Sunday, 19 February 2017 00:00

የዓለማየሁ ገላጋይ ፈለጎች

Written by  ቴዎድሮስ አጥላው
Rate this item
(55 votes)

     ዓለማየሁ ገላጋይ፣ መደቡ ዮናስ አድማሱ “ሙያውን የሚያውቁ” ከሚሏቸው ዐይነት ደራሲዎች ወገን የሆነ፣ የሚጽፈው ምናባዊ ይሁን እውናዊ ታሪክ፣ ለታሪኩ የሚያለብሰው የሀሳብና የስሜት ስጋና መንፈስ፣ ይህንኑም ለአንባቢ የሚያቀርብበት ቅርፅ (ማህደሩ)፣ እነዚህን ሁሉ ወደ አንባቢው የሚያደርስበት ቋንቋ እጅግ የሚያሳስበው ደራሲ ነው፡፡ “አጥቢያ”፣ “ቅበላ”፣ “የብርሃን ፈለጎች”፣ “ወሪሳ”፣ “በፍቅር ስም” የተባሉት ረጅም ልቦለዶቹ እና “ኩርቢት” የአጫጭር ልቦለዶች መድበሉ ሙያውን አውቆ ስለመጻፉ ምሥክሮች ናቸው፡፡
በዚህ ጽሁፍ፤“በፍቅር ስም”ን ጨምሮ፣ በዓለማየሁ ገላጋይ የረጅም ልቦለድ ሥራዎች ውስጥ ተደጋግመው ካየኋቸው ወካይ ነጥቦች መሐል ጥቂቶቹን አቀርባለሁ።
ድርሰቶቹ አውደ
ሙከራዎቹ ስለመሆናቸው
የዓለማየሁ ገላጋይን ሥራዎች ጠቅለል አድርጎ ለማጥናት የሚሞክር ተመራማሪ ሊደርስባቸው ከሚችላቸው ድምዳሜዎች አንዱ ሰውየው Experimental Novelist ነው የሚል ይመስለኛል። አሌክስ የእሱ ዘመን የድረሳ ልማድ/ዘይቤ ላይ በመሸፈት፣ ድርሰቶቹን ቢያንስ ለዘመኑ የአማርኛ ስነጽሑፍ አዳዲስ የሆኑ የአደራረስና የአቀራረብ ስልቶቹን የሚሞክርባቸው አውደ ሙከራዎች/ላቦራቶሪዎች ያደርጋቸዋል፡፡ አማርኛ ዘመናዊ ልቦለድን በ“ጦቢያ” ተዋውቆ፣ በእነሐዲስ አለማየሁ ከተራቀቀበት ወዲህ፣ ከወዲያ እነ ዳኛቸው ወርቁ በ“አደፍርስ”፣ ከወዲህ እነ በእውቀቱ ስዩም በ”እንቅልፍ እና ዕድሜ”፣ አዳም ረታ በኖቭሎቹ እና በአጫጭር ተረኮቹ እንዳደረጉት፣ ዓለማየሁ ገላጋይም በሁሉም ኖቭሎቹ ከነባር ስልት ያፈነገጡ ስልቶችን ለጭብጦቹ ማዳበሪያና ማጉያነት፣ ለታሪኮቹና ሐሳቦቹ ማቀበያነት ይጠቀማል፡፡
በ“አጥቢያ” ወዳጄ ዮናስ ታረቀኝ “ጦማራዊ ልቦለድ” ብሎ የተረጎመውን አጻጻፍ (Epistolary writing) በ1999 ዓ.ም. አስተዋውቆናል፤ ይህች የመጀመሪያ ረጅም ልቦለዱ፣ አሁን ታሪክ የሆነውን የአራት ኪሎን ህይወት ከሚተርኩ እውናዊ ደብዳቤዎችና ደብዳቤያዊ ድርሰቶቹ የዋና ገጸባሕርያቱን ያህል ሚና ከሚጫወቱበት አጓጊ ታሪክ የተዋቀረች ልቦለድ ናት፡፡ ደብዳቤዎች፣ (እውነተኛ ደብዳቤዎች) ልቦለድ ውስጥ ይህንን ያህል ወሳኝ ሚና ኖሯቸው የቀረቡበት የአማርኛ ረጅም ልቦለድ ከ“አጥቢያ” በፊት አላጋጠመኝም፡፡
