Saturday, 17 March 2012 10:29

“እኔን ያላሳቀኝ ሌላውን አያስቅም” ማለት ስህተት ነው!!

Written by  መቅደስ ሃይሉ
Rate this item
(0 votes)

አንጋፋውና ታዋቂው ደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ካለፈ በኋላ የተለያዩ ፀሐፍት በተለያዩ ሚዲያዎች በስራዎቹ እና በህይወቱ ዙሪያ ሲጽፉና ሲናገሩ ሰንብተዋል።እኔም ብዕሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ «መፈንቅለ ስብሀት» በሚል ርዕስ “መፈንቅለ ሴቶች” የተሰኘው ፊልም ላይ የቀረበው አስተያየት ነው፡፡ ፀሐፊው አስተያየት መስጠታቸው ክፉ ባይሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ “ፊልሙን አትዩት” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከራቸውን ግን አልወደድኩትም። የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ድክ ድክ እያለ “ወፌ ቆመች” እየተባለ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ጥበቡ እና ተጠባቢያኑ ላይ የእውር ጦር መወርወር ለማንም ይበጃል ብዬ አላስብም፡፡

ጸሐፊው ተመልካች፤ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል “ፊልሙ አላሳቀኝም”፤ “ታሪኩ ተረት ተረት ነው”. . .ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል። መቼም የሰው ልጅ እንደ ንቃተ ህሊናው ደረጃ የሚያስደስተው እና የሚያሳዝነው ነገር ይለያያል። እኔን ያላሳቀኝ ነገር ሌላውንም አያስቅም ማለት ስህተት ነው። ለአንዱ የተመቸው ታሪክ  ሌላውን ላይመቸው ይችላል። እኔ ፊልሙን ከጅማሬው እስከፍጻሜው ተመልክቼ፣ ስቄበትና ተዝናንቼበት ከመውጣቴም በተጨማሪ አብረውኝ ያዩት ጓደኞቼና በሲኒማ ቤቱ የነበረው ተመልካችም በአብዛኛው እንደተዝናኑበት ታዝቤያለሁ። እንደውም ፊልሙ ከዘመናችን ቀድሞ የተሰራ፣ ከተረት ተረት ያለፈ ልዩ ታሪክ ይዞ የቀረበ ይመስለኛል። ስለዚህም ጸሐፊው በንጹህ አእምሮ ፊልሙን በድጋሚ ቢያዩት ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ሌላው ያነሱት ነጥብ ርዕሱን ከማያስታውሱት (ዝንጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል) የውጪ ፊልም ጋር እንደሚመሳሰል እና እንደተኮረጀ ነው። ይህ መቼም ከባድ ነው። አሉባልታ የመሰለ ማስረጃ የሌለው ክስ ማቅረብ ከአንድ ምክንያታዊ ከሆነ ጸሐፊ አይጠበቅም። አቧራ በሌለበት አቧራ ለማስነሳት ካልሆነ በቀር።

በ “መፈንቅለ ሴቶች” ፊልም ላይ በገሀዱ ዓለም ያለው የወንዶች የበላይነት ሴቶቹ ጋር ሆኖ እናገኝዋለን። እኔ በበኩሌ እንደሴትነቴ ደስ ነው ያለኝ። ሌላው ቢቀር ሴቶች የበላይ ሆነው ወንዶችን ሲገዙ ተመልክቻለሁ። ወንዶችም ቢሆኑም በሴቶች ላይ ሲፈጽሙት የነበረው በራሳቸው ላይ ሲደርስ የተመለከቱ ይመስለኛል። ይህም በሲኒማ ቤት ያለውን የሳቅ ድምቀት እንደከፋፈለውና ቡድናዊ እንዲሆን ማድረጉን ታዝቤያለሁ። ሴቶች ሲስቁ ወንዶች ይበሽቃሉ፤ ወንዶች ሲስቁ ደግሞ ሴቶች ይበሽቃሉ። እኔ ስገምት ጸሐፊው የወንድነት ስሜታቸው ተነክቶባቸው በንዴት ሚዛናዊነታቸውን ያሳጣቸው ይመስለኛል። መቼም እንደኔ እንደኔ ወንድ የበላይ ነው የሚል የቅድመ አያቱ አስተሳሰብ ያልተለየው ኮበሌ፤ በምንም ተዓምር ፊልሙ ሊያስቀው አይችልም - ፊልሙ ቢያስቅም። ለምን ብትሉኝ? በሴት ልጅ የተሸነፈ ስለሚመስለው።

