራ የቼክ ዜግነት ያለው ምርጥ ደራሲ ነው፡፡ ምርጥ ስል ቢያንስ ለእኔ ማለቴ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ እ.ኤ.አ በ1998 ያሳተመውን “Identity” የተባለውን ድርሰቱን በማንበብ ላይ ሳለሁ ዋነኛው ገፀ ባህርይ ዣን ማርክ ከሚያስበው አንዲት ሀሳብ በመነሳት መጣጥፌን ለመጠንሰስ ወሰንኩ፡፡
ዣን ማርክ እንደሚከተለው ይላል፡- “ሦስት ዓይነት የድብርት አይነቶች አሉ፡፡ Passive የሚባለው አይነት ለምሳሌ አንዲት ሴት ድንገት እየደነሰች ሳለች፣ በመሀል ስታዛጋ ብትታይ፣ይህ ፓሲቭ ድብርት በመከሰቱ ነው፡፡ ሁለተኛው Active የሚባለው አይነቱ ነው፤ ልክ እንደ ደንበኛ ስራ ሰው የውሻ የቁንጅና ውድድር ሲያካሂድ ወይ ወላንዶ በሰማይ ላይ በሙሉ ተመስጦ (ሙሉ የህይወቱን ጊዜ) እያንሳፈፈ ተወጥሮ ሲገኝ የሚገለፅ ነው፡፡ ሦስተኛው፤ አጥፊ (Destructive) የሚባለው አይነት ነው፡፡ ሰዎች በአንድ እምነት መናጆ  ቦንብ ሲያፈነዱ፣ መኪና ሲያቃጥሉ ወይንም በተመሳሳይ አጥፊ ድርጊት ተጠምደው ሲገኙ የሚገለፅ ነው፡፡”
እንደ ገፀ ባህሪው አስተሳሰብ፣ በአሁኑ ጊዜ ግዘፍ ነስቶ የሚታየው የሰው ልጆች ተግባር በሙሉ ከዚህ የድብርት ማህጸን የተወለዱ ናቸው፡፡ “The quantity of boredom, if boredom is measurable is much greater today than it was once.” ይህ የሆነበትም ምክኒያቱ የጥንቱ የሰው ልጅ በሚያከናውነው የእለት ተለት ተግባር ላይ ከፍተኛ እምነትና ለሞያውም ጥልቅ የሆነ ፍቅር ነበረው ይላል፡፡ አናጢው በእንጨት ላይ ባለው ሞያዊ ስልጣን ከፍተኛ እምነትና ተመስጦ ነበረው፤ ሀኪሙ በህመም ላይ የፈውስ ተወካይ አድርጎ ራሱን ይመለከት ነበር፡፡ በአመለካከቱ ያምን ነበር። ለገበሬው መሬቱ እንደ ሀይማኖቱ ነበር፡፡ ሀይማኖቱ ደግሞ ሐሳዊ አልነበረም፡፡
የሰው ተግባሩ፣ ሙያው፣ ክህሎቱ-----በምድር ላይ በህልውና ለመገኘቱ (purpose for being) ዋና ምክንያቱ ነበር፡፡ ምክኒያቱ ላይ ደግሞ ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ እምነትም እውቀትም በጥልቅ ስሜት የሚመለኩ ሀይማኖቶች ነበሩ። ይህ እምነት ተለወጠ፡፡ ለምን ተለወጠ? … አያከራክረንም፡፡ ብቻ ተለወጠ። እምነትና ተግባር የነበራቸው የአፍቅሮት (passion) ጋብቻ ተረበሸ፡፡ ሀይማኖቱ ፈረሰ፡፡ ሰው አእምሮውን ፈትቶ ያለ እምነት ተግባርን ሲያከናውን ነው ድብርት የሚወለደው፡፡ እኔም ዣን ማርክ እንደተባለው ገፀ-ባህርይ ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡ ምክንያቱም፤የገለፀበት መንገድ ለሚታየኝ የሰው ሥነምግባር ጉድለት ሁሉ ዋናው ምክኒያት ስለመሆኑ ድንገት ስለተገለጸልኝ ነው፡፡  
