Sunday, 26 February 2017 00:00

አሣሣቢው የትራፊክ አደጋ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(16 votes)

 - በአገራችን በቀን 10 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ያጣሉ
              - በአዲስ አበባ ብቻ ባለፉት 6 ወራት 244 ሰዎች በመኪና አደጋ ህይወታቸው አልፏል፡፡
              - ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ወድሟል
              - ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እያደረሱ ያሉት አዳዲስና ዘመናዊ መኪኖች ናቸው
               
    በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና በየቀኑ 10 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እንደሚያጡና 31 ያህሉ ለከባድ የአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ተጠቆመ፡፡
ከመንገድ ትራፊክ ደህንነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአገሪቱ በየዕለቱ እየተከሰተ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም 3847 ሰዎች በአደጋው ህይወታቸውን እንዳጡ ያመለከተው መረጃው፤ በ2008 ዓ.ም ቁጥጥር እየጨመረ መሄዱን ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተመዘገቡ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ600 ሺ የማይበልጥ መሆኑን የጠቆመው ይኸው መረጃ፤ እያደረሰ ያለው አደጋ ግን አገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በትራፊክ አደጋ ታዋቂነትን እንድታገኝ ያደረጋት ሲሆን 90 በመቶ አደጋ ከሚደርስባቸው አገራት አንዷም ሆናለች ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት፤ ከሐምሌ 2008 እስከ ታህሳስ 2009 ዓ.ም ድረስ 244 የሞት አደጋና 8070 ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም 585 ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ይኸው መረጃ አመላክቷል፡፡ 170 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት መውደሙንም ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየደረሱ ካሉ የትራፊክ አደጋዎች አብዛኛዎቹ የሚከሰቱት ዘመናዊና አዳዲስ በሆኑ መኪኖች መሆኑን የጠቆመው መረጃው ከ5-10 ዓመት ድረስ ያገለገሉ አዳዲስ መኪናዎች አብዛኛውን አደጋ ማድረሳቸውን አመልክቷል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ ከሚባሉ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች መካከል የመኪና አደጋ በዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአለም በየዕለቱ 3400 ሰዎች በዚሁ የመኪና አደጋ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በየዓመቱ 1.24 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Read 11145 times