Sunday, 19 February 2017 00:00

ቃለ ህይወት

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(9 votes)

“ሁሉም ነገር ከቃላት ነው የሚጀምረው… It all began with words you know… ቃላትም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበሩ…” ብሎ መድረኩ ላይ ወጥቶ ዲስኩሩን ጀመረ፡፡ ታዳሚው በአንድ ላይ አጨበጨበ፡፡ ሳሪ ጥሞናውን ሰብስቦ ተናጋሪው ላይ አተኮረ፡፡ ከእሱ በስተቀር ሰው ሁሉ የሚተዋወቅ ይመስላል፡፡ ወደ አዳራሹ ተንጠብጥበው ሳይሆን አንድ ላይ ነው የገቡት፡፡ ታዳሚው ሁሉ ይተዋወቃል። መድረኩ ላይ የሚወጡትም ታዋቂ ናቸው፡፡ ሳሪ መልካቸውን ያውቃቸዋል፡፡ የቃላት አንጥረኞች ናቸው፡፡ መልካቸውን ያውቀዋል፤ ያነጠሩትን ቃላት ነው የማያውቀው፡፡
ዝግጅቱ የመፅሐፍ ምረቃ ነው፡፡ መግዛት ባይፈልግም ጦሙን እንዳይቀመጥ፣ ዲስኩሩ እስኪጀመር ድረስ ሊደበርበት የሚመረቀውን መፅሐፍ ገዝቶታል፡፡ ምንም ነገር እንደማያገኝበት ያውቃል፡፡ የጥበብ ቅዱሳን ስራዎች መልሰው በተመሳሳይ ቅርፅ የተደገሙበት ነው የሚሆነው። ያውቀዋል፤ ግን እንደው ማቀርቀሪያ ለማግኘት ያህል ትንሽ አገላበጠው፡፡ ያው፤“ እየሱስ የግጥም ጌታ ነው” ይላል፤ከአርዕስቱ ስር ያለው መፈክር፡፡ መፈክሩን መጀመሪያ… አርዕስቱን ቀጥሎ አነበበው። አነበበው ግን አልያዘውም… ያው ተመሳሳይ ስለሆነ እያነበበ ሳለ ረሳው፡፡
..ሀይማኖት ትርጉም እንደሌለው ካወቀ ቆይቷል። ሶስቱም ሀይማኖቶች ችግር አለባቸው፡፡ የገንዘብ ሀይማኖት፣ አግበስባሽ… አልጠግብ ባይ ያደርጋል፡፡ አይቶታል፡፡ እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ ሁለተኛው የጉልበት ሀይማኖት ነው፡፡… ጉልበተኛ ስላልሆነ፤ በሀይማኖቱ ቃል ወደ ተገባው ፅድቅ ላይ መድረስ አቃተው፡፡ …አሁን የቀረው የጥበብ ሀይማኖት ብቻ ቢሆንም፤ እሱም ከሀሳቡ ጋር አልገጠመለትም።… ነፍሱን የሚነካ ቅኔ አላገኘም፡፡ ሀይማኖቱም ታገኛለህ አይልም፡፡
