Sunday, 26 February 2017 00:00

ለቅበላ አልጋ በቅድሚያ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(17 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እኔ የምለው…ሰሞኑን እኛ ሳናውቀው ‘በውስጠ ታዋቂ’ የወጣ አስገዳጅ መመሪያ ነበር እንዴ! የቅበላው ሰሞን…አለ አይደል… “በዛሬው እለት ከቤቱ ውጪ ያላደረ…” ምናምን  የተባለ ይመስል ነበራ! ግራ ገባን እኮ… ከክልል አካባቢ አዲስ አበባ ለሥራ የመጡ ሰዎች እንኳን ማደሪያ አልጋ ማግኘት አቅቷቸው ሲንከራተቱ እንደነበር አንዲት ወዳጄ ስትነግረኝ ነበር፡፡ ጭራሽ ‘በሪዘርቭ ይያዝ’ ጀመር! ‘ቫለንታይን ቀን’ በሚሉት እለት ድፍን ከተማዋ አንድ ግዙፍ መኝታ ቤት ሆና እንዳላደረች በቅበላም ተደገመና አረፈው!
እናማ…‘ለቅበላ፣ አልጋ በቅድሚያ’ ዘመን ደረስንላችሁ!
ግዴላችሁም… ለከርሞ ደግሞ ‘ሰልፉ’ ከሥጋ ቤት ወደ መኝታ ቤት ሳይቀየር አይቀርም፡፡ “በቅበላ ቅዳሜና እሁድ ቀደም ብለው አልጋ ለሚይዙና በቡድን ለሚመጡ ቅናሽ ይደረጋል…”  ምናምን የሚል ማስታወቂያ ሳይወጣ አይቀርም፡፡
እናማ…መቼም ባልና ሚስት የሚሆኑት ያው ቤታቸው ነው፡፡ በዘንድሮ የአልጋ ዋጋ… “እስቲ ዛሬ የሆነ ሆቴል ምናምን እንደር…” የሚባባሉ ባልና ሚስት ካሉ የሆነ ኒሻን ሜዳልያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ‘ስለዚህ’ ቢባል… ስለዚህማ የከተማዋን አልጋዎች የያዙ ‘ጥንዶች’ እነማን እንደሆኑ ልብ ይባልማ!
እኔ የምለው… ይሄ ሁሉ ሲደረግ አማቶች ሁሉ የት ሄዱ! ጓዳ ገብተው የመሶብ እንጀራ ከመቁጠር ፔኒስዮን ሄደው የልጆቻቸው ባሎች ከእነማን ጋር እንደሆኑ አይሰልሉም! ቂ…ቂ…ቂ…
ሀሳብ አለን…
ቀጠሮ አክብረሸ አትመጪም ወይ
ፍቅር የጋራ አይደለም ወይ
የሚለው ግጥም ይለወጥልንና
የቅበላ እለት አትመጪም ወይ
አልጋው ተይዞ ያልቅ የለም ወይ
ይባልልንማ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…‘ለቅበላ፣ አልጋ በቅድሚያ’ ዘመን ደረስንላችሁ!
ደግሞላችሁ… ‘እንደ ውሀ ነው የፈሰሰው’ አሉ! ለነገሩ በቀን ሀያ አራት ሰዓት፣ በወር ሠላሳ ቀን የሚጠጣባት ከተማ ሆናለች፡፡
እኔ የምለው ገና ከአሁኑ እንዲህ የሆንን…አለ አይደል…‘መካከለኛ ገቢ’ ስንደርስ ምን ልንሆን ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
አንዱ የቸገረው ምን አለ መሰላችሁ…     “በእኛና በግመሎች መካከል ያለውን ልዩነት ታውቃላችሁ? ግመሎች ውሀ ሳይጠጡ ለሰባት ቀናት መሥራት ይችላሉ፣ እኛ ደግሞ ያለ ሥራ ሰባት ቀን መጠጣት እንችላለን፡፡”
የምር ግን…ለእንዲህ አይነት ጊዜ ፈራንኩ ከየት እንደሚመጣ ግራ አይገባችሁም!
ሀያ አራት ሰዓት የየቡና ቤቱ በረንዳና ውስጡ በሰው እየተጨናነቀ የሚጠጣባት ከተማ ወዴት እያመራች እንደሆነች ግራ አይገባችሁም!
