Saturday, 25 February 2017 13:06

እንደ መግቢያ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

ነቢይ መኮንን
የሰው ልጅነቱን እመን፣ እንጂ የዘር ግንድ አታውጅ
ከምታየው ነገር በላይ፣ የለህምና ቁም አስረጅ
ተግባር ይሁን የዕምነትህ ልክ
ከዚህ በላይ ባለታሪክ፣ ሊነግርህ አይችልም ታሪክ!!
ባለታሪክ አለው ታሪክ
አፈር ውስጥ አይደለም ከቶ፣ ዛሬ ቀብሩ እሚፈጸመው
ዝንተ- ዓለም በክብር የሚኖር፣ እኛና ኢትዮጵያ ውስጥ ነው!!
የካቲት 12 ቀን 2009 ዓ.ም
(ለሪቻርድ ፓንክረስት መታሰቢያ፤ለቤተሰቡ መፅናኛ)

“እረ ሰው እረ ሰው
ዐይኔን ሰው ራበው”!
- ዮፍታሔ ንጉሤ
ልበ - ጥኑው ኩሩ
እራሱን የሆነ፣ እራሱን የኖረ
ከአድር - ባይ ሁላ፣ ይሻላል ካልኖረ!
ምንም ይመን ምንም፣ ባቋሙ የፀና
ለደሀም የቆመ፣ በንጹህ ሕሊና
ለአገሩ እያለመ፣ ጎባጣን ያቀና
ሺ ጊዜ ይበልጣል፣ ከሚልመጠመጠው
ለሀብታሙ መክሊት፣ ሎሌነት ካደረው!
ለጨላዋ ትንፋሽ፣ ራሱን ከሸጠው!
ከዘመን ይሁዳ፣ ከዘመን አድር - ባይ
ይሻላል ድሀውን፣ በቅንነት እሚያይ!
ሸቅጦ ሸውሽዎ፣ አቋም እንደሸቀጥ
በየኳሱ ግጥሞያ፣ ማሊያ ሲለውጥ
ላሸነፈው ሲያረግድ፣ ደረቱን ሲደቃ
እንደጎይቴ ድርሰት፣ ነብሱን ሽጦ እንደዕቃ
የጭቁኑን ላብ - ወዝ እየመገመገ
እያደገደገ
እያስደገደገ
እያለተለተ
እያስለተለተ
ከሀቁ እየራቀ፤
አገሩን፣ ህዝቦቹን፣ ራሱን ያስነጠቀ
ሳይኖር እየኖረ፤
ለከበርቴው ሲሳይ፣ ለንዋይ ካደረ
ምንኛ ታድሏል፣ የዕምነቱን የኖረ
እራሱን የሆነ፣ እራሱን የኖረ!
ቀናሁብህ ጋዙ!
ሁሉን በመቻልህ፣ እስከነመዘዙ!
ቀናሁብህ ገብሩ፣ ዘመኔን አሻርከው፣
… ዘመኔን አከልከው፣
ያ ነበር እውነቱ፣ነገርህ ለገባው!
የኖረ ኖሮታል፣ የቆጨ ይቆጨው!
ወትሮም የአቋም ነበር፣ ዛሬም ያው አቋም ነው
መካከል ላይ ጠፍቶ፣ አገሬን የራበው!
ያለነገር አደል፣ ዕውነትን ፍለጋ
ኢሮብን አቋርጠህ፣ የወጣህ ጋራውጋ!
ያለነገር አደል፣ ገብሩ ጋዝ የሆንከው
ሰው ብቻ’ኮ አይደለም፣ ትግልም ደም አለው!
ማርክስ እንዲህ ገጥሟል፣ ቋንቋውን ልዋሰው፤
ያንተም ህይወት ያው ነው፡-
“እኔ መች ፈልጌ፣ ህይወት ያለችግር
መንፈሴስ መች ሽቷት፣ ራሷ ግርግር
አልፈልግም ኑሮ፣ የተሞነጨረች ባሳረኛ ብዕር፡፡
ለታላቁ ዓላማ፣ ለሰው መልካም ዕድል
ህይወቴ ትሞላ፣ ትሁን የትግል ድል!”
ጋዙ ጓድ ፈለጌ!
አይቀሬ ሀቅ ነው፣ አይገፉት ድንጋጌ
ጥንትም ወርቅ በእሳት፣ እኛም በትግላችን፣
በሐረግህ ባረጌ፤
አመፅ ውሉን አይስት፣ ከራስጌ እስከ ግርጌ
በጋዝህ በጋዜ፣ ከግርጌ እስከ ራስጌ
ጭቁኑ ሲያሸንፍ፣ አኪሩን ለውጦ
“የጠፋው በግ” ሲገኝ፣ ዕውነቱን ተፋጦ
የዳጠ ተድጦ፤
ገብሩ አትጠራጠር፣ ያሰብከው ይሞላል
ካፒታል ግፉ አይቀር፣ ግን ግፉም ይገፋል
አሮጌው ያፈጃል፣ አዲስ ይወለዳል
መቼም ይሁን መቼ፣ አዲስ ያሸንፋል!!
    (ለደፋሩና ለልበ - ጥኑው ማርክሲስት፣ ለገብሩ መርሻ (ለጋዙ)፣ ዕውቀትን ለሚያከብሩ፣ እና ለጓዶቹ)

Read 865 times