Sunday, 19 February 2017 00:00

ኢሳ ሃያቱ እና 39ኛው የካፍ ጉባኤ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     39ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከወር በኋላ  በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በጉባኤው የሁሉም የካፍ አባል ሀገሮች ተወካዮችን ጨምሮ ከ380 በላይ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 56 አባል አገራት ያሉት ካፍ ከተመሰረተ  59 ዓመቱ ሲሆን በአዲስ አበባው ጉባኤ ፕሬዝዳንቱ ኢሳ ሃያቱ ለስምንተኛ የስራ ዘመን  ለመመረጥ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ዋና ተፎካካሪያቸው የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት የማዳጋስካር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ናቸው፡፡
ኢሳ ሃያቱ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት ለሰባት የስራ ዘመናት ማለትም ለ28 ዓመታት እንዳገለገሉ ይታወቃል፡፡በአዲስ አበባ  የካፍ 39ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄደው ምርጫ በድጋሚ ተመርጠው  ፕሬዝዳንት ከሆኑ በአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳደር ከፍተኛ ስልጣን የቆዩባቸው ዓመታት 33 ዓመት ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም የስፖርት ታሪክ  በከፍተኛው ነው፡፡ የፊፋ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፈረንሳዊው ጁሌይስ ሪሜትም በስልጣናቸው 33 ዓመት የቆዩበትን ስልጣን ስለሚስተካከል ነው፡፡ የኦሎምፒኩ መስራች ፈረንሳዊው ፒዬር ደ ኩበርቲን በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንትነት ከ1896 እስከ 1925 እኤአ  ለ29 ዓመታት መስራታቸው ይታወቃል፡፡
የ71 ዓመቱ ካሜሮናዊ ኢሳ ሃያቱ ቅርጫት ኳስ ተጨዋች ነበሩ፡፡ በ400 ሜትር እና በ800 ሜትር የአጭር ርቀት ውድድሮች በአገራቸው እና በአህጉራዊ ውድድሮች ስኬታማ የሩጫ ዘመን አሳልፈዋል፡፡ በእግር ኳስ አስተዳደር የመጀመርያ ስራቸው የካሜሮን መረብ ኳስ ፌደሬሽን ፀሃፊ መሆናቸው ነበር፡፡ ከ1974 እስከ 1983 እኤአ ደግሞ የካሜሮን እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ በመሆን አገልግለው ከዚያም ከ1985 እስከ 1988 እኤአ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ ሲካሄድ የካፍ የወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው በመሾም እስከ 2017 እኤአ ቀጥለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ባሻገር በፊፋ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከ1990 እኤአ ጀምሮ፤ የፊፋ ምክትል ፕሬዝዳንት ከ1992 እኤአ ጀምሮ፤ የፊፋ ሲነዬር ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ከ2014 ጀምሮ እንዲሁም የፊፋ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው በ2015 ለ4 ወራት ሰርተዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባልም ሲሆኑ ከ2001 እኤአ ጀምሮ የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር ናቸው፡፡
በኢሳ ሃያቱ የፕሬዝዳንትነት ዘመን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን  የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎቹን ከ8 ወደ16 ማሳደጉ፤ በ2010 እኤአ 19ኛው ዓለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ ማስተናገዱ፤ የአፍሪካ ከፍተኛ ክለብ ውድድሮች በቲቪ ብሮድካስት እና በስፖንሰርሺፕ መጠናከራቸው እንዲሁም የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ውድድር መጀመሩ አበይት የለውጥ ምእራፎች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም ካፍ  ከፈረንሳዩ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ አምራች ኩባንያ  ቶታል ጋር ዘንድሮ ለ8 ዓመታት የ1 ቢዮን ዶላር ስፖንሰርሺፕ ስምምነት ማድረጉ የኢሳ ሃያቱን ዳም የመመረጥ እድል ሰፊ ያደርገዋል፡፡

                    ስለኢትዮጵያዊው የካፍ ፕሬዝዳንት ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ

 • ትውልዳቸው በጅማ ነው፡፡
• በስምንት ዓመታቸው ኳስ መጫወት ጀመሩ፡፡ ለ23 ዓመታት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጫውተዋል። በ365 ጨዋታዎች 318 ጎሎች አስመዝግበዋል፡፡
• ለብሄራዊ ቡድን 15 ጊዜ ተጫውተው 3 ጎሎች በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ በድንንም አሰልጠናዋል፡፡ በ1962 በሳቸው አመራር ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡
• በ1943 የመጀመርያውን የስፖርት ቢሮ ከፍተዋል። በ1964 እኤአ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን
ሲመሰረት አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡
• የካፍ ምክትል ፕሬዝዳንት 1964 እስከ 1972 ለ8 ዓመታት ሆነዋል፡፡
• በካፍ ፕሬዝዳንተነት ከ1972 እስከ 1987 ለ15 ዓመታት የሰሩ ሲሆን፤ የአፍሪካ ስፖርት ኮንግረስ፤ የዓለም አ ቀፉ የ ኦሎምፒክ ኮ ሚቴ፤ የ ዓለም አ ቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እና የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሆነውም አገልግለዋል፡፡
• በ1987 እኤአ ላይ በ65 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

              ከኢሳ ሃያቱ በፊት የካፍ ፕሬዝዳንቶች
• አብድልአዚዝ አብደላህ ሳሌም (ግብፃዊ፤ ከ1957-1958 እኤአ)
• አብድል አዚዝሙስተፋ (ግብፃዊ፤ ከ1958-1968 እኤአ)
• አብድል ሃሚል መሀመድ (ሱዳናዊ፤ ከ1968-1972 እኤአ)
• ይድነቃቸው ተሰማ (ኢትዮጵያዊ ከ1972-1987 እኤአ)
• አብድል ሃሚል መሀመድ (ሱዳናዊ፤ በጊዜያዊነት ከ1987-1988 እኤአ)

Read 1634 times