Print this page
Saturday, 17 March 2012 10:35

እንደ ስብሐት

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

ከአዘጋጁ:- ውድ አንባብያን፤ በዚህ አምድ በአንጋፋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር የአፃፃፍ

ዘዬ የተኳሉ ጥበባዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም ፍልስፍናዊ መጣጥፎችና ወጐች ይስተናገዳሉ፡፡ እግረመንገዳችንንም ዕውቁን የብዕር ሰው ስብአት ለአብን እየዘከርን፡፡ ለአምዱ የሚመጥኑ ጽሑፎችን ብትልኩልን ሚዛን ላይ እያወጣን እንደየሁኔታውና አግባቡ እናስተናግዳለን፡፡

ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰንና ተአምረ - ሁለትነታቸው

ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ጥሎባቸው አገራቸው እንግሊዝን በከፍተኛ መንቀጥቀጥ ታጅበው ይወዱዋታል - እንዲሁም እንግሊዛውያንን፡፡ከእንግሊዝና ከእንግሊዛውያን ጋር ለንፅፅር የሚቀርብ ሌላ አገርና ህዝብ ካለ ወዮለት!! እንዲሁ በዚያው ጉልበት የበቂውን ያህል ይጠሉታል (በመንቀጥቀጥ መታጀባቸውን ሳይዘነጉ)

አንድ ጊዜ JAMES BOSWELL ሲቆሰቁሳቸው (ሊያነዳቸው ሳይሆን ሊፅፋቸው) ስለ ፈረንሳውያንና ስለ እንግሊዛውያን የባህሪ ልዩነት ጠየቃቸው፡፡ ዶክተሩ “ካመጣሽ እግዜር ያመጣሽ” ሳይሉ አልቀሩም፣ በአበው ወግ፡፡ እንዲህ አሉ፡-

“ልዩነታቸው ይሄ ነው፡፡ ፈረንሳዊው አወቀም አላወቀም ዘወትር ማውራት አለበት፡፡ እንግሊዛዊው ደግሞ የማያውቀው ላይ ሲደርስ አፉን ይይዛል፡፡”

አበው ሁሌም የትም አለመገኘታቸው በጀ እንጂ “ለራስ ሲቆርሱ”ን ይተርቱባቸው ነበር፡፡ ዶክተሩ ግን ምን ተዕዳቸው! ይቀጥላሉ፡፡ ፈረንሳይ የታላቋ ብሪታኒያ ኮሎኒያዊ ተቀናቃኝ ጠላት ናትና ሁሌም ስሟ ሲነሳ ዶክተሩ መንቀጥቀጥ እንዳለባቸው አይዘነጉም፡፡ አንዳንዴ እረስተው ስለማይረሱዋት የውይይታቸውን መሪ ዞር አድርገው ፈረንሳይ ላይ ይዞሩባታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ “ትህትና ተፈጥሯዊ አይደለም ይላሉ?” ተብለው ሲጠየቁ እንዲህ መልሰዋል፡፡

“እንደዚያ ነው ለማለት አልችልም፡፡ በተፈጥሮው ትሁት የሆነ ሰው ለማግኘት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን የበለጠ በተማሩት መጠን የበለጠ ትሁት የሚኮን ይመስለኛል፡፡ ፈረንሳዮችን ተመልከቱ፡፡ መረኖች፣ አሳዳጊ የበደላቸውና ከግምት ውጭ የሆኑ ህዝቦች ናቸው፡፡ ፈረንሳይ በመሄዴ ያገኘሁት ትልቅ ነገር በአገሬ የበለጠ መደሰት እንዳለብኝ ማወቄን ነው፡፡”

አማትበን ስንቀጥል -

ዶክተሩ ከፈረንሳይ እኩል አሜሪካንና አሜሪካውያንንም ይጠላሉ፡፡ አሁንም ቦስዌል እንዲህ አሉ ይለናል፡፡

“I am willing to love mankind, except an American” (ከአሜሪካዊ በስተቀር የሰውን ልጅ ሁሉ ለማፍቀር ዝግጁ ነኝ) በዶክተሩ አትፍረዱባቸው፡፡ አገር ወዳድነትና ለወገን ተቆርቋሪነት ብቻውን አይመጣም፡፡ ግብታዊነትንና ጭፍንነትን አንዱን አዝሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ነው፡፡

