Sunday, 19 February 2017 00:00

ሠማያዊ ፓርቲን አቶ የሸዋስ አሰፋ እንደመሩት ምርጫ ቦርድ ወሠነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ለወራት ሲያወዛግብ በነበረው የሠማያዊ ፓርቲ አመራርነት ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በቅርቡ በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡት አቶ የሸዋስ አሰፋ  የፓርቲው ህጋዊ ሊቀመንበር መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ተስፋለም በላይ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ ባደረሱት መረጃ፤ ጉዳዩን ሲመርምር የቆየው ቦርዱ ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ፣ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት ግቢ ለተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና ሰጥቶ፣ በጉባኤው የተመረጡት አቶ የሸዋሰው ህጋዊ ናቸው ብሏል፡፡
የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ፤ ‹‹የስራ አስፈፃሚው የተሠጠውን ሃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም ብለው ካመራ የፓርቲው የኦዲትና ኢንስፔክሽን የመተማመኛ ድምፅ ሊነፍገው ይችላል፤ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤም በመጥራት ችግሩ እንዲፈታ ሊያደርግ ይችላል” እንደሚል የጠቀሱት አቶ ተስፋለም ጉባኤው በዚህ መንገድ የተካሄደ መሆኑ ተረጋግጦና ምርጫ ቦርድም ጉባኤው ያላሟላቸውን እንዲያሟላ 7 ያህል ደብዳቤ ልውውጦችን በማድረግ ለጉባኤው እውቅና ሰጥቶታል ብለዋል፡፡
የቦርዱን ውሳኔ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ቅሬታ አቅርበው የነበሩት የፓርቲው የቀድሞ ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ውሳኔውን በመረጃ ደረጃ መስማታቸውን ጠቁመው በውሳኔው ላይ ቀጣይ እርምጃቸውን ለመወሰን አብረዋቸው ካሉ የፓርቲው አመራሮች ጋር ዛሬ እንደሚመክሩ አስታውቀዋል፡፤
“ከምርጫ 97 ጀምሮ በቅንጅት ላይ፣ በዶ/ር መረራ ፓርቲ አብኮ ላይ፣ በአንድነት ላይ እና በመኢአድ ላይ የተወሰኑትን ውሳኔዎች እናውቃለን” ያሉት ኢ/ር ይልቃል በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተወሰነውም የተለመደው ውሳኔ ነው ብለዋል፡፤
ጉባኤው ህጋዊ መስፈርት የማያሟላ መሆኑን በዝርዝር ለቦርዱ አቅርበው እንደነበር የገለፁት ኢ/ር ይልቃል፤ “ቀጣይ እጣ ፋንታችንና ወደ ፍርድ ቤት የማምራት ጉዳዩን ዛሬ ተሰብስበን እንወስናለን ብከለዋል። ብዙ የፓርቲው አባላትን የሚያስከፋ ውሳኔ መሆኑንም ኢ/ር ይልቃል ተናግረዋል፡፡
በቦርዱ ዕውቅና ያገኙት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ ሰማያዊ ፓርቲን በመመስረት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በሽብርተኝነት ተጠርጥረው እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ሰብሳቢ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
በተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ከአንድ አመት በላይ በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ በከፍተኛው ፍ/ቤት በነፃ ተሠናብተው ይግባኝ ቢጠየቅባቸውም በይግባኙም በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

Read 1484 times