…ሃይማኖቱ በቅዱስ መፅሐፍቱ እንደሚገልፀው፤ …ሰው ከጥበብ ገነት የፈጣሪውን ቃል ተላልፎ ከተጣለ በኋላ… ጥበብን መልሶ ለማግኘት ያደረጋቸው ልፋቶች የሚቋጩት ከመሲሁ መምጣት በኋላ ነው፤ይላል፡፡ የጥበብ ፈጣሪ፣ልጁን ልኮ በሰው ልጆች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥበብ ለወደቀው የፍጡራን ነፍስ ሰጣቸው፡፡ በቃላትና በግጥም ተደርገው የማይታወቁ ተአምራቶች ታዩ፡፡ በግጥም ሰዎች ከሙታን ሲነሱ፣ የታመሙ ሲፈወሱ… ነፍሳቸውን ከስጋቸው ማስጣል ያልቻሉ… ነፃ ሲወጡ ታዩ፡፡
…ከጥበብ ሰማይ የመጣው ፈጣሪ በገንዘብ ሀይማኖተኞች ተከሶ… በጉልበተኞቹ ተይዞ ተሰቀለ። ተሰቅሎም ይገጥም ነበር፡፡ ግጥሞቹ ሁሉ ተአምር መስራት የሚችሉ ናቸው፡፡ የፈጣሪ ልጅ ሲሞት ወደ መጣበት የጥበብ ሰማይ እንደሚያርግ እና… ነፍሳቸውን ከቅኔ አርቀው የቀበሩትን… ቃሉን ችላ ያሉትን በድጋሚ ተመልሶ ሲመጣ እንደሚቀጣ ተናግሯል፡፡
…ተመልሶ የሚመጣበት ጊዜ አይታወቅም፡፡ ግን መምጣቱ አይቀርም… ይላል ሐይማኖቱ፡፡
ይኼንኑ ታሪክ እየደጋገሙ የጥበብ ሀይማኖተኞች ይቀኙታል፡፡ ቅኔውን ቃለ-ህይወት ብለው ይጠሩታል፡፡ …እምነት ካላችሁ በግጥም ይሄን ተራራ ተነቅለህ ጥፋ ብትሉት ይታዘዛችኋል… ይላል እምነታቸው፡፡ ግን አንድም ገጣሚ ተአምር ሲያከናውን ሳሪ አይቶ አያውቅም፡፡
የጥበብ ሀይማኖት ስሜትን እንጂ አእምሮን አይወድም፡፡
ሳሪ የፈጣሪ ልጅ በፃፈው ቅኔ ተማርኮ ነው ወደ ሐይማኖቱ የመጣው፡፡ የሐይማኖቱ ተከታዮች ግን አሰለቹት፡፡ አንድ አይነት ግጥም ከመደጋገም በስተቀር ተአምር መስራት አይችሉም፡፡
…እምነት የላቸውም፤ብሎ አሰበ፤ግጥሞቹን እያገላበጠ፡፡ እሱም እምነቱ ያጠራጥረዋል፡፡ የፈጣሪን ቅኔዎች በተፈጥሮ ላይ ሲያነብ ይደነቃል፡፡ የፈጣሪን ልጅ ቃላት በግጥሙ ዜማ አወራረድ ሲያንጎራጉር፣ ነፍሱ በታላቅ ከፍታ ላይ ትንሳፈፋለች፡፡
ግን እንደ ጥንቱ ዘመን አማኞች፣ ግጥሙን እየደገመ በሽተኞችን ይቅርና የራሱን በሽታ እንኳን ማከም አልቻለም፡፡ እምነት ነው የሚጎለው፤ልክ እንደሌሎቹ፡፡ የጥበብ ሀይማኖት አማኞች እንደ ገንዘብ ሀያማኖት አማኞች፣ ለእምታቸው ጠንካራ አይደሉም፡፡ ወይንም እንደ ጉልበት አማኞች ለግጥም እምነት ጉልበቴን አላጥፍም አይሉም። ወደ ጥበብ ሐይማኖት የሚሳቡት ለጉልበት ወይ ለገንዘብ ብለው ነው፡፡ … ጉልበትን ወይንም ገንዘብን እያመንክ፣ ለጥበብ እምነት ሙሉ አቅምህን ልትሰጥ አትችልም… ብሏል የተሰቀለው ገጣሚ፡፡