የቢራ አምራቾች ሁሉ ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ እያሉ፣ ይሄ ሁሉ የአሥራ አራት ዓመት ታዳጊ በመጠጥ ኃይል ሲንገዳገድ ጠያቂ አለመኖሩ ግራ አይገባችሁም!
ስሙኝማ…መጠጡ በጠርሙስና በብርጭቆ መቅረቡ ቀርቶ ወይ በባንቧ ይሁንልንማ! ሰዋችን ‘ይጠጣዋል’ ነው የምላችሁ፡፡ እንኳንስ ሰበብ ተገኝቶ… እንዲሁም የአጠጣችን ነገር በቅርብ ጊዜ ከዓለም እንኳን ባይሆን ቢያንስ፣ ቢያንስ ‘ከአፍሪካ አንደኛ ሳያደርገን አይቀርም፡፡  
አሁን አሁንማ አለመጠጣት ‘ከማህበራዊ ኑሮ ውጪ’  የሚያደርግ ይመስላል፡፡ አልጠጣም ማለት… “ጎሽ… እንዲች ብለህ መጠጥ የሚሉት ነገር እንዳትለምድ…” ከመባል ይልቅ ‘አፍ የሚከት’ ሆኗል።
“ቢራ ጠጣ…”
“አመሰግናለሁ፣ ግን ይቅርብኝ…”
“አንድ ጠርሙስ ብትጠጣ ምን ያደርግሀል!”
“በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ግን በቃኝ…”
“ስማ፣ ምንም አልኮል የማይቀምስ ሰው እንኳን ቢራ ይጠጣል…”
“አይ እኔ ስለማልጠጣ ነው…”
እና ዘወር ሲል…አለ አይደል… “ይሄኔ እኮ ቤቱ ሦስት ገንቦ ቅራሪ አስቀምጦ ነው…”
“አሁን አንተ…”
እኔ የምለው…በቃኝ ማለት በቃኝ አይደለም እንዴ!
ደግሞላችሁ… ዘንድሮ ችግሩ ምን መሰላችሁ… “ከብት እነዳ ብዬ፣ ከሰው እኖር ብዬ…”  ብላችሁ ያለውዴታችሁ አንድ ጠርሙስ ጨርሳችሁ አንዱን ብታጋምሱ  ያው ‘ጋባዣችሁ’…
“ትናንት ከእኔ ጋር ቢራውን ሲገለብጥ አይደለም እንዴ ያመሸው! ሰውየው እኮ ስፖንጅ ነው…” ምናምን ሊላችሁ ይችላል፡፡ ሌላኛውም “ይሄኔ ሚስቱም በር ዘግታ ዳግም አረቄዋን ስትለጋ ትውል ይሆናል…” ሊል ይችላል፡፡
ስሙኝማ…‘ፌክ ኒውስ’ እያሉ እነ ሲ.ኤን.ኤንን መከራ የሚያበሉት የአሜሪካው ሰውዬ…እንኳንስ ስለ እኛ አልሰሙ! አይደለም ‘ፌክ ምናምን’… የፈለገው መዝገበ ቃላት ቢያገላብጡ እኛን ‘ገላጭ’ ቃል ማግኘት ሳያስቸግራቸው አይቀርም!
እናላችሁ….ዘንድሮ ችግሩ ‘እንደ ሰዉ’ ካልሆናችሁ …አለ አይደል… ልዩ ሰው መሆንየፈለጋችሁ ያስመስሉታል፡፡
“ስሚ ብላክ ፎረስት ኬክ ነገር እዘዢ…” የተባለችው እሷዬዋ
“እኔ እኮ ኬክ አልበላም…”  ካለች…በቃ ኬክ አትበላም፡፡
“እሷ ማን ሆነችና ነው ኬክ የማትበላው!” ምናምን ብሎ ጭቅጭጥቅ ምንድነው!
