Sunday, 26 February 2017 00:00

የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን በደጋማው አካባቢ የሚኖሩ ሁለት አርሶ አደሮች ነበሩ፡፡ የሚኖሩት በሳር ቤት ውስጥ ነበረ፡፡ ብዙ እርሻ ለብዙ ዓመታት አካሂደዋል፡፡ ነገር ግን ኑሯቸው ፈቀቅ አላለም፡፡ ሁሌ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡
አንድ ቀን ግን አንድ የተለየ ሁኔታ በመንደሩ ታየ፡፡ ሰው ሁሉ ጉድ አለ፡፡ ይኸውም ከሁለቱ አርሶ አደሮች የአንደኛው ቤት፣የሳር ክዳኑ ተነስቶ ቆርቆሮ ለብሷል፡፡ አጥሩም እስከ ዛሬ በእሾክና በጭራሮ ታጥሮ የነበረው በአጠና ታጥሯል፡፡ የውጪ በርም በቆርቆሮ ተሰርቶለታል፡፡ አገር ጉድ ያሰኘ ነገር ተፈጠረ፡፡
የሰፈሩ ሰው መነጋገር ጀመረ፡-
1ኛው - ይሄ ገበሬ ምን ተዓምር ወርዶለት ነው እንዲህ በአንድ ጊዜ ይሄን ሁሉ ለውጥ             ያመጣው?
2ኛው - ዘርፎ መሆን አለበት እንጂ እንዲያው የሰማይ መና ቢሆንማ ለእሱ ሲዘንብ ለእኛ እንዴት አያካፋም?
3ኛው - ያን ጎረቤቱን፣ አርሶ - አደሩን ጓደኛውን ለምን አንጠይቀውም?
4ኛው - ይሄ መልካም ሀሳብ ነው፤ አለና ተያይዘው ወደ ጎረቤትየው ሄዱ፡፡ ቤቱ ቁጭ ብሎ አገኙት፡፡
“ወዳጃችን፤ አንድ ግራ ያጋባን ነገር ተፈጥሮ ነው የመጣነው!” አሉት፡፡
“ምንድን ነው? ምን ችግር ተፈጠረ?”
“ችግር አይደለም፡፡ እንዲያው የማወቅ ጉጉት ይዞን ነው፡፡ ምናልባትም እኛ ዘዴውን ካወቅነው ሊያልፍልን ይችላል፣ ብለን ነው”
“እኮ ነገሩ ምንድን ነው?” አለ እሱም የማወቅ ጉጉት ይዞት፡፡
“ይሄ ጎረቤትህና ጓደኛህ እንዲህ ባንድ ጀንበር አልፎለት፣ ቆርቆሮ ጣራ፣ የአጠና አጥር ለመስራት የቻለው፣ ምን አግኝቶ ነው? ልጆቹ ገንዘብ ላኩለት እንዳንል፣ ገና እነሱም ስደት ላይ ሆነው ለራሳቸውም በቂ ያላገኙ ናቸው፡፡ በውርስ አገኘ እንዳንል በቅርብ የሞተ ዘመድ የለውም፡፡ ሚሥጥሩ ጸነነብን፡፡ የምታውቀው ነገር ካለ ንገረን፡፡ ይሄ ዘመን አመጣሹ ሙስና የሚሉትም ከሆነ ንገረንና፣ ቁርጣችንን አውቀን ቁጭ እንበል!”