በ2001 ያሳተመው “ቅበላ” የዓሌክስ ፍንገጣ ጠንከር ብሎ የመጣበት አውደ ሙከራው ነው፡፡ ዓሌክስ የድርሰት ኤክስፐርመንቱን ልብ እንድንልለት አስቀድሞ በገጠ-ጡፋዊ አቀራረቡ ያነቃናል፡፡ ድርሰቱ “ክስ”፣ “ፍትህ” እና “ፍርድ” በሚሉ ሦስት ክፍሎች የቀረበ ሆኖ፣ በተለይ “ክስ” የተባለውና አንብበን ካስቀመጥነው ወዲያም የአንጎል ግድግዳችን ላይ እንደ ሸህላ ተመርጎ የሚከርምብንን ህማም የሚተርከው ክፍል ካሉት አስር ምዕራፎች፣ ጎዶሎዎቹ ምዕራፎች (1፣ 3፣ 5፣ 7 ፣9) በጥቁር ገፅ ላይ ርእሳቸው ብቻ ተጽፎ የተተዉ ናቸው፡፡ የተተረከውን ህማም ስናነብ በእነዚህ ጎደሎ ምዕራፎች ሳይተረክ የተተወውን፣ ምናልባት በቃላት ሊገልፁት፣ ወይም ምናልባት ለሰው ገልፀው ሊነግሩት የሚከብድ ህማም ልንገምት እንችላለን፤ በዚህ አኳኋን፣ ደራሲው በንባብ ብቻ ሳይሆን በድረሳ ተግባሩም ከጎኑ ያሰልፈናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፣ ዓለማየሁ በ“ቅበላ” ድርሰቱ የድኅረ ዘመናዊ ልቦለዶች መገለጫዎች ተደርገው ከሚጠቀሱት ባህርያት ሜታፊክሽን  (ምናልባት “ዲብ” የሚለውን የግዕዝ ቃል ከልቦለድ ጋር አቀናጅተን “ዲበ-ልቦለድ” ልንለው እንችላለን) የሚባለውን ስልት በልቦለድ ውስጥ ሌላ ልቦለድን በመተረክ አቅርቧል፤ይህ ድርሰቱ የዲበ-ልቦለድ ቤተ ሙከራው ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ድርሰቱ እኛ ጋ የሚደርሰው ሁለት ምናባዊ ዓለማትን አነባብሮ ነው፡፡ አንደኛው ዓለም ራሱን እውናዊ አስመስሎ ውስጡ ያለውን ዓለም ደግሞ ምናባዊ ሊያደርግብን ይሞክራል፡፡ በልቦለዱ ሆድ ውስጥ ያለውን ልቦለድ የሚተርክልን በአቃፊው ልቦለድ ውስጥ በደራሲነት የምናገኘው ማቴዎስ የተባለ ገፀባህርይ የሁለት ዓለማት ገፀባህርይ ሆኖ እናገኘዋለን። ድርሰቱ በታቃፊው (Inscribed) ልቦለድ ያሉትን ገፀባህርያት፣ ታሪካቸውንና ዓለማቸውን በአቃፊው ልቦለድ ውስጥ በማምጣት፣ ታቃፊውን እንደ ልቦለድ፣ አቃፊውን ደግሞ እንደ እውናዊ ተረክ እንድንቆጥረው ይታገለናል፡፡
ወደዚህ ትንታኔ የሚገፋፋን ይሄ ዲበ-ልቦለዳዊነት ብቻም አይደለም፡፡ ልቦለዱ በግልፅ ልቦለድነቱን ሲክድ እናገኘዋለን፡፡ እዚሁ ድርሰት ውስጥ ከዋና ገፀባህርያቱ አንዱ “ይሄ ህይወት ባይሆንና ድርሰት ቢሆን ኖሮ...” ብሎ ያስደነግጠናል፡፡ ይኸው ገፀባህርይ ቀደም ባለ የመጽሐፉ ክፍል ድርሰትንና ደራሲን በመተቸት፣ አንባቢውን ማመንታት ውስጥ ይከታል። በትረካው ውስጥ ገንኖ የሚሰማው የእሱ ሐሳብ እንደመሆኑ፣ ወይም ትረካው ከዚሁ መንክር ከተባለ ገፀባህርይ አንፃር እንደመተረኩ ትችቱን የሚሞግት ሐሳብ አናገኝም፡፡ “ደራሲ ሥራው መፍጠር ነው። ሌላ አይደለም የሚፈጥረው፤ የተቀናበረ ውሸት፣ የተደራጀ ቅጥፈት ነው የሚፈጥረው፡፡ ... ደራሲ ትልቅ ቆርጦ ቀጥል ነው፡፡ የቅጥፈት ስልቱ ያልገባው ተራ ሰው ውሸታም፣ ወሬኛ እየተባለ ክብሩ ሲገፈፍ የተሳካለትና በስልት የዋሸው ግን ‘ደራሲ’ ተብሎ ይወደሳል፣” ይላል።