“በአውቶብስ መሄድ አልወድም…” የሚል ሰው አንድ ሺህ አንድ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ “እሱ ማን ሆነና ነው በአውቶብስ የማይሄደው! ተረከዙ የእርከን እርሻ እስኪመስል በእግሩ ሲያስነካው እንደኖረ የማናውቅ መሰለው!” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
“ጠይም ሴት አልወድም የምትለው…ፈረንጅ መሆንህ ነው!” ምናምን ብሎ ጭቅጭቅ አሪፍ አይደለም፡፡
በቃ “ጠይም አልወድም” ማለት አልወድም ነው። ቂ…ቂ…ቂ
አሜሪካ…አለ አይደል… “ከዛሬ ነገ የትረምፕ ሰዎች መጥተው በሬን አንኳኩብኝ…” እያሉ ስጋት ላይ ያሉ ወዳጆችን እኮ የሚያውቁት እንኳን ተርፎ አልጋ በሪዘርቭ ልንይዝ…ቲማቲም ‘አንድ ኪሎ፣ ግማሽ ኪሎ’ እያልን ሳይሆን ‘አንድ፣ ሁለት’ እያልን በጣታችን ቆጥረን እንደምንገዛ ነው፡፡ እናማ… ማደሪያ ጎጆ ሳናጣ አልጋ ለቅበላ እያስያዝን፣ የበጀት ድጎማ ጥያቄያችን ግን ‘ዓለም በቃኝ’ ለማለት አንድ ሐሙስ የቀረን ነው የምናስመስለው፡፡
“መቼም ኑሮ እንዴት እንደከበደ አልነግርህም፡፡ አንተ እዛ ሆነህ ከእኔ የበለጠ ሳታውቀው አትቀርም። ቲማቲም እንኳን ስንት እንደገባ ታውቃለህ!… ወጣ ብለህ አንዲት ሸሚዝ ልገዛ ብትል ዕቁብ ሊደርስህ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች በካኔቴራ ወዲህ፣ ወዲያ ስል ሲያያኝ መዘነጤ ይመስላቸዋል፡ ጉዴን የማውቀው እኔ ነኝ፡፡”
“ከመክሳቴ የተነሳ ከሩቅ ብታየኝ የተሰበረ የመጥረጊያ እንጨት ነው የምመስለው…” ‘ፕሮፋይል’ ፎቶው ላይ እኮ በውፍረት ጧ ሊል ደርሷል!
እናማ…‘ለቅበላ፣ አልጋ በቅድሚያ’ ዘመን ደረስንላችሁ!
ስሙኝማ…እግረ  መንገዴን… የዘንድሮ ‘የፎቶሾፕን’ ውለታ ተናግረንም አንጨርሰው፡፡
“ምን አይነት ደስ የሚል ሰው መሰለሽ…”
“ማ! ያ ስሙኝማ ምናምን እያለ የሚቀባጥረው!”
“ታዲያማ…”
“አሁን ማን ይሙት እሱ ፊት እንደው እህልስ ይቀመሳል!”
“የፌስቡክ ፕሮፋይል ፎቶውን ብታዪው እንዲህ አትዪም ነበር…”
አሪፍ አይደል! (ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ምን አለ መሰላችሁ… “ዓለም ላይ ‘አርፈህ ፌስቡክህ ላይ አተኩር…’ የምትል እናት ያለችው ብቸኛው ሰው ማርክ ዙከርበርግ ነው፡፡”)
እናላችሁ …በየቀኑ ስለኑሮ የምናማርረውና እነ ‘ቫለንታይን ቀን’ና እነ ‘ቅበላ’ ሲመጡ… አለ አይደል… ‘ዓለም ዘጠኝ’ አባባላችን ለትንታኔ እንኳን የሚያስቸግር ሆኗል፡፡ ሀሳብ አለን… ‘ለቅበላ፣ አልጋ በቅድሚያ’ በሚል ‘መሪ ቃል’ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ይካሄድልን፡፡ ወይንም ‘መሪ ቃሉ’ን … ‘ቅበላ፣ ከሥጋ ቤት እስከ መኝታ ቤት’ ማለትም እንችላለን፡፡ የዛሬ ዘጠኝ ወር ጥቅም ላይ የሚውሉት ‘የልደት ሰርተፊኬቶች’ ብዛት ሳስበው የማተሚያ ቤት ባለቤቶች አስቀኑኝማ! ቂ…ቂ…ቂ…  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6786 times