Sunday, 19 February 2017 00:00

እንጉዳይ ወደ ውጭ ለመላክ የምታልም ወጣት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(16 votes)

 “የስኬቴ ምክንያት እልኸኛ መሆኔ
                   
        ዛሬ፣ እንጀራዋ፣ ክብሯና ሽልማቷ ሊሆን፣ ከሰባት ዓመት በፊት የእርሻ ትምህርት እንድትማር ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ስትመደብ፣ ሕክምና (ሜዲስን) ወይም ኢንጂነሪንግ ካልሆነ በስተቀር እንዴት እርሻ እማራለሁ? እዚሁ ኮሌጅ ገብቼ ሌላ ነገር እማራለሁ እንጂ አልሄድም” በማለት አልቅሳና አስቸግራ ነበር፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲው የሄደችው በአባቷ ግፊት ነው። አባቷ፣ ‹‹ከኮሌጅ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ ነው መመረቅ ያለብሽ” በማለት ኮስተር አለባት፡፡ እሷም አባቷን በጣም ስለምትወደው እሱን ላለማስቀየም፣ “እንደምንም ብዬ ገንዘብ እንኳ የሚያስከፍል ቢሆን ከፍዬ፣ ከሌሎች ልጆች ጋር እቀያየራለሁ” በማለት ሄደች፡፡ በተለያዩ መንገዶች ብትሞክርም ቅያሬው ሊሳካ አልቻለም፡፡ ትምህርት ሲጀመር እንኳ “እቀይራለሁ” የሚለው ስሜቷ እንደጋለ ነበር፡፡
“እቀይራለሁ” የሚለው ፍላጎቷ ሳይቀንስ አንደኛ ሴሚስተር አልቆ ሁለተኛ ተጀመረ፡፡ በዚህም ሴሚስተር የፍላጎቷ ሳይፈጸም፣ የአንደኛው ዓመት ትምህርት አልቆ ዩኒቨርሲቲው ለእረፍት ተዘጋ። በሁለተኛው ዓመት “የሚቀይረኝ ካገኘሁ፣ የአንድ ዓመቱን ትምህርት ምንም እንዳልተማርኩ ቆጥሬ እንደ አዲስ ገቢ እጀምራለሁ” የሚል ስሜት ይዛ ትምህርት ጀመረች፡፡ በዚያ ዓመት ከተሰጡ ትምህርቶች አንዱ ስለ እንጉዳይ ነበር፡፡ ወደደችው። “እቀይራለሁ” የሚለውን ሀሳቧን ትታ፣ ከልብ ትከታተለው ገባች፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ሲመረቁ የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፍ ይሰራል፡፡ ቃልኪዳን ስለሺ የመመረቂያ ጽሑፏን የመሽሩም ዘር አመራረት (Mushroom Spawn Production) በሚል ርዕስ እንጉዳይ ላይ ሠራች፡፡
ቃልኪዳን በ2005 ዓ.ም ስትመረቅ፣ ተቀጥሮ የመስራት ሀሳብ አልነበራትም፡፡ ነገር ግን ተመቻችቶላት የራሷን ሥራ እስከምትጀምር “ከመቀመጥ” ብላ ያለ ሙያዋ ሥራ ብትጀምርም አልገፋችበትም - አቋረጠችው። ቀድሞውንም ሀሳቧ የራሷን ስራ መጀመር ነውና ስሌው (የአባቷ ስም ነው) መሽሩም ፕሮዳክሽን የሚል ድርጅት አቋቁማ፣ እንጉዳይ ማምረት ጀመረች፡፡ ነገር ግን አልቀጠለችበትም፡፡ ምክንያቱም የእንጉዳዩ ዘር ጥራት ስላልነበረው ስኬታማ አልሆነችም፡፡ “ምርጥ ዘር እስካገኝ ድረስ አልሰራም” ብላ ምርቱን ተወችው፡፡
በዓለም ታዋቂና ተወዳጅ የሆነው እንጉዳይ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሁለት አሠርት ዓመት እንኳ ዕድሜ የለውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዘሩ በአገር ውስጥ ስለማይመረት ነው፡፡ ጥቂት እንጉዳይ አምራች ድርጅቶች ብቅ ብቅ ቢሉም፣ በወረት የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ሆኖ ይቀራል፡፡ በተለይ የሚያመርቱትና ገበያ ላይ ያለው ዘር ጥራት የሌለው ለመሆኑ ትምህርቷና መመረቂያ ወረቀቷን የሰራችበት በመሆኑ ቃልኪዳን በሚገባ ታውቃለች “ጥራት ያለው ዘር ለማምረት ዘመናዊ መሳሪያ ያስፈልጋል። መሳሪያዎቹ ደግሞ ውድ ናቸው፡፡ በእኔ አቅም የሚሞከር አይደለም” ትላለች፤ ቃልኪዳን፡፡
በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት (ቻምበርስ ኦፍ ኮሜርስ) ‹‹በእርሻ ተመርቃችሁ፣ ፕሮጀክት ያላችሁ ተወዳደሩ›› የሚል ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ቃል ኪዳን የውድድሩን መስፈርት ታሟላለች። ተወዳደረችና ለሽልማት ከተመረጡ አምስት ሰዎች አንዷ ሆና 75 ሺህ ብር ተሸለመች፡፡ ገንዘቡ ግን ዘር ማምረቻ መሳሪያ መግዣ በቂ አልነበረም፡፡ ሸላሚው አካል አሸናፊ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ይፈልጋል። ስለዚህ ቃልኪዳንም “ወደ ተግባር ግቢ” ተባለች። አንዴ ገብታበታለችና ወደ ኋላ ማለት አልቻለችም። የተሸለመችው ገንዘብ ደግሞ ለመሳሪያ መግዣ አይበቃም። ስለዚህ ሌላ የሚያሸልም ውድድር ማፈላለግ ጀመረች፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ቻምበርስ ኦፍ ኮመርስ፣ ለከባቢ አየር (ክላይሜት) የሚጠቅም ፕሮጀክት ያላቸው እንዲወዳደሩ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ የቃልኪዳን እንጉዳይ ደግሞ ለክላይሜት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ለእንጉዳይ ምርት የሚጠቀሙበት የግብርና ተረፈ ምርት ከጫካ የሚገኝ ተረፈ ምርት፣ የሚጣሉ ነገሮች፣ ቀቅለው ነው የሚያመርቱት። እንጉዳይ የተመረተበት ተረፈ ምርት ደግሞ አይጣልም፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለሚሰሩ ድርጅቶች በጥሬ ዕቃነት ያገለግላል፡፡ በውድድሩ የተሳተፉ ትላልቅ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ቃልኪዳን፤ “የእኔ ፕሮጀክት ያሸንፋል” የሚል ግምት ባይኖራትም ከተመረጡ ፕሮጀክቶች አንዱ የእሷ ሆኖ 33 ሺህ ዶላር ተሸለመች፡፡ ሁለቱን የሽልማት ገንዘብ አቀናጅታ የእንጉዳይ ዘር ማምረቻ በ600 ሺህ ብር ገዝታ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታ፣ የማምረቻ ቦታ እንደተሰጣት በ2007 ዓ.ም ወደ ሥራ እንደገባች ተናግራለች፡፡
በዓለም ላይ ብዙ ሺህ የእንጉዳይ ዝርያዎች ቢኖሩም የታወቁት ሦስት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ኦይስተር፣ ቤተንና ሽታጊ የተባሉ ዝርያዎች በዓለም ላይ በከፍተኛ መጠን ይመረታሉ። ሦስቱም ታዲያ የየራሳቸው የአመራረት ዘዴ እንዳላቸው ባለሙያዋ ገልጻለች፡፡
በኢትጵዮያ ያለውን ኦይስተር የተባለ የእንጉዳይ ዘር ለማምረት በአካባቢ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል የግብርና ተረፈ ምርቶች፣ ጭድ፣ ገለባ፣ የጥጥ ፍሬ፣ ከጀርም፣ ከባክቴሪያ፣ ከተለያዩ ተህዋሲያን ነፃ ካልሆኑ በሽታን ተቋቁመው ማደግ አይችሉም፤ ስለዚህ ይቀቀላሉ፡፡ ተረፈ ምርቶቹ ከተቀቀሉ በኋላ የእንጉዳዩ ዘር ምግብ ሊሆነው ከሚችል ከጭድ ከገለባው፣ ከጥጥ ፍሬው ወይም ከሦቱስም ድብልቅ ጋር ይለወስና ወደ ጨለማ ክፍል ይገባል፡፡ በዚህ ክፍል ከ21-30 ቀን  ውሃ ሳይጨመርበት፣ ብርሃን ሳያገኘው ይቆያል፡፡ 25 ዲግሪ ሰልሸስ የሚደርስ ሙቀት ግን ይፈልጋል፡፡ ከ21 ቀን በኋላ በሻጋታ መሸፈን ሲጀምር፣ ወደ ብርሃን ክፍል ይገባል፡፡ እዚህ ክፍል በገባ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንጉዳዩ ማደግ ይጀምራል፡፡ ምርቱ ከ3-4 ጊዜ ከተቆረጠ በኋላ ተረፈ ምርቱ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ አምራቾች ይሸጣል፡፡
እነ ቃል ኪዳን የእንጉዳይ ዘር እንጂ እንጉዳይ አያመርቱም፡፡ ነገር ግን የእንጉዳዩን ዘር ለሸጡላቸው አምራቾች በ200 ብር ስለእንጉዳይ አመራረት ዘዴ የአንድ ቀን ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ የሚከፈለው ዋጋ ለሥልጠናው ብቻ ሳይሆን አምራቾቹ ዘሩን ገዝተው ማሳደግ ከጀመሩ በኋላ ባለሙያዎች እየሄዱ የሚያደርጉትን ክትትልና ምክር ይጨምራል፡፡ እነ ቃልኪዳን እንጉዳይ ባያመርቱም ያሠለጠኗቸው ደንበኞቻቸው ያመረቱትን ይገዟቸውና ለትላልቅ ሆቴሎችና ሱፐር ማርኬቶች ይሸጣሉ፡፡ አምራቾቹ ገበያ ካገኙ ራሳቸውም መሸጥ ይችላሉ፡፡
ለሥልጠና ወደ “ስሌው ምሽሩም ፕሮዳክሽን” የሚመጡ ሰዎች ከአሁን በፊት እንጉዳይ ምርት ጀምረው ሳይሳካላቸው የቀሩ ናቸው፡፡ ‹‹ማንኛውንም ነገር ለመሥራት እውቀት ያስፈልጋል፡፡ የእንጉዳይ ምርት ደግሞ ከምንም የበለጠ እውቀት ያስፈልገዋል። ምርት ከጀመሩ በኋላ ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተው ከተውት በኋላ፣ እኛ ጋ የሚመጡ ሰዎች ቀድሞውኑ ያለ እውቀት ስለጀመሩት ነው፡፡ እኛ የምንሰጠው ስልጠና የአንድ ቀን ቢሆንም በዚያ ብቻ አንተዋቸውም። ምርት ሲጀምሩ እየሄድን እንዴት ነው? ምን ችግር ገጠማችሁ? እንዲህ ብታደርጉ የበለጠ ጥሩ ነው… በማለት ክትትል እንክብካቤ እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ውጤታማ ይሆናሉ።›› ብላለች፡፡
እንጉዳይ በፕሮቲን፣ ሚኒራሎችና ማዕድናት የበለፀገ ስለሆነ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የገለጸችው ቃል ኪዳን ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ እንደሆነም ተናግራለች፡፡ ስኳር፣ ለደም ብዛት፣ ልብ ድካም፣ ኮሎስትሮል፣ ካንሰር…ለመከላከልና ባለበት እንዲቆይ ለማድረግ እንጉዳይ ፍቱን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ጥቅሙን እየተረዱ እንደሆነ የጠቀሰችው ባለሙያዋ፤ ‹‹ድሮ ደንበኞቻችን ዳያስፓራዎችና የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያንም ደንበኞቻችን እየሆኑ ነው›› ብላለች፡፡
ይህን ሥራ ከጀመረች በኋላ ብዙ ሽልማቶችና ዋንጫ ተሸልማለች፡፡ ካፒታሏም በአሁኑ ሰዓት ከ 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