ሳሪ ወደ መድረኩ ተመለከተ፡፡ መድረኩ ላይ የወጣው አዛውንት ሰውዬ፤ ከኪሱ አንድ ረጅም ወረቀት እንዴት እንዳወጣ ገረመው፡፡ የወረቀቱ አወጣጥ ተአምር ሆነበት፡፡ ካወጣው ወረቀት ላይ አንገቱን ወደ አንድ ጎን አዝምሞ… ያነበበው ግጥም ግን ምንም ተአምር የለውም፡፡ እንዲኖረውም አይጠብቅም፡፡ ከኪሱ ወረቀቷን እንደፈጠረው ያህል እንኳን አስማት፣ ያነበባቸው ቃላት ቢኖራቸው ኖሮ…  ብሎ ሳሪ ተቆጨ፡፡
ከእሱ በስተቀር ሌላው ታዳሚ በጭብጨባ አዳራሹን ሊያፈርስው ነበር፡፡ ነፍሱ እንጂ ጆሮው በህልውና አለ፡፡ ቢያንስ ጭብጨባ ይሰማል። ግጥሞቹ ምክር ይበዛቸዋል፡፡ ሰውየው አራት ግጥም አነበበ፡፡ ግጥሞቹ አጭር ይሁኑ ረጅም የሚያውቀው በጭብጨባ የሚረበሽበትን ቅፅበት ቀረብ ወይንም ራቅ ማለት ገምቶ ነው፡፡ አርዕስቶቹ አንዳንዴ የግጥሙን ያህል ይረዝማሉ፡፡ የአርዕስቱ ማብራሪያ እና የአናት ማስታወሻ ሲጨመር ግጥሙ የሚጀምርበት ቅያስ የትኛው ጋ እንደሆነ ግር ይላል፡፡
…ግጥሙ ሳይጀመር ነበር ለካ የተጨበጨበው… አራት የመሰለው ግጥም ያው የመጀመሪያው ነው፡፡ …እሺ ተዓምር ይለቅበት… እምነት ይጣ… ግን ቢያንስ እንዴት አጣፍጦ፣ልብ ሰቅሎ ግጥም መስበክ ያቅተዋል… እያለ ያስባል፡፡ ጭብጨባ ይቀሰቅሰዋል፡፡ እጆቻቸውን እያጣሉ ሳይሆን እርስ በራሳቸው በጥፊ እየተጠፋጠፉ የሚያወጡት ድምፅ ይመስላል፡፡ መላጣውን በጥፊ ሊሉት መስሎት ተሸማቀቀ፡፡ የሚያጨበጭብ በድንጋይ ይወገራል የሚል ህግ በቅዱስ መፅሐፉ ላይ ባይኖርም… ቀስ ብለው ሳይደነግጉት እንደማይቀር ጠረጠረ፡፡… አብሯቸው ማጨብጨብ ጀመረ፡፡ ጭብጨባው ዘግይቶ የሚጀምር እና የሚቆም መሆኑ ግልምጫ አስከትሎበታል፡፡ በመከራ ወረደ ገጣሚው፡፡ ተራ ሰባኪ ግጥሙን አንብቦ ካልጨረሰ የፈጣሪ ልጅ አይመጣም ብለው ያስባሉ፡፡… ፈጣሪን መጠበቅ አይደለም የሚያሰለቸው… የሐይማኖተኞችን የውሸት ግጥም እያደመጡ መቆየት ነው ስቃዩ፡፡
…አንድ ነገር ሲደጋገም መደንዘዝ እንደሚጀመር …ሂፕኖቲዝም… ማለት በአጭር ዙር ጊዜ ውስጥ አንድ ነገር ሲደገም የሚፈጠር የመደንዘዝ ስሜት እንደሆነ ከተሞክሮ ተምሯል፡፡ ይኼንን ያስተማሩት የገንዘብ ሐይማኖተኞቹ ነበሩ፡፡ ለገንዘብ ሀይማኖተኞቹ ሁሉም ነገር ፈጣን ነው… ፈጥነው ይንቀሳቀሳሉ… እንቅስቃሴያቸው አይደገምም፤ ሁሌ ወደፊት የሚያድግ ነው፡፡… ግን አድጎ አድጎ ቅልጥፍናውን ወደ ዝሆንነት ይቀይረውና… ጉልበተኞች አይን ውስጥ ይገባሉ፡፡ ጉልበተኞቹ ወፍረው ሲታዩዋቸው መጥተው ይደፈጥጧቸዋል፡፡