*    *   *
አዎ፤ የምመለከተው እውነታ ግራ የገባው ነው፡፡ “የሰከረ” ነው፡፡ ሀይማኖተኞቹ ከእምነት ተፋተው፣ ሳይንሳዊ ተግባር ለማከናወን ሲሞክሩ አያለሁኝ፡፡ ወይንም ደግሞ በተቃራኒው ሳይንቲስቱ ከምክኒያታዊነት ርቆ እምነትን ምክኒያታዊ አድርጎ ሊሰብክ ሲላላጥ ይገኛል፡፡ ጥቅም በምንም የዋጋ ሚዛን ያልተተመነለት ነገር ልክ እንደ መሰረታዊ እውነት ቆጥሮ አብዮት ሊያፋፍሙለት ሲጥሩ ይታያሉ - ማህበራዊ ሳይንቲስቶቹ፡፡ ሳይኮሎጂስቶቹ የሰውን ወይንም የግለሰብ ነፍስን ሰልለው ግራ የሚያጋባ  መፍትሄ ወይንም ህመም ለማወለድ ሲጥሩ ታያለህ፡፡ … እኔም አያለሁኝ፡፡ … ልክ እንዳይደለ አንተም ይሰማሀል፤ እኔም አውቃለሁኝ፡፡
እኔ የሰው ልጅ ሰከረ ብዬ ነበር የማስበው። ስካር ቢሆን እሰየው ነው፤ከስካር ይልቃል፡፡ የማይሽር ስካር እብደት ነው፡፡ የሰው ልጅ ሰክሮ ካልሆነ አብዶ መሆን አለበት .. ብዬም ማሰብ ጀምሬ ነበር፡፡ ተሳስቼ ኖሯል፡፡ … ምክንያቱ ለካ ድብርት ነው፡፡ ድብርት ደግሞ እንደ ስካር ሲነጋ ወደ አቅሉ የሚመለስ አይደለም፡፡ ወይንም እንደ እብደት ሁነኛ ሀኪም ካገኘ ጤነኛ የሚሆን የህመም አይነት አይደለም፡፡ እብደትም ሆነ ስካር … ከ “አልቦአዊነት” መንስኤ የመነጩ አይደሉም፡፡ ምክንያታዊ ለመሆን ሲያቅት በግራ መጋባት የሚመረጥ አጉል መንገድ ናቸው እንጂ “አልቦአዊ” አይደሉም፡፡ ድብርት ግን ወደ ባዶነት ፍልስፍና በጣም ያጋደለ ነው፡፡
ቢዮንሴ ያለ ፅንሰ ሀሳብ ወይንም ያለ ምንም የእምነት ንጥረ ነገር፣ ሀይማኖት የምታቋቁም ከሆነና በዛው ቅጽበት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ መሰረት አለው በሚባል የሀይማኖት ተቋም ስር ተጠምቃ የምትሄድ ከሆነ የድብርት መገለጫ ነው፡፡ ድብርቷን ለመሸወድ በያይነቱ እርስ በራሱ የሚጣላ አስተሳሰብ በአንድ ላይ ደምራ ልታስኬድ ትችላለች፡፡ ግን የእሷ ድብርት እስክስታ እየወረደች እንደምታዛጋዋ የድብርት ተምሳሌት---- Passive ተደባሪ አይደለችም።… እስክስታ ወራጇ፣ የማትፈልገውን ተግባር (እስክስታን) ወይም ተግባሩን ማከናወን በማትሻበት ጊዜ እስክስታ እንድትወርድ በመገደዷ ሊሆን ይችላል ያዛጋችው፡፡  የቢዮንሴ እንደዛ አይመስለኝም፡፡ የቢዮንሴ Active ድብርት ነው፡፡ እስክስታ እየወረደች ሳለች አይደለም ማዛጋት የሚያመልጣት፡፡…. እንዲያውም ማዛጋትን ወደ እስክስታ ቀይራ፣ ‹‹እያዛጉ እስክስታን›› በጥበብ መልክ ማስለመድ ነው የድብርቷ አይነት፡፡