እንደ ግሩም ግጥም፣ በተነበበ ቁጥር ሌሎች ትርጓሜዎችን የሚያነቃው፣ ሌሎች ትዝታዎችን የሚቀሰቅሰው፣ ሌሎች ስሜቶችን የሚያባንነው “ወሪሳ” ደግሞ፣ የዓለማየሁ ከቀድሞው/ከነባሩ የተለየ ነገር የመስጠት ጠባይ ይበልጥ በርትቶ የታየበት ድርሰት ነው፡፡ በዚህ ድርሰት ዓለማየሁ እንደ ጋብሬል ጋርሺያ ማርቆስ፣ እንደነ ሁሊዮ ኮርታዛር፣ ምትሃታዊ እውነታዊ/ማጂካል ሪያሊስት ሆኖ ይመጣል፤ እንደ ፋንታሲ ደራሲዎች ከእውናዊው ዓለም የተለየ የአሰፋፈር፣ የአኗኗር፣ የአስተዳደር ደንቦች ያሏቸውን ምናባዊ መቼቶችም ይሰጠናል፡፡
የ“ወሪሳ” ታሪክ የሚከናወንባቸው መቼቶች፣ የዘራፊዎቹ ምድር ወሪሳ እና የፀበኞቹ ምድር እሪ በከንቱ በጠላትነት የሚተያዩ ተጎራባች መንደሮች ናቸው፡፡ የእነዚህ ዓለማት እውነታ ከምንኖርበት ዓለም እውነታ የተቀዳም ቢሆን፣ የአንድ ማኅበረሰብ መለያ ሆኖ ሲመጣ ግን ቢያንስ የኛ እውነታ ነው ብለን ከምናምነው ጋር ይማታብናል፡፡ ወሪሳዎች የሌብነትን፣ የነጣቂነትን፣ የዘራፊነትን ትክክለኛ ማኅበራዊ እሴትነት እያጸደቁ፣ እሪ በከንቱዎች ደግሞ ወንድ ልጅ ካልተጣላ፣ ካልገደለ፣ ካልተካሰሰ ... ምኑን ወንድ ሆነው የሚል ማኅበራዊ እሴት እያወደሱ የሚኖሩ ናቸው፡፡
በእኔ ንባብ “ወሪሳ” ተቀጣጣቢ (Parodist) ድርሰት ነው፤ ታሪካችንን፣ ፖለቲካችንን፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን፣ ትምህርታችንን በተውላጠ ታሪኮች (Alternate History) እንደ አዲስ እንድናየው፣ እየሳቅን እንድንሳቀቅበት፣ መጪውንም እንድንፈራው ያደርገናል፡፡ በ“ወሪሳ” የአለማየሁ ገላጋይ ቀልድ አዋቂነት፣ በቋንቋ እንዳሻው የመጫወት ብቃት፣ የተረት (የተውላጠ ታሪክም ጭምር) ፈጣሪነት አቅም የታየበት ድርሰት ነው፡፡
“በፍቅር ስም”ም እንዲሁ፣ ዓለማየሁ ከራሱም ሆነ ከነባር ድርሰቶቻችን አንጻር አዲስ ነገር የሞከረበት ነው፡፡ ከሙከራው ቀድሞ የሚመጣው በእውናዊው ዓለም እውነታ እና በድርሰቱ ምናባዊ እውነታ መሐል፣ ወይም በሌላ አነጋገር፣ በደራሲው እና በተራኪው መሐል እንደ ልማዱ ሊኖር የሚገባውን ድንበር ማፍረሱ ነው፡፡ የመጽሐፉን የህትመት መረጃዎች የሚይዘውን ክፍል ጨርሶ፣ ክፍል አንድ ብሎ ወደ ድርሰቱ ከገባ፣ የዚህን ክፍል ገዢ ርዕስ እና መሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካቀረበ በኋላ “መታሰቢያነቱ…” ብሎ ደራሲው በቅርቡ ያጣቸውን ወዳጆቹን የአብደላ ዕዝራን እና የአስማማው ኃይሉን ስም ይጠራል፡፡ ተራኪው ክፍል ሁለት እና ሦስትን ድርሰቱ ውስጥ ላሉት ገፀባህርያት መታሰቢያ ማድረጉን ስናይ፣ እውናዊዎቹን ሰዎች በመታሰቢያው አማካይነት የድርሰቱ አካል ማድረጉ ለምን ነው ያስብለናል፡፡
