Sunday, 26 February 2017 00:00

ትምህርት ሚኒስቴር ከጠመመ፣ ወደ “የኔታ” ብንመለስ ይሻላል!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(19 votes)

  • የጨነቀው ብዙ ቢያወራ አይገርምም። ተማሪዎች፣ አንብበው መገንዘብ የማይችሉ፣ “የዘመናዊ መሃይምነት” ሰለባ እየሆኑ ነው።“ቢላዋ” የሚለውን ቃል “ካራዋ” ብሎ ማንበብ፤ “Dog” የሚለውን ቃል “Cat” ብሎ ማንበብ፣ … ይሄ አዲስ አይነት መሀይምነት ነው፡፡
      • ወደ የኔታ የመመለስ ሃሳብ፣ ለቀልድ ለዋዛ የተነገረ አይደለም። ከትልቅ ጥናት የተገኘ “የመፍትሄ ሃሳብ” ነው። በንባብ ችሎታ ዙሪያ፣
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ትልቁ ጥናት ማየት ትችላላችሁ። (በትምህርት ሚኒስቴር እና በዩኤስኤአይዲ ትብብር በ2002 ዓ.ም የተካሄደ
ጥናት)።
      • አሁን ደግሞ የባሰ ተስፋ አስቆራጭ ሃሳብ መጥቷል። “የዛሬ ልጆች፣ ት/ቤት ገብተው፣ የማንበብ ችሎታ ያዳብራሉ” ብለን እንዳንጠብቅ
ተነግሮናል። ከበርካታ ትውልዶች በኋላ ነው፣ ማንበብ የሚችል ትውልድ የሚመጣው ተብሏል። (ይሄ ትኩስ የጥናት ሪፖርት ነው -
በ2008 ዓ.ም በዩኤስኤአይዲ እና በትምህርት ሚኒስቴር ትብብር የተካሄደ ጥናት)፡፡
     • በሌላ አነጋገር፣ ይሄ “ዘመናዊ መሃይምነት”፣ ለበርካታ ዓመታት መፍትሄ ሳያገኝ ይቀጥላል እንደማለት ነው። እና በፀጋ መቀበል ሊኖርብን
ነው። ምን ተሻለ? የኔታዎችን ፈልገን፣ ልጆችን ፊደል እናስተምር። ወይም የፊደል ገበታ ገዝተን እናለማምዳቸው።

      በቅንነት ለሚያገናዝብ ሰው፣ ነገርዬው ውስብስብ አይደለም። በጥቅሉ፣ ሁለት አይነት “የንባብ ማስተማሪያ ዘዴዎች” አሉ። አንደኛው ዘዴ፣ ከፊደላት ወይም ከሆሄያት የሚጀምር ትምህርት ነው - ፊደልን በአግባቡ በመጨበጥ፣ ወደ ቃላትና ወደ ዓረፍተ-ነገር እያደገና እየሰፋ ይቀጥላል (phonics ይሉታል)።
ሌላኛው ዘዴ፣ ከዓረፍተ ነገር ወይም ከቃላት ነው፣ የንባብ ትምህርትን የሚጀምረው (whole language ይሉታል)። ተማሪዎች፣ ፊደላትን ለይተው ሳያውቁ፣ በቀጥታ ወደ ንባብ እንዴ መግባት ይችላሉ? ያው፣ በሺ የሚቆጠሩ ቃላትን እንደ ስዕል እንዲሸመድዱ ይገደዳሉ። በዚህም ነው፣ እስከዛሬ ያልነበረ፣ አዲስ አይነት “ዘመናዊ መሃይምነት” ሲስፋፋ የሚታየው።
አንድ የስራ ባልደረባዬ የታዘበውን ምሳሌ ልጥቀስላችሁ - “ቢላዋ” የሚለውን ቃል፣ “ካራይ” ብሎ የማንበብ ችግር አጋጥሟችሁ ያውቃል? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣ አዲስ አይነት የንባብ ችግር ነው።