‹‹የሰው ልጅ አይለወጥም፣ ተለውጦም አያውቅም›› ይላል፤ሊሮይ የሚባል በዚሁ የኩንዴራ መጽሐፍ ላይ ያለ ገፀባህርይ። አይለወጥም ግን…. እንደሚለወጥ ደጋግሞ ይዝታል፡፡ ዛቻውን ወደ አብዮት ቀይሮ፣ አብረውት የማይዝቱትን ‹‹ፀረ-ህዝብ›› ብሎ ሊጨፈጭፋቸው ይችላል፡፡ … ይኸም የድብርት አይነት ነው፡፡ በሦስተኛው የድብርት እርከን ላይ የሚገኝ ነው፡፡ አጥፊው የድብርት አይነት። አጥፊው ድብርት ጽንሰ ሀሳብ ተመርኩዞ፣ ለጠቅላላ የሰው ልጆች ጮራ የምፈነጥቅ ብቸኛው አማራጭ ነኝ ብሎ ራሱን ያስተዋውቃል፡፡ ተግባሩ ሌላ ስብከቱ ሌላ ይሆናል፡፡
በሁለተኛው አለም ጦርነት ወቅት በጃፓን ላይ ከተጣሉት ሁለት ቦንቦች አንደኛው ከመፈንዳቱ አስቀድሞ ስም ወጥቶለት ነበር - ‹‹little boy›› ነው ስያሜው፡፡ ቦንቡን ጠበል አስመስሎ መሳል የአደገኛ ድብርት መገለጫ ነው፡፡ የአተም ቦንብን “ትንሹ ህፃን ልጅ” ብሎ በመጥራት እንቦቃቅላ አበባ ሲፈነዳ የሚሰጠውን አዎንታዊ፣ ተስማሚ ገፅታ ለመፍጠር ጥረዋል፡፡… ሲፈነዳ የታየው ግን ሌላ አሰቃቂ ነገር ነው። መልካም ነገርን ነው የምናፈነዳው መልካም ውጤትን ለማግኘት… የሚል ሰበካ ከአደገኛ የድብርት የዘመን መንፈስ የሚመነጭ  ነው። ‹‹የፀደይ አብዮትም›› ተመሳሳይ ምስል መፍጠሪያ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ ስሙን የሚመስል አይደለም፡፡ ማዛጋትን እስክስታ ለማስመሰል እንደ መጣር ነው፡፡
የሰው ልጅ ድብርት ውስጥ ከሆነ እውነታውን እንዳለ መቀበሉ ይሻላል፡፡ ድብርትን የእድገት ወይንም የተስፋ ጮራ አድርጎ “ያልተደበሩትን” ለመስበክ ከመትጋት የተሻለ ነው፡፡ አሁን ላለው በቀላሉ የሚደበር የአለም ህዝብ የተለያየ ሳቢያ እያመረቱ ወይንም በመረጃ መልክ እያቀረቡ ግራ የሚያጋቡ ሁሉ… ከዚህ የሦስት እርከን የ‹‹Boredom›› ሰንጠረዥ ነፃ የወጡ ቢመስሉም ነፃ ግን አይደሉም፡፡
ዣን ማርክ ስለ ራሱ አባት ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአስራ አራት አመት ልጅ እያለሁኝ ወንድ አያቴ ለመሞት እያጣጣረ የተከሰተው ነገር አሁንም ይታወሰኛል። በተጋደመበት አንድ ትርጉም የለሽ ድምፅ ከአፉ ያለ እረፍት ያፈልቃል፡፡ ድምፁ ማቃሰት ወይንም ሌላ ትርጉም የሚሰጥ የድምፅ አይነት አይደለም፡፡