የዓለማየሁን የቀድሞ ድርሰቶች አስተውሎ ላነበበ ሰው (በተለይ “ቅበላ”ን እና “የብርሃን ፈለጎች”ን)፣ ይሄ ሰውዬ እውናዊው፣ ሕልማዊው እና ምናባዊውን እውነታዎች ሆነ ብሎ የማደባለቅ፣ መለያያ ግድግዳቸውን የማሳሳት ዝንባሌ እንዳለው ስለሚረዳ፣ “በፍቅር ስም” ለዚህ ሌላ ጥሩ ማስረጃ ይሆንለታል። እንግዲህ “በፍቅር ስም” ገና ከመነሻው በምናባዊ ድርሰት እና በእውናዊው ህይወት መሐል ያበጀነውን መስመር አጥፍቶ የሁለቱን ዓለሞች ግንኙነት ደግመን እንድንጠይቅ ቆስቁሶን ነው ወደ ትረካው የሚሻገረው። ይኸው የእውነታ ብዥታ የድርሰት ታሪኩ ውስጥ በተራኪው ታለሰው/አልአዛር እና በቹቹ መሐል በሚደረገው/ የሚደረግ በሚመስለው የማንነት ልውውጥም ላይ ይታያል፡፡
“በፍቅር ስም” በሌሎች ድርሰቶቻችን ውስጥ ፍትሐዊ በሆነ፣ ከፈራጅነት በተነጠለ አቀራረብ ሲካተቱ የማናያቸውን ከአደባባይ የተገለሉ/ችላ የተባሉ ሐሳቦችን የቃላት ስጋ አልብሶ በገለልተኝነት ተርኮልናል። ለምሳሌ ይሕ መጽሐፍ ህይወትን ባልተለመደ/በተገለለ የማኅበረሰባችን አካል ዐይን እንድናይ ዕድል ይሰጠናል፡፡ ተራኪው አልአዛር (ታለሰው) በእናቱ እና በስድስት እህቶቹ ታጥሮ በማደጉ የሴቶቹን ባህርይ የወረሰ፣ ሲሮጥ እንኳን ጭኖቹን ገጥሞ የሚሮጥ “ሴታሴት” ልጅ ነው፡፡ በሴቶች ግንብ ተከልሎ ባለበት ጠባብ ዓለሙ ውስጥ አድፍጦ፣ በሌሎቹ የአለማየሁ ድርሰቶች  እንደምናየው ሁሉ፣ የከተሜነት ለውጦች ያልበገሯቸውን የአዲስ አበባን የጎስቋላ መንደሮች አኗኗር የሴት ወይም የወንድ ብለን በማንለየው አተያዩ ያስቃኘናል፡፡
ሌላኛው የዚህ ድርሰት የተለየ ነገሩ፣ በሃይማኖት ተፅእኖ ምክንያት በአሉታ (በፈራጅነት) ካልሆነ በቀር የማናነሳውን የጥንቆላ/የአውሊያ ጉዳይ ተራኪው እና ጥቂት አልፎ ሂያጅ ገፀባህርያት በገባቸው ልክ ሲያስተናግደው፣ደራሲው የመናፍስቱን አሠራር ልክ/ስህተት መሆን አይበይንም፡፡ እንዲያውም የውይይት ሐሳብ አድርጎ የናዝሬቶቹን ጎረምሶች ያፈላስፍበታል፡፡
የሚወዳጁን ወይም የሚላከኩብን ገጸባሕርያት
