Sunday, 19 February 2017 00:00

በአዲስ አበባ ከ45 ሺ በላይ ህፃናት ለአደገኛ ሱሶች ተጋልጠዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

 · ቤተሰብ … ት/ቤት … መንግስት .. ሱሰኛ ህፃናት መታደግ አለባቸው
                   · ት/ቤቶች ለህፃናት በሱስ መለከፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው
                      
     ሱስ አስያዥ ለሆኑ የተለያዩ ነገሮችና እፆች ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና፤ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንድ ጥናት አሳሰበ፡፡
“ፊዩቸር ኬር” በተሰኘ ድርጅት የተሰራውና ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ያልደረሱ በርካታ ህፃናት የተለያዩ ሱሶች ተገዥ እየሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሱሰኛ ህፃናት እስከ እብደት ሊያደርሱ በሚችሉ የአዕምሮ ጤና ችግር ሊጠቁ የሚችሉ ሲሆን ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከሱሰኛ ህፃናቱ መካከል በተለያዩ መንገዶች ራሳቸውን የሚያጠፉ ህፃናት ቁጥርም እየተበራከተ መምጣቱን ጥናቱ አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ በተደረገው በዚሁ ጥናት መሰረት፤ በአገሪቱ ያሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት እጅግ አደገኛ ለሆኑ ሱሶች ተጋልጠዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ45 ሺ በላይ ዕድሜያቸው ከ4-15 ዓመት የሆናቸው ህፃናት፣ ለአደገኛ ሱሶች የተጋለጡ ናቸው ብሏል ጥናቱ፡፡
የህፃናቱ የአደንዛዥ እፆች ሱሰኝነት መበራከት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለከተው ጥናቱ፤ ከሱሰኛ ህፃናቱ መካከል ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፈልባቸው የግል አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተማሪዎችና የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ጠቁሟል፡፡
ከዓመታት በፊት በግዮን ሆቴል ተካሂዶ የነበረውንና በአፍሪካ የህፃናት ፖሊሲ መድረክ የህፃናት ህጋዊ ከለላ ማዕከል ተዘጋጅቶ የነበረውን ጉባዔ መነሻ ማድረጉን የገለፀው ይኸው ጥናታዊ መረጃ፤ የህፃናቱ የአደንዛዥና አፍዛዥ ነገሮችና እፆች ሱሰኝነት ችግር ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡
ወላጆች ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ልጆቻቸውን የተሻለ ትምህርት ለማስተማርና ብቁ ዜጋ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉበት ሁኔታ እየተበራከተ መምጣቱን የጠቆመው መረጃው፤ በዛው መጠን ከየት/ቤቶቹ ደጃፍ ላይ እንደ አሸን በፈሉት የሱስ መለከፊያ ጎተራዎች ውስጥ እየገቡ በአደንዛዥ እፅ ሱሰኝነት እየተመረቁ የሚወጡ ህፃናት ቁጥር ተበራክቷል ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉና ስማቸው ባልተገለፀ አምስት ስመ-ጥር ት/ቤቶች ውስጥ በሚማሩ እድሜያቸው ከ7-15 ዓመት በሆናቸው ተማሪዎች ላይ ጥናት መደረጉን ያመለከተው መረጃው ጥናት ከተደረገባቸው 283 ተማሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ በት/ቤቶቻቸው አካባቢ በሚገኙ እንደጫት ቤትና ሺሻ ቤቶች ያሉ የሱስ መሸመቻ ጎተራዎች ደንበኞች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች እነዚህን ቤቶች በየዕለቱ ይጎበኙዋቸዋል፡፡
ሱስ አስያዥ አደንዛዥ እፆች የተለያየ የዓይነትና መጠን እንዳላቸው ያመለከተው ጥናቱ፤ በት/ቤቶች አካባቢ በሚገኙ ህፃናት ሱሰኞች የሚዘወተሩት በቁም ቅዥት ዓለም ውስጥ የሚከቱ፣ የሚሸተቱና በያዙት ሱስ አስያዥ ሽታ ሳቢያ ሱሰኛ የሚያደርጉ የእፅ አይነቶች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ተማሪ ህፃናት ሱሰኝነት መጋለጥ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ በጥናቱ የተጠቀሰው በት/ቤቶቹ አካባቢ ሆን ተብለው የሚከፈቱ ሺሻ ቤቶች፤ ጫት ቤቶች፣ ከረንቦላ ቤቶችና በአሁን ወቅት እየተላመዱ የመጡት የቀን ጭፈራ ቤቶች ናቸው፡፡ በከተማዋ በሚገኙ እንደ ቦሌ፣ መገናኛ ሲኤምሲ አካባቢ ባሉ የግል ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ህጻናት፤ በተለያዩ ሱሶች በከፍተኛ መጠን እየተያዙ መሆናቸውን የጠቆመው መረጃው፤ በት/ቤቶቹ አቅራቢያ በሚገኙ መጠጥ ቤቶች ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት ቦታች የሆኑ ህፃናት ሲጋራና በሲጋራ መልክ ተጠቅልሎ የተዘጋጀ ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ እፅ እንደሚያጨሱም በጥናቱ መረጋገጡን አመልክቷል፡፡ በአንዳንድ የሱስ መለከፊያ ሺሻ ቤቶችና ጫት መቃሚያዎች ላይ ተማሪዎች ከነዩኒፎርማቸው ማየት የተለመደ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ በየመጠጥ ቤቶቹ ጎራ ለይተው እያውካኩ መጠጣት፣ በቂማ ቤቶቹ ፈርሸው ሲቅሙ መዋል፣ የሺሻ ፓይፓችን እየሳቡ በጭሱ መዝናናት፣ አለፍ ሲልም በሲጋራ ወረቀቶች እየተጠቀለሉ በሚሸጥላቸው ካናቢስ መጦዝ … ቦሌ አካባቢ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ በሚማሩ  ህፃናት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ህፃናቱ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚከለከል አሊያም የሚፈፀሙት ድርጊት እጅግ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጣቸው መሆኑን አበክሮ የሚያስተምር አካል ባለመኖሩ ምክንያት ህፃናቱ አሁንም ወደ ጥፋት ጎዳናው ከማምራት አልተቆጠቡም፡፡
ለሱሰኛ ህፃናት ቁጥር መበራከት ዋንኛ ምክንያቶች ተደርገው ከተገለፁት ጉዳዮች መካከል የአቻ ግፊት፣ ተቆጣጣሪ ማጣት፣ ከጓደኛ ያለመለየት ፍላጎት፣ የቤተሰብ መፈናቀልና የጎዳና ህይወት መሆናቸውን ይኸው ጥናት አመላክቷል፡፡ አብዛኛዎቹ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት፤ ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ከእነሱ ቀድመው የጎዳናውን ህይወት የጀመሩ ጓደኞቻቸው የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ቀድመው በሱስ የተያዙት ጓደኞቻቸው ደግሞ ሕፃናቱን ወደ ሱስ ገደል ጫፍ ይመሯቸዋል፡፡
ጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ከሚያዘወትሩአቸው ሱስ አስያዥ አደንዛዥ ነገሮች መካከል እነሱ “ጡጦ” እያሉ የሚጠሩት፣ በአፍና በአፍንጫ የሚሳበውና ህሊናን የማሳትና የማደንዘዝ ባህርይ ያለው ነገር ዋነኛው ነው፡፡  አብዛኛዎቹ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት፤ ከቫርኒሽ ቀለሞች፣ ከጫማ ማጣበቂያ ማስቲሽና “ቺፍቼ” እያሉ በሚጠሩት የናፍታ ፍሳሽ በሚያዘጋጇቸው (በአፍና በአፍንጫ የሚወሰዱ) አደገኛ አደንዛዥ ነገሮች አእምሮአቸውን ያደነዝዛሉ፤ ረሃብ፣ ብርድ፣ ውሃ ጥም፣ ድካምና ህመምን ያስረሳል በሚሉት በነዚህ ለጤና እጅግ አደገኛ በሆኑ ነገሮች እስከ እብደት ሊያደርሱ ለሚችሉ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡
የምግብ ፍላጎት ስለማይኖራቸውና ምግብ ሰለማይመገቡ በቀላሉ ለተለያዩ የጤና ችገሮች ይጋለጣሉ፡፡ አብዛኞዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች እራሳቸውን እንዲያጠፉ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች መካከል ዋንኛውም የሱስ ተገዥነታቸው ነው፡፡ ራሳቸውን በተለያዩ መንገዶች ያጠፉ ሱሰኛ የጎዳና ህፃናት መኖራቸውንም ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
እነዚህ የዚች አገር ተረካቢ ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ለጋ ህጻናት፣ ያለ ዕድሜያቸው የሱስ ተገዥ ሆነው ሲሰናከሉ ማየት  ለማንኛውም ዜጋ ከባድ ራስምታትና የጊዜው የአደጋ ጥሪ ደወል መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና ህፃናቱን ከአደገኛ እፆች ሱሰኝነት ለመታደግ አሁንም አልረፈደም ይላል፡፡ በቅዱስ ጳውሎ እና በአማኑኤል ሆስፒታሎች ውስጥ እንዳሉት የሱስ መላቀቂያና ማገገሚያ ማዕከላት ሁሉ፤ ህፃናቱን ከአደገኛ ሱሰኝነታቸው ሊያላቅቁ የሚችሉ ማዕከላት በመገንባትና በህፃናቱ ህክምናና እንክብካቤ በመስጠት ከችግራቸው ማለቀቅ እንደሚገባም ጥናቱ በማጠቃለያው ላይ አስገንዝቧል፡፡ የህፃናትን ሱሰኝነት ለመከላከል ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንግስትና ሁሉም ዜጎች ኃላፊነት እንዳለባቸው “””በጥናት ውጤቱ ላይ ተገልጿል፡፡

Read 3447 times