Sunday, 19 February 2017 00:00

የጥንት የጠዋቱ “ኖኪያ 3310” እንደገና ሊመጣ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 • በጥንካሬው ወደር አልተገኘለትም
                      • ከ17 አመታት በኋላ አሁንም ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ቀፎዎች አሉ

      ዓለማችን እጅግ በተራቀቁ ስማርት ፎኖች ከመጥለቅለቋ፣ ተች ስክሪን ሞባይል በልጅ በአዋቂው እጅ ከመግባቱ፣ ሞባይል ከመደዋወያ መሳሪያነት አልፎ እጅግ በርካታ ተግባራትን መፈጸሚያ ወሳኝ ቁስ ከመሆኑ በፊት፣ በቀዳሚነት ወደ ገበያ የገባውና እንደ ብርቅ ይታይ የነበረው፣ በጥንካሬው ዛሬም ድረስ አቻ እንደማይገኝለት የሚነገረው ኖኪያ 3310፤ እንደገና ወደ ገበያ ሊገባ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
    የዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎች ዘመን ጅማሬ ምልክት እንደሆነ የሚነገርለት ፈር-ቀዳጁ ኖኪያ 3310፤ በአለማችን የሞባይል ቀፎዎች ቴክኖሎጂ ታሪክ እጅግ ጠንካራውና ሃይል ቆጣቢው እንደሆነ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፣ የሞባይል ቀፎው ከ17 አመታት በኋላ በቅርቡ እንደገና ወደገበያ ሊገባ መሆኑን ገልጧል፡፡
   የተወሰነ ማሻሻያ ይደረግበታል የተባለው አዲሱ ኖኪያ 3310፣ በዚህ ወር መጨረሻ በሚከናወነው የአለም የሞባይል ኮንግረስ ላይ ለእይታ ይበቃል ያለው ዘገባው፤ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በገበያ ላይ እንደሚውልና የመሸጫ ዋጋው 59 ዩሮ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድቷል፡፡
   ኖኪያ 3310 እ.ኤ.አ በ2000 ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቶ ወደ ገበያ መግባቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ምንም እንኳን ኩባንያው ይህንን የሞባይል ቀፎ ማምረት ካቆመ 12 አመታት ቢቆጠሩም ከ16 አመታት በፊት የተመረቱና አሁንም ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ቀፎዎች እንዳሉ ገልጧል፡፡ ኖኪያ ኩባንያ ከሚታወቅባቸው ስኬታማ የሞባይል ቀፎዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ኖኪያ 3310 ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ በቀረበበት ወቅት በአለም ዙሪያ 126 ሚሊዮን ያህል እንደተሸጠ የተነገረ ሲሆን፣ የተሻሻለው አዲሱ ምርት ከሳምንታት በኋላ ለአውሮፓና ለደቡብ አሜሪካ አገራት ገበያ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡ ኩባንያው “ኖኪያ 215”ን የመሳሰሉ የቀድሞ ተወዳጅ የሞባይል ቀፎዎቹን
እንደገና አሻሽሎ በማምረት የገበያ ድርሻውን የማስፋት ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ዘገባው አብራርቷል፡፡

Read 2981 times