በዓለማየሁ ገላጋይ ድርሰቶች ውስጥ የመርማሪን ትኩረት ከሚስቡት የድርሰቶቹ ባህርያት አንዱ የገፀባህርያቱ የተካነ አሣሣል ነው፡፡ በተለየ ድርጊታቸው፣ በንግግራቸው፣ በአነጋገራቸው ተለይተው የሚታወቁም የሚታወሱም “ሊትራሪ  ካሪኬቸር” ሊባሉ የሚችሉ ገፀባሕርያት አሉት። ኃይለሚካኤል እፉፉን፣ ፋሲልን፣ አምጰርጵርን፣ ብዜንን ከ”አጥቢያ”፣ ከ”ቅበላ”፣ ከ”ወሪሳ” እና ከ”በፍቅር ስም” በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ገፀባህርያት በያሉበት ድርሰት ከታሪካዊ ተሳትፏቸው ይልቅ በአመሳሰላቸው ወይም በአወካከላቸው ብቻ በአንባቢው ላይ የተለየ ስሜት የመቀስቀስ ሙያ የተሰጣቸው ናቸው፡፡
ለምሳሌ የ“ቅበላ”ው ፋሲል በየንግግሩ ላይ “ፀብ የማያስነሳ ከሆነ፣” የማለት አመል አለበት፤ ይህ አመሉ መጀመሪያ ላይ ሳቅን ያጭራል፤ እየተደጋገመ ሲመጣ ግን የልቦለድ ዓለም ሰሚዎቹን የሚያሰለቸውንና እና የሚያበሳጨውን ያህል የእኛን የአንባቢዎቹንም ትዕግስት ይፈታተናል፡፡ “በፍቅር ስም”  የተተረከበት ቤት አባወራ የሆኑት የብዜን “ጣ”፣የማስፈገጓን ያህል ድግግሞሿ ሲበዛ ታታክታለች፤በኋላ ደግሞ ተራኪው በሹፈት ሲያመጣት ታጫውታለች፡፡ በዚህ የካሪኬቸር ገፀባህርያት አቀራረፅ አፈወርቅ ገብረየሱስን እና ኋላ ደግሞ “ከአድማስ ባሻገር” ድርሰቱ ላይ በወጉ ከይኖ ያቀረበውን በዓሉ ግርማን ከስነጽሑፍ ታሪካችን በምሳሌነት ልንጠቅስ እንችላለን፡፡
የዓለማየሁ ገፀባሕርያት ሲያሻቸው እንደነ ጩና፣ ቻይና እና ናፍቆት ተወደው ይናፍቁናል፤ ሲያሻቸው እንደ “ቅበላ”ው ፋሲል፣ የ”ወሪሳው” ተራኪ መምህር፣ በንግግራቸው ወይ በድርጊታቸው ያበሳጩናል፤ እንደ “ቅበላዋ” የክቴ እና የ”በፍቅር ስሙ” ቹቹ ደግሞ ህማማቸውን አጋብተውብን ከአእምሯችን አልወጣ ይሉናል፡፡
የቋንቋ ጥብቅናው
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ የመጀመሪያ ዘመናዊ የአማርኛ ልቦለድ ነው የሚባልለትን፣ “ልብ ወለድ ታሪክ” (“ጦቢያ”) የተባለውን ድርሰት ያበረከቱልን ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ የአውሮፓውን የልቦለድ ቅርፅ ቀድተው ይዘውልን ከመምጣታቸው በላይ ግርማ ሞገሳቸው የሚታየን በቋንቋቸው ላይ ነው። ለዚህም፣ ሊቀ ማእምራን ታምራት አማኑኤል፤ “ስለ ኢትዮጵያ ደራሲያን” ብለው ከዛሬ ሰባ ሦስት ዓመት በፊት (በ1936 ዓ.ም.) በጻፉት ጽሑፍ ላይ “ላማርኛ አጻጻፍና ንግግር ብዙ ትጋት ያሳዩ … በነገር አስተያየትም መልክ ባለው ንግግር አሳብን በጽሕፈት በመግለጥ ልዩ ስጦታ ያላቸው ደራሲ ናቸው፣” ብለውላቸዋል፡፡ በዚያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ደግሞ ቀደምቶቹ እነ አፈወርቅ፣ እነ ኅሩይ፣ እነ ሐዲስ፣ እነ ዮሐንስ፣ እነ ዳኛቸው፣ እነ ጸጋዬ፣ … ለአማርኛ ቋንቋ ያሳዩት የነበረውን ትጋት ወርሶ፣ ታምራት አማኑኤል ለአፈወርቅ ገብረየሱስ የተጠቀሟቸውን ቅፅሎች የሚያስታውሰን ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በ“አጥቢያ” ተወልዶልናል፡፡