ዶክተሩ ከአገር መውጣትን ከፍቅረኛ እንደመነጠል ይመለከቱታል፡፡ “የትኛውም ብልህ ሰው ከአገር ስለመራቅ ማሰብ የለበትም፤ በመራቁ የሚያከናውነው ሳይንሳዊ ተግባር ከሌለ በስተቀር” ይላሉ፡፡ በዚህ ጠባያቸው ቦስዌል ሁሌም ግራ እንደተጋባ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ወደ አየርላንድ እንሂድ ይላቸዋል፡፡

“አየርላንድ መሄድ ከሚገባኝ ቦታ የመጨረሻዋ ናት” ይላሉ

“ዋና ከተማዋ ደብሊንን ማየት የለብዎትምን?”

“የለብኝም፣ ደብሊን፣ አስቀያሚ ከተማ ብቻ ናት፡፡”

“ዝና ያላት ከተማ አለመሆኗ በራሱ ለመታየት አያበቃትም?”

“ለመታየት ያበቃታል፡፡ ነገር ግን ከዚህ እስከመሄድ ድረስ አይደለም”

ሰሜን አየርላንድና ስኮትላንድ የታላቋ ብሪታኒያ አካል ቢሆኑም የዶክተሩ አገር ወዳድነት ቀላቅሎ ለመመልከት ይቸገራል፡፡ አንድ ጊዜ ወደ ስኮትላንድ ሄደው እንዲህ እንዳሉ ይነገራል፡፡

“አንድ ስኮትላንዳዊ አንድ ጥሩ ነገር አለኝ ማለት ያለበት ወደ ኢንግላንድ የሚያደርሰውን አውራ ጐዳና  ነው፡፡”

ጭፍንነት እንዲህ ያምራል? ግብታዊነት ያማልላል? (ሰውየው ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ናቸዋ!) አንድ እብሪትና ሌላ ትዕቢት የወለደው ገጠመኛቸውን ነግረን ወደ ሌላ እንተላለፍ፡፡

ሰሜን አየርላንዳዊ ብሔራዊ ታጋይ ነው፡፡ “ተመልሻለሁ ተመለሱ ወደ ሀቀኛው ወደ ሳይንሱ” እያለ ከኢንግላንድ ጋር የመቀላቀልን ስብከት ጀምሯል፡፡ የአንድነት ማህበር አቋቁሟል፡፡ አንድ ቀን ቁጭ ብለው ሲያወሩ ዶክተሩ እንዲህ አሉት፡፡

“ጌታዬ፣ ከእኛ ጋር አንድነት መፍጠር አያስፈልጋችሁም፡፡ እናንተ የሚዘረፍ ነገር ካላችሁ አንድነቱ ግድ የሚለን እኛ ነን፡፡ ስኮትላንዶችም’ኮ የምንዘርፋቸው ነገር ስለነበራቸው አይደል የዘረፍናቸው፡፡” ወደድክም፣ ጠላህም እንደማለት ነው፡፡

ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን የእናት አገራቸው ጉዳይ እንዲህ የሚያንቀጠቅጣቸው ለምንድነው? ብለን እንጠይቅ፡፡ እንደኛ ቅደስቲቷ አገር እንግሊዝ በማር በወተት ስላሳደገቻቸው አይደለም፡፡ ጥሎባቸው ነው ማለቱ ይቀላል፡፡ ውዲቱ እንግሊዝ ያኔ ለትንሹ ጆንሰን ማቅረብ የቻለችው ካቅሙ በላይ የሆኑ መፃህፍትን ነበር፡፡ ምክንያቱም አባቱ የሊችፊልድ ከተማ ችስታ መፅሐፍት ነጋዴ ነበሩ፡፡ በዚህ ላይ እንግዲህ ተፈጥሮይቱም የጤና አቅርቦቷን በመንፈግ፣ የትንሹን ጆንሰን ህይወት ገሃነም ለማድረግ ጀምራለች፡፡ ከእይታው እና ከመስማት ፀጋው ላይ ግማሽ - ግማሹን ቀንሳለች፡፡ አእምሮውም ላይ የፍርሃትና የቁም ቅዠት እንከኖች ጣል አድርጋለች፡፡ ለምሳሌ እናቱ ሩቅ ከተማ የሚኖሩ ቢሆንም እንደሚያናግራቸው ያምን ነበር፤ ከሞቱም በኋላ በዚያው የማናገር እምነቱ ቀጥሏል፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት!