ሌላው ጸሐፊው ያነሱት ነጥብ «መሰረታዊ ተጠይቆችን አይመልስም» የሚል ነው። በዚህም የተጠቀሰው መቼቱ ነው። «ተዋናዮቹ አማርኛ ስለሚናገሩ ነው እንጂ መቼቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ አይታወቅም» ብለዋል። ፊልም ማለት መቼም ልቦለድ መጽሐፍ አይደለም፤ ሁሉ ነገር በቃላት የሚገለጽበት። ነገር ግን ፊልም ስለሆነ ሁሉ ነገር በምስል ይገለጽበታል። የፊልሙ ዘመን አሁን ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም የወንዶች እና ሴቶች ባህሪ እና ስብዕና ከመቀየሩ ውጪ ፊልሙ ላይ የሚታዩ ነገሮች ሁሉ ዛሬን ይገልጻሉ። መቼም ቅን ልቦና ካለ “የት” የሚለውንም ነገር ፊልሙ በደንብ አድርጎ ይመልሳል። ምክንያቱም ተዋንያኖቹን አንድ የኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ እንጂ የሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ ወይም የሮም አደባባይ ላይ አናገኛቸውምና ነው። በዚህም ምክንያት «መፈንቅለ ሴቶች መቼቱ አይታወቅም» የሚለው ክስ አመክኖአዊ ነው ብዬ አልቀበለውም።

ጸሐፊው «የፊልሙ ታሪክ፤ ሴራና ልብ ሰቀላ የሌለውና የማያልቅ ተረት ተረት ነው» የሚል ሀሳብም አንስተዋል። ቁም ነገር ጠብቀው እንደነበርም ጠቅሰዋል። ይሁና!…… ለማንኛውም “መፈንቅለ ሴቶች” ዘውጉ ኮሜዲ ነው። ኮሜዲ ፊልም ላይ ቁም ነገር ሊኖር ይገባል የሚል ህግ እንደሌለ ይታወቃል። በተጨማሪም ኮሜዲ በባህሪው ሴራው ያልጠበቀ እና ያልተወሳሰበ እንዲሁም ብዙም ልብ ሰቀላ የማይጠበቅበት ዘውግ እንደሆነ አውቃለሁ። በቃ እያሳቀ ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት በልል ሴራ (ባልጠበቀ)፣ የታሪክ አወቃቀር እና ፍሰት የሚገነባ ነው። ከዚህ አንጻር “መፈንቅለ ሴቶች” ልብ ሰቀላ የለውም፤ በቅጡ አልተዋቀረም ለማለት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ተመልካቹ ፊልሙን ከጅማሬው እስከፍጻሜው አይቶ ተዝናንቶ ሲወጣ በአይኔ ስለተመለከትኩ ነው። ፀሐፊው የታሪኩ አወቃቀርና ሴራውን ጨምሮ በሰጡት አስተያየት ሙሉ በሙሉ በሙሉም ባይሆን በከፊል የምስማማ ቢሆንም፣ ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ ፊልሙን ሙሉ በሙሉ ጥላሸት ለመቀባት መሞከር ጤናማ አዕምሮ ካለው ሰው አይጠበቅም።