…የትኛው ይሻላል? ብሎ ራሱን ሲጠይቅ… እሳት የተቀጣጠለበት የፎቅ ቤት ውስጥ ያለ መሰለው፡፡ እዚህ ቢቆይ ግጥሙ እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ አፍኖ ይገለዋል፡፡ በፎቁ ቢዘልም ተሰባብሮ ይሞታል፡፡ ማን ወደ ጉባኤው ና አለኝ? …እያለ እየታፈነ… እየፈዘዘ ሙሉ በሙሉ ከመደንዘዙ በፊት ጭብጨባው መልሶ አነቃው፡፡ መንቃት ደስ አይልም፡፡ ሰው በእርጥብ ፎጣ ፊቱ ላይ ተገርፎ እንዴት ይነቃል፡፡ ብቻ ነቃ፡፡
ሌላ ቀልጠፍ ያለ ወጣት መድረኩን ተቆጣጠረው፡፡ ታዳሚው ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲያጨበጭብለት ተስፋ አደረበት፡፡ …የመፅሐፍ ምረቃው ምክንያት የሆነው ደራሲ ከሆነ፣ ጉባኤውን ረግጦ ለመውጣት አሰበ፡፡ ጉባኤ ጥሎ የወጣ አማኝ ደግሞ በጥበብ ካድሬዎች ይጠቆራል፡፡ ሐይማኖትን መናቅ በሚል ተወንጅሎ፣ከማህበረሰብ ጥበባት ተቋም የሚቆረጥለትን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ድጎማ ሊነጠቅ ይችላል፡፡
 …ከሶስቱ ሐይማኖቶች ውጭ ሌላ አራተኛ ሐይማኖት ቢኖር እሞክር ነበር… እያለ እያሰበ… ከጎኑ የተቀመጠውን… የዘነጠ ሽማግሌ ቀስ ብሎ… መድረኩ ላይ የወጣው ገጣሚ ማነው ብሎ ለመጠየቅ ፈለገ..፡፡ ግን ሰውየን ተጠራጠረው፤ የሆነ የጥበብ ካድሬ ነገር ይመስላል፡፡… በፊደል የተሰራ ልብስ ነው የለበሰው፡፡ ሳሪ የሰውየው አኳሃን አልጣመውም፡፡ “ፀጋዬ ቤት” ተብሎ በሚጠራው የጥበብ ባለስልጣናት መኖሪያ የሚኖሩት ናቸው ፊደል መልበስ የሚያበዙት፡፡
ከመፍዘዝ ግን መጠየቅ እንደሚሻለው ቆርጦ… ጭብጨባው ሳይቋረጥ ሾልኮ መውጣት እንዲችል በቀስታ የሰውየውን ክንድ ገጨት አደረገው፡፡ ጭብጨባውን ሳያቋርጥ ያንኛው ጆሮውን ወደ ሳሪ ዘንበል አደረገ፡፡ ሳሪ የገጣሚውን ስም ጠየቀው፡፡
የጥበብ ሐዋሪያቱን ስም የረሳ ይመስል አጉረጠረጠበት፡፡ የተሰቀለው የግጥም ጌታ መቼም ተመልሶ መጥቶ አይሆንም፡፡ እስኪመጣ ደግሞ ምንም ተአምር አይኖርም፡፡ …መድረክ ላይ የቆመው ሰባኪ ባይታወቅ የሚያስቀጣ አይደለም… እያለ ሳሪ መረጋጋት ሞከረ፡፡ ካድሬው  አጉረጥርጦ እስኪጨርስ እያጨበጨበ ጠበቀ፡፡
“ተአምር የሚፈፅመውን ገጣሚ አታውቀውምን?” አለው የጥበብ ካድሬው፡፡
“አላውቀውም”
“እንዴት አታውቀውም፤በሀገር የለህም እንዴ?”