አዎ፣ በአግባቡ ማንበብ የምንችል ሰዎች፣ እንዲህ አይነት የንባብ ስህተት ሲያጋጥመን፣ ግራ እንጋባ ይሆናል። ግን፣ አስቡት።
ተማሪዎች ፊደል ላይ የተመሰረተ ንባብ ካልተለማመዱ... በዚያ ላይ፣ ከፊደል ጋር እንዳይቀራረቡ፣ የዘመኑ የትምህርት ዘዴ ጋሬጣ ከሆነባቸው፣ ሌላ አማራጭ የላቸውም። እያንዳንዱን ቃል እንደ ስዕል እንዲሸመድዱ፣ አልያም በግምት እንዲሞክሩ ነው፤ ሸክም የሚጫንባቸው። እንዴት መሰላችሁ? “ለማ” የሚለውን ቃል በልምምድ ማንበብ ቻላችሁ እንበል፡፡ “ማለ” የሚለውን ቃል ግን ማንበብ አትችሉም፡፡ ይህንንም መሸምደድ አለባችሁ፡፡ በእርግጥ ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ “ለማ” እና “ማለ” ይምታታባችኋል፡፡ አዲስ የንባብ ቀውስ ተፈጠረ ማለት ነው።
ድሮ ድሮ፣ የንባብ ስህተት አይከሰትም ነበር እያልኩ አይደለም። ይከሰታል።  በተለይ የፊደል ትምህርት ላይ ደከም የሚሉ ተማሪዎች ይሳሳታሉ። አሁን ግን፣ ስህተት የሚከሰተው በሁሉም ላይ ሆኗል - በጎበዝ ተማሪዎችም ላይ ጭምር። የፊደል ትምህርት እንደ ነውር ስለተቆጠረ፣ ሁሉም ተማሪዎች ላይ ድክመት ይፈጠራል።
ተማሪዎች ከፊደል እውቀት እንዲርቁ ባስገደድናቸው ቁጥር፣ ንባብ እንደ ቅዠት ይሆንባቸዋል፡፡ ቃላትን ለማንበብ የሚሞክሩት በፊደላት ላይ በመመስረት ሳይሆን፣... በስሜት በመመራት ይሆናል - በስሜትና በግምት! እንዴት በሉ።
“ቢላዋ” የሚለውን ፅሁፍ ሲያዩ፣... ነገርዬው፣ ከስለት ጋር የተያያዘ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። የስሜት ጭምጭምታ ልትሉት ትችላላችሁ። ቃሉ፣ ከስለት ጋር እንደሚዛመድ፣ በደምሳሳው፣... በስሜት ደረጃ ያስታውሳሉ። በዚህም ምክንያት፣ አንዳንዶቹ ተማሪዎች፣ “ምላጭ” ብለው ሊያነብቡት ይችላሉ። ንባብ ማለት... የስሜት፣ የግምትና የጭምጭምታ ጉዳይ እንዲሆንባቸው አድርገናላ። ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ፣ “ካራ” የሚለው ቃል ብልጭ ይልላቸዋል። ግን፣ ድምፁ ትንሽ ያጥርባቸዋል። ምን ይሻላል? የሆነ ድምፅ በመጨመር ሊያስረዝሙት ይጥራሉ... “ካራይ”፣ “ካራው”፣ “ካራዋ”... ብለው ያነብቡታል።
