Saturday, 25 February 2017 13:05

ታሪክ ያለው የታሪክ ሰው

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

የአገሬ ህዝብ ሆይ! አንዴ ጆሮህን አውሰኝ
የአገሬ ሰው አንዴ አዳምጠኝ
አደለም አንቶኒ እንዳለው
ፓንከረስትን ልናወድስ እንጂ አልመጣንም ልንቀብረው!
ታሪክ አለው የታሪክ ሰው!
ሰው አጥተናል ተራራ- አከል፣ ሰው አጥተናል ከአገሬ
ቋንቋም ሳይጠፋ አይቀር ከቶ፤ ለደረሰው እጦት ዛሬ!
የሚባል ምንድን ነው ከቶ፤ በልምድም ሆነ በባህል
ዘመናዊም ሆነን ብንል፤ ብናስበው በሥልጡን ውል
አንድ የታሪክ ባለ ገድል
ታሪክ ሲፅፍ ኖሮ ራሱ፣ አሁን ታሪክ ሆነ ስንል
የት ነው የፍልስፍናው አቅል?
ታሪክስ ወደፊት እንጂ፣ ጥንድ የኋሊት ይመለሳል?
እኔ ጭንቀት አለኝ ዛሬ፣ እስቲ እንጠያየቅ የሚል፡፡
‹‹ለእረፍት ከሞት በኋላ፣ ጊዜ ይኖራል›› ያለ
ዘመን ሊገል ያልታከተ፤ ለዓለም ሲሣይ ያልማለለ
ይሄው ዛሬ ጊዜ አገኘ፣ የዕፎይታ ጊዜን ታደለ!
ላሊበላና ዕንባን እኩል፤ ልቡ ውስጥ ያንከባለለ
አክሱም ላገሩ እንዲበቃ፣ እንዳገሬው የታገለ
ለአገሬ ቅርሶች መመለስ፣ አቃቤ-ንዋይ የሆነ፤
እንደ እናቱ የህዝብ አንጀት፣ ጧት ገብቶት የሠለጠነ፤
ያቀደ ሰው ነበር ብዬ፤ ባስብ፣ ሊኖር ያመነውን
ታሪክ-ሠሪ ታሪክ-ጣፊ፣ ይሆናል እንኳ ባንል
በአለም ላይ ታላቅ ገድል፣
ታላቅ ስምን መታደል፤
ታሪክን ሲፅፉ ኖሮ፣ ታሪክን ራሱን ማከል!
ግናሳ ምንስ ቢሆን ምን፤
ታሪክ- ጣፊ ታሪክ ሲሆን፣ እንዴት አየን ብለን እንመን?
የ’ውን ታሪክ ሢሠራ፣ ሲፅፍ ሲከትብ ብዙ ኖሯል
የተሰራም ታሪክ ሲያርቅ፣ ጊዜውን በጊዜ አክርሟል
ጊዜውን በጊዜ አክሟል!!

መፃፍ ዳግም መፃፍ እንደሁ፣ መላ-ነገሩን ዱሮ አውቋል
ሆኖም እስከድሜው ጫፍ ድረስ፤ ከቶም ብዕሩን፣ ላፍታም ሳያሰንፍ
ይኸው ታሪክ ሲፅፍ ኖሯል፣ ያውም እስከታሪክ አፋፍ!
አረጀ ሸበተ አይባል፣ የታሪክ የብዕር ጀግና
ያን መሳይ የዕውቀት ናሙና
ዛሬ በአካል ወድቆ፣ ሥጋውን አይተናልና
ምን እንፃፍ ለእሱ ል’ልና
ተፃፈ እምንለው ቃል፣ በእድገታችን ተተምኖ፣
የተፈጥሮ ግዴታችን፣ ሁሉም ግድ ማለፍ ሆኖ
ምንስ እንተውለት ከቶ፣ ለነገ ሰው ታሪክ መኖ
ሰው ብናጣም በየለቱ፣ እኛም ብናጣ እንኳ መቅኖ
ይህ ጀግና ሰው ነበርኮ፣ የታሪክ ህልው መስኖ!
በዚህ ቢባል በዚያ መንገድ፣ ታሪክ አይቀርም ባክኖ፡፡
የዚህ ታላቅ ሰው መቃብር፣ እኛ ውስጥ እንጂ ምድር አደል
ሳንወድ ሥራው እያዘዘን፣ ሁሌ ሲታደስ ይኖራል!!
ከቶም ባዕድ የሚባዕድ፣ ልቡ ሲባዕድ ነውኮ
በጧት ራሱን ከኛ አገር፣ ያቀሰሰን ልብ-ምርኮ
እንዴት ይጠር ልንለው ነው፣ የህልውናውን ለኮ?
ከዘር ማን ዘር ተሳስቦ፣ ኢትዮጵያን ያነገበን ሰው
እስከናቱ ለኛ ደሙን፣ የገበረን የታሪክ ሰው
የአበሻ ደም እንጂ ሌላ፣ ኬት አምጥተን ልንሰጠው ነው?
ሞተ ቢሉን እንዴት እንመን፣ ተግባር በውል እያኖረው?
ውስጣችን ከማኖር በቀር፣ እኛስ ምርጫችን ምንድን ነው?
የሀገሬ ሰው አድምጠኝ
አንዴ ጆሮህን አውሰኝ
የሰው ልጅነቱን እመን፣ እንጂ የዘር ግንድ አታውጅ
ከምታየው ነገር በላይ፣ የለህምና ቁም አስረጅ
ተግባር ይሁን የዕምነትህ ልክ
ከዚህ በላይ ባለታሪክ፣ ሊነግርህ አይችልም ታሪክ!!
ባለታሪክ አለው ታሪክ
አፈር ውስጥ አይደለም ከቶ፣ ዛሬ ቀብሩ እሚፈጸመው
ዝንተ- ዓለም በክብር የሚኖር፣ እኛና ኢትዮጵያ ውስጥ ነው!!
            የካቲት 12 ቀን 2009 ዓ.ም
           (ለሪቻርድ ፓንክረስት መታሰቢያ፤ለቤተሰቡ መፅናኛ)

Read 891 times