ዓለማየሁ ገላጋይ በሁሉም የፈጠራ ሥራዎቹ ከእሱ ዘመን ደራሲዎች በተለየ ለሚጽፍበት ቋንቋ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ትረካውንም ገለጻውንም ለአንባቢው ማሳየት የሚችል ደራሲ ነው፡፡ ከከተሜ የዕለት ከዕለት ተግባቦት ወደ ዳር እየተገፉ ያሉ ቃላት፣ ሐረጎች፣ አገላለጾች፣ ዘይቤዎችና ምሳሌያዊ አነጋገሮች ከ“አጥቢያ” እስከ “በፍቅር ስም” ድረስ ለዓለማየሁ ድርሰቶች መለያ ቀለማት ሆነውለታል፡፡ “ወሪሳ” ላይ ይህ ችሎታውና የቋንቋ ትኩረቱ ላቅ ብሎ ታይቷል፡፡ በአማርኛ ልቦለድ ውስጥ ተረትና ምሳሌዎች የተለያዩ ተግባራት ተሰጥቷቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ እናያለን፤ ነገር ግን በ“ወሪሳ” ደረጃ የገፀባህርያት ምልልስና የተራኪም ማሰላሰል ማድመቂያ እና ሐሳብን እና ስሜትን አጉልቶ ማቅረቢያ መሳሪያዎች ሆነው በስፋት የቀረቡባቸው መጻሕፍት አላጋጠሙኝም፡፡
ዓለማየሁ በተረት እና ምሳሌዎች አማካይነት አንባቢው የድርሰቱን ስለምን እንዲረዳለት ከማገዝ፣ በአገባባቸውም አማካይነት ከማዝናናት ባሻገር ተራኪውን አሰልቺ ለማድረግም ይሆነኝ ብሎ ተጠቅሞበታል፡፡ (ይሄ ምናልባትም ዋና ገፀባህርይውን ተሸናፊ በማድረግ ለልቦለዱ በአንባቢዎች የሚወደድ፣ የሚደነቅ፣ የሚታዘንለት፣ አርአያ  የሚሆን ተጋዳሊ (fictional hero) በመፍጠር ፈንታ ሆነ ብሎ  `anti-hero` ከመፍጠር ፍላጎት የመነጨ ይሆናል፡፡ ለነገሩ ደራሲው በየትኞቹም የረጅም ልቦለድ ሥራዎቹ አንድን ገፀባህርይ ለይቶ ለአርአያነት ሲያበቃው አናይም፡፡
በአጠቃላይ…
የዓለማየሁ ገላጋይ ሥራዎች ለሚጽፍበት ቋንቋ፣ ለሚተርከው ታሪክ፣ ለሚተርክበት ቴክኒክ፣ ለሚቆሰቁሳቸው ጥልቅ ኀሳቦች እኩል የሚጨነቅ ደራሲ እንዳለን ይመሰክራሉ፡፡ በእነዚህ አስር ዓመታት ከዓለማየሁ ያገኘናቸው ድርሰቶች፤በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ውስጥ የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊመረመሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ፣ ወጣት ጸሐፊዎች ሊከተሏቸው፣ መነሻ ሊያደርጓቸው፣ ካስፈለገም ሊወርሷቸው፣ የሚገቡ የአከያየን ስልቶችና የድርሰት ኀሳቦች ጭምር አበርክቶልናል፡፡

Read 21541 times