“አይ፤ለሐይማኖቱ አዲስ ነኝ”
“እፍነ… ይባላል… አሁን የጠፋውን ተአምር እና እምነት ወደ ግጥማዊያን እየመለሰ ያለ ነብያችን ነው፡፡”
… ድንገት ሳሪ ትዝ አለው፤የገጣሚው ስም… ስሙ ሳይሆን ስም አወጣጡ፡፡ “እየሱስ ፍቅር ነው” የሚለውን ጥቅስ አሳጥሮ፣ በምህፃረ ቃል ለራሱ ስም ስለማውጣቱ አንድ ጊዜ ሲፎከርለት ሰምቶዋል፡፡ አሁን በደንብ ነቃ፡፡ ነፍሱም አብራው ነቃች፡፡ ነፍስ ስትነቃ ሁሉም ነገሯ ክፍት ነው የሚሆነው፡፡ እንደ ንብ አምስት ሺ አይን ታወጣለች፡፡ ባወጣችው አይንና ጆሮ ልክ የሚሞላት ነገር ካላገኘች ግን ተመልሳ ወደ ዋሻዋ እንደ ሸረሪት ገብታ ትደበቃለች፡፡ አንዴ ካፈገፈገች በቀላሉ ተመልሶ መውጣት አትችልም፡፡
እንደ ሐይማኖቱ ታሪክ፤ በጥንት ዘመን፤…ልብም… አይንም ከውጭ ነበሩ፡፡ ያኔ ግጥም ተአምር በሚሰራበት ዘመን፣ነፍስ ከሰው ግጥም ለመዋስ ወይ ለማዋስ… ውጭ ነበር የምታድረው፡፡ በሯን መለስ አድርጋ እንደወጣች፣እንደ ፊኛ ስትንሳፈፍ ትውል ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር ታምን ስለነበር ምንም ነገር አያስፈራትም ነበር፡፡ አሁንም እንደ ድሮው ቀፎዋን ዘግታ እንድትወጣ የሚያደርጋትም ነው የምትፈልገው። ከስጋ ምሽጓ… ከፍርሐቷ…፡፡
ቃላት እንደዛ የማድረግ አቅም አላቸው ይባላል፡፡… የሳሪ ነፍስ በዛች ቅጽበት አዳራሹን ጥላ ጭልጥ አለች፡፡
… ቃላቱ በእኛ ጆሮ ላይ ድንጋይ፣ በፀሐፊዎቹ እጅ ላይ ደግሞ እባብ ሆኑ…
… እየፈሩ የሚያምኑት ቃል በጥንቃቄ ስለሚፃፍ ከወፍነት… ወዳስፈለገው ነፃነት ከመብረር ይልቅ ጥርሱን በብልቃጥ ጠርዝ ላይ ተጭኖ መርዝ እንደሚተፋ እባብ ይሆናል፡፡ መርዙ መድሀኒት ይሆናል፡፡ በጥንቃቄ… በእውቀት… እና በምክንያታዊነት ከተቀመረ… ይላሉ፡፡
… መድሐኒት ተአምር አይደለም፤አስማት ነው፡፡ …መርዝ ለበሽታ መድሀኒት ሊሆን ይችላል፡፡ ተራራን ከተተከለበት አንስቶ ወደ ማዶ የሚወረውር ተአምር ሊሆን ግን አይችልም፡፡…
…ተአምር እየተመናመነ መጥቶ ከእነአካቴው ጠፍቷል፡፡… በድሮ ዘመን ማንም ተራ ሰው፣ ፀሐይን በግጥም ወይ በዋሽንት ማቆም ይችል ነበር፡፡… እርግጥ ፀሐይዋን አቆማት ወይንስ የዋሽንቱን ዜማ ለመስማት ስትል ራሷ ቆመች?... አከራካሪ ነው፡…
…ድሮ ሁሉም ገጣሚ ስለነበር… ሁሉም ባለቅኔ ደግሞ ተአምርን ማከናወን ይችል ስለነበር… ተአምር ተራ ነገር ነበር፡፡ ተአምራት እየተመናመኑ ሲመጡ… ጥቂት የቀሩ ቅዱሳን ተደርገው ተቆጠሩ፡፡ ሁሉም የሰው ልጅ ራሱን እንደ ፍጹም ስለሚቆጥር፣ስለ ገነት ምንነት የተለየ እውቀት አልነበረውም፡፡….ተአምራት እተመናመኑ ሲመጡ የመሬት ስበት ነፍሶችን መጎተት ጀመረ፡፡ አካላት ከነፍስ በላይ ከበዱ… ተአምራት መመናመን ሲጀምሩ ነው ከገነት መባረሩን የሰው ዘር ያወቀው፡፡ ሁሉም ሰው ፈጣሪ… ሁሉም ሰው ባለቅኔ ከነበረበት ስፍራ መውጣቱን ሲያውቅ ጥቂት ሰዎች ብቻ የተአምር አቅም እንዳላቸው በዛው ሂደት ገባው። ተአምር የሚሰሩትን ከፈጣሪ ጋር አንድ ላይ ይኖር የነበረበትን ስፍራ ርቀት ማነጻጸሪያ አደረጋቸው… ቅዱሳን ብሎ ጠራቸው፡፡