ጎረቤትየውም፤
“ወገኖቼ፤እኔም እንደናንተ ግራ ገብቶኝ ትላንትና ጠይቄው፣ ዛሬ እነግርሃለሁ ብሎ ቀጥሮኛል፡፡ ስለዚህ ማምሻውን እነግራችኋለሁ” አላቸውና ተለያዩ፡፡
የተሻሻለውን ገበሬ ያልተሻሻለው ገበሬ በቀጠሮው መሰረት አገኘው፡፡
“እህስ ወዳጄ፤ የብልፅግናህ ሚሥጥር ምንድን ነው?” አለው በቀጥታ፤ ወደ ፍሬ ጉዳዩ ገብቶ፡፡
“ምን መሰለህ ወዳጄ፤ ምንም ምስጢር የለበትም፡፡ የደጋ ወንድሞቻችን ገበሬዎች የማረሻ፣ የዶማ፣ የማጭድ፣ የአካፋ ችግር እንዳለባቸው ተገነዘብኩ፡፡ ስለዚህ በሬዎቼን ሸጥኩና ቆላ ወረድኩ፡፡ ያለ የሌለ ብረት ሰብስቤ ማረሻ በል፣ ዶማ በል፣ ማጭድ በል፣ መኮትኮቻ፣ መንሽ፣ ድጅኖ … ምኑ ቅጡ --- ቁጭ ብዬ አሰራሁ፡፡ እግረ መንገዴን ቀጥቃጩ በምን ዘዴ እንደሚቀጠቅጥ፣ በምን ዘዴ ቅርፅ እንደሚያወጣ ተማርኩ። በሁለተኛ ዙር ቆላ ወርጄ ያመጣኋቸውን ጥቂት ብረቶች እኔው ራሴ ቀጥቅጬ፣ ቀርጬ አበጀኋቸው፡፡ ከዚያ ሁሉንም ዋጋ ተምኜ፣ ገበያችን ላይ ቸበቸብኳቸው! ይሄው ነው ጉዳዩ!”
ጎረቤትየው አመስግኖት፤ “ወይ ነዶ” እያለ፣ በቀጥታ ወደ ቤቱ ሄዶ፣ በሬዎቹን ፈትቶ ገበያ አወጣቸው፡፡ ሸጧቸው ተመለሰ፡፡ በቀጣዩ ቀን ገንዘቡን ይዞ ማልዶ ቆላ ወረደ፡፡ ቆላ ያለ፣ አንድ ቁራጭ ሳይቀረው፣ ያገሩን ብረታ ብረት ሁሉ ገዛ፡፡
ብረቶቹን ተሸክሞ የደጋውን ዳገት ተያያዘው፡፡ ሆኖም ገና የደጋውን ወገብ ሳያልፍ፣የራሱ ወገብ ቅንጥስ አለና ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡
የሰፈር ሰዎች ወደ ቆላ ሲወርዱ ወድቆ አገኙት! በድንጋጤ፤
“ምነው አያ፤ ምን ሆነህ ነው?” ብለው ጠየቁት፡፡
“አይ ወዳጆቼ! በእኔ የደረሰ አይድረስባችሁ! ያ ወዳጄ ጎረቤቴ ገበሬ፣ የሰራኝ ሥራ፤ ሥራ እንዳይመስላችሁ። አለ እያቃሰተ፡፡
መንገደኞቹም፤ “ምን አደረገህ?” አሉት በድንጋጤ፡፡
እሱም፤ “አዬ! ትርፉን ብቻ ነግሮኝ፣ መከራውን ሳይነግረኝ!!” አላቸው፡፡
*         *       *
በአንድ ጀንበር ባለጠጋ መሆን አይቻልም፡፡ በአንድ ጀንበር ከገበሬነት ወደ ነጋዴነት መለወጥም ዘበት ነው፡፡ ከነጋዴነትም የነጋዴዎች ሁሉ የበላይ ቱጃር መሆን አይቻልም፡፡ ይሄ ተዓምር ሊፈጠር የሚችለው በሙስና ብቻ ነው! ሙስና ደግሞ ጊዜ ይውሰድ እንጂ የሚጋለጥ ነገር ነው! ዛሬ በሀገራችን በሀቅ የሚከበር፣ በሰለጠነው መንገድ የሚበለፅግ ነው የጠፋው፡፡ ይሄን መስመር ለማስያዝ እንዳይቻል፣ ትርፉን ብቻ እያሰቡ፣መከራውን ማሰብ የማይሹ መንግሥታዊ፣ ነጋዴያዊ፣ ደላላዊ አካላት እና ረብ ያለው ህጋዊ ህልውና የሌላቸው ወገኖች፤ የአሻጥር መረብ ሰርተው፣ ከራስጌ እስከ ግርጌ ዘርግተውና እግር ከወርች አስረው፤ “ለውጥ የሚባል አይታያትም!” እያሉ ይፏልላሉ፡፡ የገባውና ጨዋታው ውስጥ የሌለበት አካል ያስፈልጋል!  