ይሁንና ግሩም የማስታወስ ችሎታው ላይ ተፈጥሮይቱ ጣልቃ አልገባችም፡፡ ትምህርት ሲቀበልም የጉድ ነው፡፡ በፍጥነት ተረድቶ በቀላሉ ማስታወስ መቻሉ የሚያስደምም ነበር ይላሉ፡፡ ታዲያ በዚህ አእምሮው እኛ ማድረግ ያልቻልነውን ችሎ ይሆን ከተማ አሻግሮ፣ ሞትን አቆራርጦ የሚያደምጠው? ማን ያውቃል?

አለች ደሞ አብሮ አደግ ድህነቱ፡፡ እንደ መልካም አሽከር ልጅነቱን አጅባ፣ ጉርምስናውን ተቀብላ፣ አብራው ኮሌጅ ገብታ፣ ትምህርቱን እንዲያቋርጥ ያደረገች ጥሩ ወዳጁ ናት፡፡ የዕለት ጉርሱ፣ የአመት ልብሱ ላይ በጉልህ ተፅፋ ዘወትር ትነበባለች፡፡ በመጨረሻ ድህነቲቱን ሽሽት ገሌ ገባ፡፡ ባላቸው የሞቱባቸው ሞጃ አገባ፡፡ እሱን የሚያክል ልጅ የነበራቸው፡፡ ወፍራም ሰውነታቸውን ዝብርቅርቅ ያለ ደማቅ ቀሚስ ውስጥ ከትተው ሲመጡ ከሩቅ የሚታዩ፡፡ ወጣቱ ጆንሰን ጠቅልሏቸው ሚስስ ጆንሰን እስኪያሰኛቸው ድረስ ሚስስ ኤልዛቤት ፓርተር ይባሉ ነበር፡፡

አንዳንድ ዘባራቂ ጥልቅ ብዬ ይሄንን የዶክተሩን ውሳኔ ሲሰማ፣ ያው ድህነቱ ይሻለው ነበር ይል ይሆናል፡፡ ዶክተሩ ግን እንዲህ አይሉም፡፡ እሳቸው የሚሉት It is commonly a weak man, who marries for love” (ስለ ፍቅር የሚያገባ ሰው ደካማነቱ የተለመደ ነገር ነው)

“ቆፍጣናው የእንግሊዚቷ ልጅ እኔ ነኝ ደሞ ለአንዲት ሴት ፍቅር ስል እንደማለት ነው ማን መሰልናቸው እኛን የማይረባ ፈረንሳይ ማድረጋቸው ነው እንዴ?”

የፈረደባቸው ፈረንሳውያን በሴቶች ጉዳይም በዶክተሩ ከመወቀስ አልዳኑም፡፡ እንዲህ አሉ፡፡ “ፓሪስ ስትሄድ ፈረንሳውያን ሲኮሩ የምትመለከተው ከሴቶች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ለውይይት በመቀመጣቸው ነው፡፡ እኛ ደግሞ ሲገባን ፈረንሳውያኑ ወንዶች ከሴቶቹ የተሻለ ባለማሰባቸው ነው፡፡”

ዶክተር ጆንሰን ከሴቶች ጋር ፍቅርና እኩልነት የሚባሉትን ዝባዝንኬ ያውግዙ እንጂ የበታችነቱን አይጠየፉትም፡፡ ይሄን እሳቸው ባይነግሩንም እኛ ህይወታቸውን ስንመረምር ደርሰንበታል፡፡ እማማ ፓርተር (በወይዘሮ አሰጋሽ ሴት ባላባታዊ ስልት) ባላቸውን አሽከር አድርገው ነው የገዙዋቸው (የሌሊቱን ባናውቅም የቀኑን ማለታችን ነው) ወደ አንድ ቦታ በፈረስ እንኳን ሲሄዱ በባልና ሚስት ወግ ጐን ለጐን አልነበረም፡፡ (ማን ቢፈቅድ) ዶክተር ከኋላ ናቸው፡፡ እማማ ፓርተር አስፈላጊ መስሎ ሲታያቸው ትዕዛዛቸውን ወደ ኋላ ያስተላልፋሉ፡፡

