Sunday, 19 February 2017 00:00

በድርቅ ከብቶቻቸው ለሞቱባቸው አርብቶ አደሮች ዛሬ 1.6 ሚ ብር የመድን ዋስትና ካሳ ይከፈላል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በኦሮሚያ ክልል በቦረናና በምዕራብ ጉጂ ዞን አካባቢ ከብቶቻቸው ለሞቱባቸውና ጉዳት ለደረሰባቸው 1474 አርብቶ አደሮች፣ የኦሮሚያ
ኢንሹራንስ ኩባንያ 1.6 ሚሊዮን ብር የመድህን ካሳ ይከፍላል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፣ ኤልኒኖ ባስከተለው
ድርቅ ምክንያት ከብቶቻቸው ለሞቱባቸውና ለተጎዱባቸው አርብቶ አደሮች፣ በገቡት የመድህን ዋስትና መሠረት፣ ዛሬ በቦረና ዞን በያቤሎ ከተማ 1.6 ሚሊዮን ብር ካሳ እንደሚከፍል አስታውቋል፡፡የከብት ሀብት ዋስትና ሽፋን የሚሰጠው ለረዥም ጊዜ በተሰበሰበ የአየር ሁኔታ መረጃና በተጠና ቀመር ላይ ተመስርቶ ሲሆን አንድ አርብቶ አደር አገልግሎቱን ለማግኘት በአንድ ዓመት ውስጥ ላሉ ሁለት ዝናብ አጠር ወይም የበጋ ወቅቶች ለከብት መኖ የሚያወጣውን ወጪ ከ7-11 በመቶ የሚደርስ ግምት ፕሪሚየም መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹አንድ ግመል በእነዚህ ሁለት ወቅቶች የ5 ሺህ ብር መኖ ይፈልጋል፡፡ ፍየልና በግ የ500 ብር መኖ፣ አንድ በሬ ወይም ላም የ3 ሺህ ብር መኖ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት፤ ለአምስት በሬዎች ዋስትና መግዛት የሚፈልግ አርብቶ አደር የ3 ሺህ ብር 7 በመቶ ሲባዛ በ5 በድምሩ 1050 ብር ፕሪሚየም መክፈል ይጠበቅበታል።›› ሲሉ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የከብት ሀብት ዋስትና ከፍተኛ ባለሙያ፣ አቶ ጌታሁን ኢሬና ገልጸዋል፡፡
የፕሪሚየም ደጎማ ለአርብቶ አደሮቹ ዋስትና ማግኘት መሰረታዊ ነገር መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታነህ፤ ‹‹የክልልና የፌደራል መንግሥት እንዲህ
አይነት ድጎማ ማድረግን ከግምት ውስጥ ቢያስገቡ፣የዋስትና ተጠቃሚ አርብቶ አደሮችን ቁጥር በማሳደግ ከድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል›› ብለዋል፡፡በከብቶች ላይ ለሚደርስ የከብቶች ጉዳት ካሳ ማግኘት የሚያስችል የመድህን ሽፋን አገልግሎት፣
ለአሮሚያ ክልል አርብቶ አደሮች መስጠት የተጀመረው በ2004 ዓ.ም በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያና በዓለም አቀፍ የከብት ሀብት ምርምር
ተቋም ትብብር ሲሆን የከብት ሀብት መድህን ፕሮጀክት ሀሳብ ያመነጨው ይህ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም፣ ከአሜሪካ የጠፈር ምርምር
ድርጅት (ናሳ) የሚያገኘውን የአየር ሁኔታና የአየር ንብረት የሚመለከት ዝርዝር መረጃ ለኢንሹራንስ ኩባንያው ያቀርባል። በዛሬው ዕለት የሚፈጸመው የካሳ ክፍያ የዋስትና አገልግሎቱ ከተጀመረ ከሐምሌ 2004 ዓ.ም ጀምሮ 4ኛው ዙር ሲሆን፤ የዕለቱን 1,474 አርብቶ አደሮች ጨምሮ በጠቅላላው እስካሁን ድረስ ለ4,588 አርብቶ አደሮች ካሳ መከፈሉ ታውቋል፡፡

Read 1013 times