እንዲህ አይነት የንባብ ችግር፣ ዛሬ በዘመናችን የተፈጠረ አዲስ ችግር ነው - ተማሪዎችን ከፊደል ጋር በሚያራርቅ አዲስ የማስተማሪያ ዘዴ አማካኝነት የተፈጠረ! ...(የማስተማሪያ ዘዴ ሳይሆን የማደናገሪያ ዘዴ ብትሉት ይሻላል።) … በሌሎች አገራትም፣ ተመሳሳይ ቀውሶችን አስከትሏል። አሜሪካ ውስጥ፣ ይሄው “የማስተማሪያ ዘዴ”፣ ከ20 ዓመታት በፊት በተስፋፋበት ወቅት፣ ምን አይነት ችግር እንደተፈጠረ ለማየት አንድ ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ ተመልከቱ - (COGNITIVE SCIENCE Vol 23/4 ገፅ 548)።
Cat የሚለውን ቃል Cot ብሎ የማንበብ ችግር፣ አዲስ አይደለም። ድሮም የነበረ ነው። ነገር ግን፣ ይሄ የድሮ ችግር፣ በአዲሱ የማስተማሪያ ዘዴ ሳቢያ፣ ተባብሷል። ነገር ግን፣ አዳዲስ የንባብ ችግሮችም ተፈጥረዋል። ከፊደል ጋር እንዲጣላ የተደረገ ተማሪ፣ ፊደሎች ላይ በመመስረት፣ ማንበብ ስለማይችል፤ ፅሁፍንና ንባብን አራምባና ቆቦ ያደርጋቸዋል።
Cat የሚለውን ፅሁፍ ሲያይ፣ በደፈናው እንዴት እንደሚነበብ ለማስታወስ ይሞክራል። ትንሽ ትንሽ ትዝ ይለዋል። ቃሉ፣... ከእንስሳ ጋር የተገናኘ ሳይሆን አይቀርም። በዚህች የስሜት ጭምጭምታ እየተመራ፣ በግምት ለማንበብ ይሞክራል፡፡ dog ብሎ ያነብበዋል።
Sympathy የሚለውን ፅሁፍ፣ Orchestra ብሎ ማንበብስ? እንዲህ አይነት ስህተት እንዴት ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት። ፊደል የተማረ ሰው፣... እንዲህ አይነት ስህተት አይሰራም፡፡ በዘመናዊው የትምህርት ዘዴ ከፊደል ጋር ተራርቆ፣ ቃላትንና አረፍተ-ነገራትን እንዲማር የተፈረደበት ልጅ ግን፣ ለእንዲህ አይነት ቀውስ ይዳረጋል።
Sympathy የሚለው ፅሁፍ Symphony ከሚለው ፅሁፍ ጋር በመልክ ይመሳሰልበታል፡፡ … “ይህንን ፅሁፍ የሆነ ቦታ አውቀዋለሁ” የሚል የስሜት ጭምጭምታ ይፈጠርበታል፡፡ … ከሙዚቃ ጋር የተያያዘ ቃል ሳይሆን አይቀርም ብሎ ይገምታል። ኦርኬስትራ ደግሞ ሙዚቃ የሚጫወት ቡድን ነው። Orchestra ብሎ ያነብበዋል።
በቃ፣ ንባብ ማለት... በስሜት የሚመራ የግምት ሙከራ ሆኖ አረፈው። ይሄንን ስል፣ ደረቅ ስድብ እየሰነዘርኩ ሊመስል ይችላል። ግን፣ አይደለም። ከፊደል ጋር የሚያጣላ የትምህርት ዘዴ፣ በፍጥነት እንዲስፋፋ በመሪነት የሚቀሰቅሱ ሰዎች ራሳቸው፣ ይህንን አይክዱትም። እንዲያውም በኩራት ነው የሚናገሩት - ንባብ ምን እንደሆነ ሲገልፁ፣ “psycholinguistic guessing game” ይሉታል - (The Dyslexia Debate፤ Julian G. Elliott፤ Cambridge University፤ 2014፤ ገፅ 125)።
ፅሁፍን ማንበብ፣... በስሜት የሚመራ የግምት ጨዋታ እንዲሆን ማድረግ፣ … እናም በዚህ መኩራት?