ፊልሙን ሁለቴ ተመልክቼዋለሁ፡፡ በመጀመሪያ ያየሁት “መፈንቅለ ሴቶች” በእርግጥም የታሪክ ችግር ነበረበት፡፡ ፊልሙ በእንጥልጥል መቋጨቱና የታሪክ ፍሰቱ ላይ ችግር እንደነበር አስታውሳለሁ። በሚዲያ ላይ መስተካከሉን ሰምቼ እስኪ እንዴት ሊያስተካክሉት ይችላሉ ብዬ ደግሜ ስመለከተው ግን ፊልሙ በጥሩ አጽመ ታሪክ ተዋቅሮና ተስተካክሎ መቅረቡ አስደንቆኛል። ተስፋ ካልቆረጡ ፊልምን አስተካክሎ ማቅረብ እንደሚቻል ባለሙያዎቹ በስራ አሳይተውናል። አንዴም ሁለቴም ያየው ተመልካች በአድናቆት ተቀብሏቸዋል። ከዚሁ ፊልም ቀጥሎ ሌሎች ፊልሞች እየተስተካከሉ መቅረባቸው ደግሞ ይበልጥ አስደስቶኛል። ይልቅስ እንደነዚህ ያሉ ተስፋ ሰጪ ባለሙያዎች እንዳይጠፉብን ብናበረታታቸው የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ጸሐፊው የታላቁ ደራሲና ዳይሬክተር ጀምስ ካሜሮንን የህይወት ታሪክ ቢያነቡ ጥሩ ነው፡፡ የዛሬዎቹ “ታይታኒክ” እና “አቫተር” ፊልሞች ለስኬት የበቁት ትላንት ቅስማቸውና ሞራላቸው በተሰበሩት በእኚሁ ታላቅ ደራሲና ዳይሬክተር መሆኑን ይረዱ ነበር፡፡ በመጨረሻም ጸሐፊው የገለጹት የጋሽ ስብሐትን ጉዳይ ነው። እኔ የምለው ፊልሙ ላይ ያየነው ስብሐትን ነው ወይስ አንድን ግለሰብ የወከለ ገጸ ባህሪ? እኔ የተረዳሁት ጸሐፊው ፊልሙን በደንብ አለመመልከታቸውን ነው። ካልተሳሳትኩ ጋሽ ስብሐት በ “መፈንቅለ ሴቶች” ፊልም ውስጥ ያለው ሚና ፀሃፊው እንዳሉት ሳይካትሪስት ሳይሆን የባህል ሃኪም ነው። ለዛውም ሴቶችን የሚደግፍ የባህል ሀኪም። ጋሽ ስብሐት የተቀመጠበት አካባቢ በባህላዊ የህክምና ቁሳቁሶች የተሞላ ነው። ለሴቶችም ስለሚደግፍ ወንዶች መጥተው ሲያማክሩት ቀና ያልሆነ አሉታዊ መልስ እየሰጠ ያባርራቸዋል። ጸሐፊው በፊልሙ ውስጥ ደራሲውን ስብሐት ለማየት አስቦ ከነበረ ተሳስቷል። ከገጸ ባህሪውም ቁም ነገር ጠብቆ ከሆነ ስህተት ነው። የፊልሙ አዘጋጆች የምንወደውን ስብሐትን በፊልም ቀርጸው ታሪክ ስላኖሩልን ሊወደሱ በተገባ ነበር።  ሐሳቤን ስደመድም ፊልሙ «ኹሉ በኩሉ» ነው ለማለት አይደለም። ነገር ግን አሁን ካሉት ፊልሞች አንጻር ስንመለከተው አዲስ እይታ ይዞ መጥቷል ብዬ አስባለሁ - ከነስህተቶቹ። ለኛ ለሴቶችም በጣም ያደላል፡፡ አልዋሽም ያ በጣም አስደስቶኛል። በመጨረሻም የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ከፈለግን ባለሙያዎቹን እያሳደድን በኩርኩም ከማለት መደገፍ እና ማገዝ ሳይሻልም አይቀርም፡፡  ለፊልሙ አዘጋጆች የምመክረውም፤ “በርቱ ጠንክሩ ተስፋ አትቁረጡ። አሁን ያሉባችሁን ችግሮች አርማችሁ ለወደፊቱ የተሻለ ስራ ይዛችሁ መቅረብ ይኖርባችኋል” በማለት ነው። «እኔ አይቼ ስላልወደድኩት እናንተም አትወዱትም» የሚል ከግላዊ ስሜት የመነጨ አሉታዊ አስተሳሰብን ማንጸባረቅና ሰው ላይ መጫን ግን ተገቢ መስሎ አይሰማኝም። ቸር ሰንብቱ።

 

 

Read 3195 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:34