ሊያቃስት አይችልም፤ምክኒያቱም ህመም ውስጥ አልነበረም፡፡.. ለመናገር እየሞከረ አይደለም። መናገር አቁሟል፤ የሚናገረው መልዕክትም ፈፅሞ የለውም።… የሚናገረው መልዕክት ቢኖረው እንኳን በተኛበት ክፍል ውስጥ ማንም ሰው አብሮት የለም፡፡ በአስራ አራት አመት እድሜዬ ለምን ያንን ትርጉም የለሽ ድምፅ ተጋድሞ እንደሚያፈልቅ አላቅም ነበር፡፡ አሁን ከፍ ስል ግን ገባኝ… ድብርት ነው የሚያስለፈልፈው፡፡ ተጋድሞ ሞቱን እየጠበቀ ባለበት ቅጽበትም ቢሆንም---የተጫነበትን ድብርትና በድብርቱ ጫና ምክኒያት አልነቃነቅ ያለውን ጊዜ ለመግፋት ሲል ትርጉም የሌለው ድምፅ እየደጋገመ ይጮሀል..››  
ሰውየው እየሞተ እንኳን ከድብርቱ መላቀቅ አልቻለም፡፡… ድብርት የትርጉም ማጣት ብቻ አይደለም፡፡ ትርጉም የማፈላለጊያ ፍላጎትንም አብሮ ማጣት ነው፡፡ ፍላጎት ያላቸው ላይም ማላገጥ፡፡ በጠፋ ፍላጎት አርፎ ወደ ሞት በመሄድ ፈንታ ሌሎችን በመበጥበጥ፣ የሌሎችንም ትርጉም የሚያጠፋ ጊዜያዊ ተልዕኮ ቀርፆ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡
…በሰው እያላገጡ ‹‹ሙድ›› መያዝ… ለማንም አይጠቅምም… ሙድ ያዥም ከቅፅበት ወደ ቅፅበት ጊዜን ለመራመድና ከድብርት ለማምለጥ ሌሎችን እያበሸቀ ከመቀጠል ከፍ ያለ ተስፋ የለውም። “ሙድ” በመያዝ ድብርትን ለቅፅበትም ቢሆን መፈወስና አቶም ቦንብ በመጣል የተወሰኑትን ከምድረ ገፅ መፋቅ  ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ሁለቱም ከድብርት ነፃ የመውጫ መንገዶች ናቸው። የድብርቱ ተጠቂ ከግለሰብ (ሙድ ያዥ) ጀምሮ እስከ መንግስታዊ ተቋም ድረስ ሊያድግ ይችላል፡፡ ወይንም ሀይማኖታዊ ሰውነት ያለው መስሎ ሊገዝፍ ይችላል፡፡ .የፈለገ ቢገዝፍ ወይንም ቢገንን … ተቋምም ይሁን መንግስት እምነቱንና ተግባሩን በማነፃፀር ብቻ ነው “የድብርት በሽታ ተጠቂ” መሆኑን ወይንም አለመሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው፡፡
“እብድ መሪ” የሚለው አገላለፅ “የድብርት ተጠቂ መሪ” ከሚለው የበለጠ አስፈሪ አይደለም። እብድ የሚያደርገው ይታወቃል። በእብድ አቅም ማድረግ የሚቻለው ውሱን ነው። ምክኒያታዊነት ወደ ታች በአናቱ ሲዘቀዘቅ እብደት ነው ውጤቱ። ምክኒያታዊና ተያያዥነት ባለው አስተሳሰብ እኩይነትን መልካም አስመስሎ እንደ አብዮት የማስፋፋቱ አቅም ግን የድብርት ተጠቂው እንጂ የእብዱ አይደለም፡፡ ረቂቅ ድብርት ከእብደትም ይከፋል፡፡ “እያነቡ” ሳይሆን … “እያዛጉ” እስክስታ መውረድ ነው ወደ አደጋ እየወሰደን ያለው፡፡  

Read 1301 times