እነሱ ቢኮሩበትም እንኳ፣... ውጤቱ ግን፣ ለብዙ ህፃናት ትልቅ ጠባሳ፣ ለብዙ ወላጆች ደግሞ በጣም አስደንጋጭ ሆኖባቸዋል። ለዚህም ነው፤ ይሄ ከፊደል ጋር የሚያጣላ የትምህርት ዘዴ፣ ከዛሬ 20 ዓመት ወዲህ፣ በምድረ አሜሪካና በአውሮፓ፣ “አይንህን ለአፈር!” ተብሎ የተተወው።
ተማሪዎችን እያደናገረ ለመሃይምነት ሲዳርጋቸው፣ ታይቷላ።
ግን መሄጃ አላጣም። እንደ ኢትዮጵያ ወደ መሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ተሸጋግሯል።
በዚህም የተነሳ በአሜሪካ፣ ከ3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ 90 በመቶ ያህሉ፣ ፅሁፍን አቀላጥፈው ያነብባሉ - በደቂቃ፣ ከ50 ቃላት በላይ የማንበብ ችሎታ አላቸው።
እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ግን፣ ፅሁፍን አቀላጥፈው ሊያነብቡ ይቅርና፣ ዝቅተኛውን ደረጃ ለማሟላት የሚችሉ ተማሪዎች፣ 10 በመቶ አይሆኑም። 90 በመቶ ያህሎቹ ተማሪዎች በደቂቃ 30 ቃላት ማንበብ አይችሉም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ፅሁፍ አንብበው መረዳት አይችሉም፡፡ ትምህርት ላይ በመመራመር የሚታወቁት Dr. Helen Abadzi እንደሚሉት፣ በደቂቃ ከ45 ቃላት በላይ ማንበብ የማይችል ተማሪ፣ አንብቦ መረዳት አይችልም፡፡ ይሄ ነው፣ “ዘመናዊ መሀይምነት”፡፡
ለዚያውምኮ፣ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋር ሲነፃፀር፣ የአማርኛ ፅሁፍ፣ ለንባብ በጣም የተመቸ ነው። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ... ሌሎቹም ቋንቋዎች ለንባብ ይመቻሉ፡፡ ... በንግግር ድምፅ እና በፅሁፍ መካከል፣ ብዙ የሚያምታታ ነገር የላቸውም። የእንግሊዝኛ ያህል፣ አያምታቱም። እናም፣ ለንባብ ትምህርት ይመቻሉ። ለዚህም ነው፣ በእንግሊዝኛ ላይ የምናየው “የስፔሊንግ” ውድድር፣ በአማርኛ ብዙም ትርጉም የማይኖረው። ፊደል ያወቀ ሰው፣ በንግግር የሚሰማቸውን ቃላት ወደ ፅሁፍ መቀየር፣... ወይም በፊደላት መግለፅ አይከብደውም።
የፊደል ትምህርትን እንደ ክፉ በሽታ የሚያንቋሽሽ የማስተማሪያ ዘዴ ተግባራዊ ሲደረግ ግን፣ የፅሁፍንና የንግግር ድምፆችን ያጣላቸዋል፡፡ እስካሁን ያልነበረ አዲስ በሽታ ጎትቶ ያመጣል፤ ዘመናዊ መሃይምነትን ይፈጥራል።
ጥፋቱ ይበልጥ አሳዛኝ የሚሆነው ደግሞ፣ 1ኛ እና 2ኛ ክፍል ላይ በአግባቡ ማንበብን አለመማር ማለት፣... የእድሜ ልክ ጠባሳ እንደማለት መሆኑ  ነው። በልጅነት ጊዜ፣ በቀላሉ የሚጨበጥ የንባብ ችሎታ፣ እድሜ በጨመረ ቁጥር፣ በጣም አስቸጋሪና አታካች ሸክም እየሆነ ይሄዳል። በሌላ አነጋገር፣ የሚሊዮን ህፃናት የወደፊት ህይወት ላይ ነው፣ እየተጫወቱ ያሉት - ትምህርት ሚኒስቴርና ዩኤስኤአይዲ።
አስገራሚው ነገር፣ መፍትሄው ቀላል መሆኑ ነው - መፍትሄው፣ ፊደልን በአግባቡ ማስተማር ነው - በቃ!