የተማረ የሰው ኃይል ነገር ዛሬም አሳሳቢ ነው፡፡ በተለይ ዋና ዋና የምንላቸውን ምሁራን እያጣን ባለንበት በአሁኑ ወቅት፤ ‹‹የተተኪ ያለህ!›› የሚያሰኝ ጩኸት በየደጃፋችን እየተሰማ ነው፡፡ አሉን የምንላቸው ፕሮፌሰሮች እያለቁብን ነው! እንደ ዋዛ፣ ለዓመታት ያፈራናቸው አዕምሮአውያን፤ይቺን ዓለም እየተወ እያለፉ ነው! የቀሩንን ምሁራን ጠንቅቀን መጠበቅ አለብን፡፡
አንጋፋ ችግሮቻችንን ቀዳሚ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የበላይ ነው! ማንም ከዚያ በላይ እንዳልሆነ እናሳይ ዘንድ ተግባራዊ ትግል እናካሂድ፡፡ በዱሮ ዘመን Bureaucratization of the party የሚል ችግር ነበር፡፡ የፓርቲ አባላት በቢሮክራሲው መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ቢሮክራሲውን ፓርቲ አደረጉ፤ፈላጭ ቆራጭ ሆኑ እንደ ማለት ነው፣ የግዢና የጫረታ ሥርዓት ወገናዊና ህግጋቱን የጣሰ መሆኑ ዜጎችን እጅግ ያሳዝናል፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበር ጀምሮ በአግባቡ ተመሥርተው፣ በአግባቡ መደራጀትና መጠናከር የሚሹ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አቅል - እስከ ማሳጣት መድረስ አሳፋሪ ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶች አገርን የገንዘብ ሰለባ  ወደ ማድረግ የሚንደረደሩ ናቸው፡፡
 በገዢው ፓርቲ በኩል የታየው የህዝብን ብሶት የመረዳት አዝማሚያ ደግ ነው፡፡ መፍትሄ ካልተገኘ ግን ችግር መዘመር ብቻ ነው! መልካም አስተዳደር እንደ ሰበብ ሳይሆን እንደ ትንተናዊ ምክን፣ እንደ ችግር መፍቻ፣ በትክክል ሥራ ላይ ማዋል ይገባል፡፡ የትምክህትም ሆነ የጠባብነት ድባብ ጥላውን እያጠላብን፣በሀቅ የምንቀሳቀስበት ሜዳ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በዚህ ሁሉ ውጣውረድ መካከል ዕርቅና ድርድር በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ መካከል ይደረጋል ስንል፤ በአዕምሮአችን የሚያቆጠቁጡ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ‹‹የትም አይደርሱም!›› ዓይነት አመለካከት አስወግደናል ወይ?”፣ ‹‹ከእኛ ጋር እኩል ከተቀመጡ አይበቃቸውም ወይ?›› ከሚል ዕብሪት ተላቀናል ወይ? ‹‹የጊዜ ጉዳይ ነው፤ እንሠራላቸዋለን!›› ከሚል ሴራዊ አካሄድ ተገላግለናል ወይ? ‹‹ተልባ ቢንጫጫ፣ ባንድ ሙቀጫ›› ከሚል ትምክህት ነፃ ወጥተናል ወይ? እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ዕሳቤዎች ካልተወገዱ፣ ‹‹የማይተማመን ባልንጀራ፣ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል›› የሚለው ተረት፣ አሁንም አለ ማለት ነው፡፡ ይታሰብበት!!

Read 7054 times