“ወደፊት ጋልብ፣ ምን ሶምሶማ ይረግጥብናል ከኋላችን ሆኖ” ዶክተር ጆንሰን እንደ ትዕዛዙ ኃይልና መጠን ፈጥነው ይገኛሉ፡፡

እማማ ፓርተር ሞቱ (ተረት ቢሆን በተድላ በፍሰሃ ኖረው የሚል እንጨምር ነበር፡፡ እውነት ሆነብን እንጂ) ውድ አንባቢያን እንደገመታችሁት ሀብቱን ዶክተሩ ወርሰዋል፡፡ መቼም ዘባራቂ ጥልቅ ብዬ ባለመታጣቱ “ተገላገሉ” የሚል አስተያየት መሰንዘሩ ግድ ነው፡፡ እኛም መልስ መስጠታችን እንዲሁ ግድ ነው፡፡ ትልቅ ስህተት! ዶክተሩ ተገላገልኩ አላሉማ! ያላሉትን! እሳቸው ያሉት (ወደኋላ ዘመናቸው ላይ ሲያምሰለስሉና ሲያብላሉ ቆይተው መሆን አለበት) እንዲህ ነው፡፡

“ሚስትን ያህል ነገር ማጣት ምን ማለት እንደሆነ አውቀዋለሁ፡፡ ከሞላ ጐደል ልቤ ተሰብሯልና” (በአማርኛ ለዛውን አጣ መሰለኝ I have known what it was to lose a wife I had almost broke my heart) ውድ አሽሟጣጪያውያን:- አሁን “ድንቄም” የማለት ሰአቷ ደርሳለች፡፡ ከማሽሟጠጣችሁ ስትመለሱ ግን ይሄን አድምጡ፡፡ ዶክተሩ ፋይዳ ለሌላU አገራቸው እንዲሁም ለቁንን ሚስታቸው በግብታዊነትና በመንቀጥቀጥ ታምነው አልፈዋል (አልፈዋል አልን እንዴ? ምን አስቸኮለን ያውም እኮ ደራሲ ሆነው ሳለ ስለ ድርሰት ምንም ሳንል) ነገር ግን ዶክተሩ ስለ ድርሰት እንዲህ በማለታቸው እንጽናናለን፡፡

“ሰዎች ሁሉ ስለ ሥነ ጽሑፍ ሲሉ እንደሚያከብሩኝ አውቃለሁ፡፡ የሚገርመው ግን ሥነ ጽሑፍ ከተቀረው አለም ጋር ሲነፃፀር ኢምንትና የማይረባ ነገር ነው”አፋችሁን አሲያዝናችሁ ውድ አንባቢያን? እንግዲያው ቀጥታ ወደማይቀረው የሞት ተዳፋት እናቅና፡፡ ቆሞ መቅረት ወደሌለበት፣ መንደርደር ዕጣ ፈንታ ወደሆነበት…

…የዶክተሩ የሞት ሰበብ (ያለሰበብ ቆሞ ይቀር ይመስል) ድንገት የጣላቸው ደም ብዛት ነው፡፡ በኛ ቢሆን አጋንንት ነበር፡፡ (እጅና እግራቸውን ያዛቸው አበስኩ ገበርኩ የት አገኛቸው? ምናምን እንዳለ ሆኖ) ዶክተሩ አልጋ ላይ ዋሉ፡፡ የአልጋ ላይ ዘመናቸውን ያሳለፉት በመናዘዝ ይመስለናል፡፡ ረጅም አታካች ኑዛዜ፡፡ ሰባራ ሳንቲም ሳትቀር አደላድለው ጨረሱ እና “አመሰግናለሁ” ብለው ሞቱ፡፡ ምስጋናቸው ለአስታማሚዎች ብቻ አይደለም፡፡ ለኛም ጭምር ነው - ስለዘከርናቸው፡

 

 

Read 2345 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:40