ትምህርት ሚኒስቴር፣ ዩኤስኤአይዲ እና ሌሎቹ እርዳታ ለጋሾች፣ ከፊደል የሚጀምር ትምህርትን የማይፈቅዱ ከሆነስ? አማራጭ ከጠፋ፣ … ጥንታዊውን የ“የኔታ” የፊደል ትምህርት ማበረታታት ይሻላል ይላል - የ2002ቱ ሰፊ ጥናት።
(...children are not fluent at letter identification after 2 years of schooling... This provides support for the types of church schools that Ethiopia has had in abundance in earlier times and that ensured children mastered the fidel...)
(ምናለፋችሁ፤ በየኔታ ዘመን፣ የፊደል ችግር አልነበረም። አሁን የምናየው የፊደል ችግር፣ የድሮውን እንድንናፍቅ የሚገፋፋ ነው።) Ethiopia Early Grade Reading Assessment; Data Analytic Report; August 31, 2010፣ ገፅ 31 (ሪፖርቱን የትምህርት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ላይ ልታገኙት ትችላላችሁ)።
መልእክቱ ግልፅ ነው። “የንባብ ትምህርትን በቃላትና በዓረፍተነገር እንጀምራለን” እያላችሁ በስካር መንፈስ መደናበርን በመተው፤ ፊደልን በቅጡ በማስተማር ብትጀምሩ፣ ጥሩ መፍትሄ ይሆንላችኋል የሚል ነው መልእክቱ።
ጥሩ ምክር ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? ሰሚ ጠፋ፡፡ ይሄውና፣ ከ2002 ዓ.ም ወዲህ 6 ዓመታት አልፈዋል። ግን ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ፣ እርዳታ ለጋሾቹ እነ ዩኤስኤአይዲ፣ የፊደልን ትምህርት እርም እንዳሉ ናቸው - እንደ ጠላት ነው የሚያዩት።
በዚህ ከቀጠሉ ደግሞ፣ ዘመናዊ መሃይምነት ይባባስ እንደሆነ እንጂ፣ ይሻሻላል ብሎ መጠበቅ፣ ቂልነት ይሆናል። ይህንንም የሚክዱት አይመስልም፡፡ በአዲሱ የጥናት ሪፖርት ውስጥም፣ በተስፋ-ቢስነት ዘመናዊ መሃይምነትን በፀጋ እንድንቀበል የሚያግባባ መልዕክት አቅርበውልናል።
የንባብ ችሎታን በአገር ደረጃ ሲሻሻል ለማየት የሚፈልግ ሰው፣ ብዙ አመታትን መጠበቅ እንደሚኖርበት ይጠቅሳል - አዲሱ ሪፖርት። (Early Grade Reading Assessment (EGRA) in Three Mother Tongues; Data Analytic Report; April 13, 2016፡፡)
ትውልድ አልፎ፣ ሌላ ትውልድ እስኪተካ ድረስ መጠበቅ አለብን?
የማስተማሪያ ዘዴን በመቀየር፣ የትምህርት ይዘትን በማሻሻል፣ የመማሪያ መፃህፍትን በማቅረብ፣... የተማሪዎችን የንባብ ችሎታ ማሻሻል አይቻልም በማለት ቁርጡን ይነግረናል - ተስፋ ቢሱ ሪፖርት። “ትውልድ አልፎ ትውልድ እስኪተካካ ድረስ ጠብቁ እንጂ፤ የፊደል ትምህርትን አልደግፍም” እንደማለት ነው።
እና ምን ይሻላል? ትምህርት ሚኒስቴር እና ዩኤስኤአይዲ ከጠመሙ፣ ምን ብናደርግ ይሻላል?
አያችሁ፤ … ወደ የኔታ መመለስ የሚለው ሀሳብ … ቀልድ አይደለም፡፡ ልጆችን ከፊደል ጋር አስተዋውቀው፣ የንባብን መሰረት የሚያስጨብጡ የኔታዎችን በጊዜ ብታፈላልጉ ይሻላል። ካልሆነም፣ የፊደል ገበታን በማዘጋጀት፣ ልጆችን ቤት ውስጥ ማስተማር!

Read 3455 times