… አሁን ያለበትን በፊት ከነበረበት ጋር ማገናኛ ገመድ ሆኑለት፡፡
…ሰው፤ ከገነት በአንድ ቀን አልተባረረም፡፡  በዝግመተ ለውጥ ሂደት ነው የወረደው፡፡ መውረዱ አንድ ወለል ላይ ደርሶ አልቆመም… መውረድ ቀጥሏል።… መውረድ ሲቀጥል ተአምራት እየተመናመኑ ብቻ ሳይሆን እየጠፉ መጡ፡፡ ከመጥፋታቸው በፊት የተወለደው የመጨረሻው ተአምረኛ.. የመጨረሻው ባለቅኔ፣ ከሁለት ሺ አመት በፊት በመስቀል ላይ ገደሉት፡፡…
…ሙውረዱ ሲቀጥል ከጥበብ ሰማይ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመወጣጫው መሰላል ጋር ራሱ መነካካት ይቀራል፡፡ መሰላሉም ከሰማዩ ይርቃል፡፡…
…ይህ የላይኛው ግዛት ነው፡፡
 መውረዱ ሲቀጥል ከታችው ግዛት መውረጃ መሰላል ጋር ወደ መነካካት ይቀርባል፡፡ ይቀርብና ያነካካል፡፡ ወደ ጥልቁ ጉድጓድ እና አዘቅቱ ሲኦል መድረሻው መሰላል ጋር ይጨባበጣል፡፡…
ይኼም መሰላል ገጣሚዎች አሉት። ተአምረኞች ይኖሩታል፤ ወደ አዘቅቱ የሚጥሉ እኩይ ቅዱሳንም         እንደዚሁ።                                                                                                                                                                                                                                      
 አዎ! ገጣሚዎች አሉት፡፡ ግጥማቸው ቅኔ ሳይሆን የድግምት ቃና ይኖረዋል፡፡
 በድግምትም ተአምር ይፈጠራል፡፡
 ተአምሩ ግን ፀሐይ ቆማ የምትሰማው አይነቱ ሳይሆን ላለመስማት ጆሮዋን ደፍና ለመሸሽ ስትል ገደል የምትወድቅበት አይነት ነው፡፡
***
ወጣቱ ገጣሚ መድረኩ ላይ ከወጣ በኋላ ጭብጨባውን… በግጥሙ አርዕስት በድንገት ቀጥ አደረገው፡፡ አርዕስቱ ራሱ የተአምር ባህርይ አለው፡፡ ግን ደስ የማይል ኃይል ከተአምሩ ጋር ተያይዞ አዳራሹን እንደ ቅዠት ዞረው፡፡ ወጣቱ ያነበበው አንድ ግጥም ብቻ ነበር፡፡ ግጥሟም ባለ ሁለት መስመር ናት፡፡ ሳሪ ግን ሁለት አመት የሚያክል እሾክ ነፍሱ ላይ ሁለት መቶ ዙር ሲጠቀለል ተሰማው፡፡
ብዙው ታዳሚ በስንኙ አየር ላይ መንሳፈፍ ጀምሯል ግን የሚንሳፈፈው ጉሮሮው ላይ ገመድ ታስሮ ነው የሚመስለው፤ይንፈራገጣል፡፡ … ወደ መድረክ ቀረብ ያለው መቀመጫ ላይ የተቀመጡት ታዳሚዎች… የጥንቱ የአውሬ ዘመን ፁጉራቸው፣በልብሶቻቸው እንደ ጃርት እሾክ በስቶ እየወጣ ነበር፡፡ መድረኩ ላይ ቆመው የነበሩ… ግጥም ለማንበብ ተራቸውን የሚጠብቁ ጥበበኞች ድንገት እንደ ፈንዲሻ ጧ - ጧ ብለው ፈነዱ።…
ባለ ሁለት መስመር ግጥም ቢሆንም… ሳሪ ተአምር አይቶአል፡፡ ግን ተአምሩ ጥቁር አዘቅት ነው፡፡ የሲዖል ተአምር ነው፡፡ ቃለ- ሞት ሆኖ እየገደለው ስለነበር የግጥሙን ውበት ሊያጣጥመው አልቻለም፡፡

Read 5168 times