Sunday, 19 February 2017 00:00

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር 25ኛ ዓመታ የብር ኢዮበልዩ በዓሉን አከበረ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

      የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር 25ኛ ዓመት የብር ኢዮበልዩ በዓሉን ያከበረ ሲሆን ማኅበሩ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አሳታውቀዋል፡፡
ማኅበሩ 25ኛ የብር ኢዮበልዩ በዓሉንና ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ በሸራተን ሆቴል ባከበረበት ወቅት የቦርድ ሊቀመንበሩ ኢ/ር አበራ በቀለ፣ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ማኅበሩ ስኬታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የአባሎቻቸው የመፈፀም አቅም እየጎለበተ የኮንትራት አስተዳደር፣ የሳይት ማኔጅመንትና የኩባንያ አደረጃጀት እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩ ሲመሠረት የአባላት ቁጥር 30 እንደነበር የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ በአሁኑ ወቅት የአባላት ቁጥር ከ1600 በላይ መድረሱን፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በክልል ከተሞች በባህርዳር፣ በመቀሌና በሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መክፈቱ የስኬታማነቱ መገለጫ ናቸው ብለዋል፡፡
አገሪቷ ባለፉት 25 ዓመታት ያከናወነቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የቤቶች ግንባታ፣ የመንገዶች፣ ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦች…. ፕሮጀክቶችና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም አይመጣጠንም ያሉት ኢ/ር አበራ፤ ከመንግሥት ጋር በጣምራ በመሆን ኮንትራክተሮች ራሳቸውን የሚያደራጁበት የአቅም ግንባታ ሥራ ይጠብቀናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቶችን መጓተትና መዘግየት በተመለከተ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ውጫዊ የምንለው፣ ሥራው ለኮንትራክተሮች ሲሰጥ ፅድት ብሎ ተሰርቶ፣ ፕላኑ ፣ በጀቱ፣… ካልተሰጠ፣ ፕላኑ የሚቀየር፣ በጀቱ የሚቀነስ ከሆነ፣ ከሥራው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ሥራ ካልተጠናቀቀ፣ ማለትም ሥራው ከመጀመሩ በፊት የተጠናቀቀ ዶክመንት ካልቀረበ  ፕሮጀክቱ ይጓተታል፡፡ ውስጣዊ ምክንያቶች የሚባሉት ደግሞ የኮንትራክተሩ የአቅም ማነስ ችግር ነው፤ በተለይ የፋይናንስ፡፡ “የኮንትራክተሩ ገንዘብ ያለው ሚክሰር፣ ገልባጭ፣ ዶዘር፣ የመሳሰሉት ላይ ስለሆነ ሥራ ማስኬጃ ያጥረዋል፤ ገንዘብ እስኪያገኝ ድረስ ሥራው ይዘገያል፣ ይጓተታል በማለት አስረድተዋል፡፡

Read 1089 times