ቃል ኪዳን ይህን ሥራ ስታከናውን ብዙ ችግሮች እንደገጠማት ትናገራለች፡፡ አንደኛው ችግር የሕዝቡ ስለ እንጉዳይ ያለማወቅ ነው፡፡ ስለ እንጉዳይ ስታስረዳ፤ ‹‹ይኼ ይበላል?›› ይሏታል፡፡ “ስለ እንጉዳይ ምንነትና ጠቃሚነት ማስተማር የመንግስት ስራ አይደለም፤ ህብረተሰቡን ማስተማር የጋዜጠኞች ሥራ ነው።” ትላለች፡፡ ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ዘርፍ መሆኑን ገልጻለች፡፡ የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለእንጉዳይ ምርት በጣም ጥሩ ነው፡፡ እኛ ግን እንጉዳይ የምናስገባው፣ ለእንጉዳይ ምርት ጥሩ የአየር ንብረት ከሌላትና በልዩ ቴክኖሎጂ ከተመረተባት ዱባይ ነው፡፡ ይኼ ለምን ይሆናል? የእኛ አፈር ለእንጉዳይ ምርት ተስማሚ ነው። ለምንድነው ለእንጉዳይ ምቹ አፈር ከሌላት ዱባይ የምናስመጣው? እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ሳስብ ያመኛል›› ትላለች፤ ቃልኪዳን፡፡
ሌላው ዋነኛ ችግር ገንዘብ ነው፡፡ የሽልማቱን ገንዘብ እስክታገኝ ድረስ በገንዘብ እጦት ለሁለት ዓመት ሥራ መፍታቷን ገልጻለች፡፡ የማምረቻ ቦታ እጦትም ሌላው ችግር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥራ በኪራይ ወይም በአነስተኛ የግል ቤት አይሰራም ትላለች፡፡ ይህን ቦታ መንግሥት ባይሰጠኝ ኖሮ፣ በፍፁም ቦታ ተከራይቼ መስራት አልችልም ነበር፡፡ መንግሥት ለዚህ አንገብጋቢ ችግር ምላሽ ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ ብላለች፡፡
ቃል ኪዳን የተወለደችው አዲስ አበባ ውስጥ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ቢሆንም ያደገችው ሳሪስ ነው። አንደኛ ደረጃን እዚያው አካባቢ ባለ ፍሬሕይወት በሚባል ት/ቤት ተምራ፣ ሁለተኛ ደረጃን ቦሌ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ተማረች፡፡ 12ኛ ክፍል ስታልፍ፣ ሀሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በናቹራል ሪሶርስ ማኔጅመንት በዲግሪ ተመረቀች፡፡
የእንጉዳይ ባለሙያም የስኬት ምስጢር ጠንክሮ መስራት እንደሆነ ተናገራለች፡፡ ‹‹በጣም እልኸኛ ነኝ›› ትላለች፡፡ ‹‹አንድ ነገር ለማድረግ ካሰብኩኝ ብዙ እጥራለሁ፣ እሠራለሁ ፣ እለፋለሁ፡፡ ያሰብኩት እስኪሳካ ድረስ ዕረፍት የለኝም፤ ጠንክሮ መሥራት ልዩ ባህሪዬ ነው፡፡ አንድ ነገር ለማድረግ ሳስብ የተለያዩ ማሳኪያ መንገዶችንም አብሬ አስባለሁ፡፡ የስኬቴ ምክንያት እልኸኛ መሆኔ ይመስለኛል›› ብላለች፡፡
የቃልኪዳን የወደፊት ዕቅድ ሰፊ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የእንጉዳይ ዘር ፍላጎት አሟልታ ወደ ውጭ መላክ አንዱ ነው፡፡ ሌላም ዕቅድ አላት፡፡ በአገራችን ከእንጉዳይ ዝርያዎች ከኦይስተር በስተቀር ቤተንና ሽታጊ የተባሉ ዝርያዎች አልተሠራባቸውም፤ ከውጪ ነው የምናስገባው። የእነዚህ ዝርያዎች ተፈላጊነት በሆቴሎችና በሱፐር ማርኬቶች ከፍተኛ ነው፡፡ በአይስተር ላይ የምናተኩረው ሥራው ቀላልና በአጭር ጊዜ ስለሚደርስ ነው፡፡ የሁለቱ ዝርያዎች ሥራ ከባድ ነው፤ ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ወደ ፊት በእነሱ ላይ መሥራት እፈልጋለሁ፤ ኤክስፖርት ማድረግ፣ ብዙ አምራች ማፍራት›› እፈልጋለሁ፡፡ እንጉዳይን በተለያዩ መልኮች፣ ለምሳሌ በማኪያቶ በታሸጉ ምርቶች ሆኖ ሁሉም ሰው በየሱፐርማርኬቱ እንዲያገኘው የእንጉዳይ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ማቋቋም እፈልጋለሁ›› በማለት አስረድታለች፡፡

Read 5798 times