Print this page
Saturday, 17 March 2012 10:36

የእግዜር “ሱፐር ማርኬት”

Written by  ዳዊት ስዩም
Rate this item
(2 votes)

ከቤቴ ጓሮ ከሚገኝ ድንጋይ ላይ ተቀምጬ የፀሐይን መጥለቅ እያየሁ ተመስጫለሁ፡፡  እደግመዋለሁ ተመስጫለሁ ነው ያልኩት፤ እንደ አንዳንድ ደራሲያን በሀሳብ ባህር ሰምጫለሁ፤ አልወጣኝም፡፡ በሃሳብ መስመጥ ልክ እንደ ዲቃላ ባቄላ፣ እንደ ድንጋይ፣ እንደ ብረት፣ ወለሉ ላይ ሄዶ መዘርፈጥ ሲሆን በሃሳብ መመሰጥ ግን ዙሪያ ገባውን መቃኘት፣ ማስተዋል፣ መሽከርከር፣ መብረር ነው፡፡ (ትርጉም፡- ያልታተመው የራሴ መዝገበ ቃላት ገፅ 141…)

እናም በተመስጦዬ ውስጥ እንደ ፒያሳ በመሰለ ጐዳና ላይ እጄን ኪሴ ውስጥ ከትቼ እየተራመድኩ ነው የጐዳናው መብራት ወርቃማ ብርሃኑን ይረጫል፡፡ በጐዳናው  በስተቀኝ በኩል አንድ ሱፐር ማርኬት በር ላይ ሰልፍና ግርግር ይታየኛል፡፡ ደግሞ ምን ተገኘ? የዳቦ ነው የዘይት … በምሽት ወረፋ የተያዘው? አበሻ መቼም ሰልፍ ይወዳል፡፡  አንዳንዱ’ኮ የሰላማዊ ሰልፍ አምሮቱን በዘይት፣ በዳቦ፣ ብቻ በተገኘው ሰልፍ የሚወጣ ነው የሚመስለው አልኩኝ፤ ለራሴ በፈጠርኩት ተረብ ለመሳቅ እየዳዳኝ፡፡ “የእግዜር  ሱፐር ማርኬት” ይላል በሩ ላይ በወርቃማ ቀለም የተፃፈ ፅሁፍ፡፡ ወይ ጉድ ደግሞ ብሎ ብሎ እግዚአብሔርም ንግድ ጀመረ፡፡ ዘንድሮ ንግድ ነው የሚያዋጣው ልጄ! እንደ እኛ አንድ ቀን ተቀብሎ ሃያ ዘጠኝ ቀን ከማሰብ! ይሄንንማ ማየት አለብኝ አልኩኝ፤ ወደ   ሰልፈኛው እየተቀላቀልኩኝ፡፡ ተራዬ ደረሰ፡፡ በር ላይ ያለው መልአክ በሚያጠግብ ፈገግታ ወደ ውስጥ ጋበዘኝ፡፡ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ እንደ በሩ ጠባብነት ሳይሆን ውስጡ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ፈረንጆች ሞል (Moll) እንደሚሉት አይነት፡፡ አንድ የሚያብረቀርቅ ነጭ ልብስ የለበሰ መልአክ ወደኔ መጥቶ፤

የምትፈልገውን ንገረኝና እኔ ወዳለበት እወስድሃለሁ፤ ሰፊ ስለሆነ እንዳይጠፋብህ ብዬ ነው አለኝ በትህትና፤

“ምን እንደምፈልግ አላወኩም፤ ምን ምን እንደሚሸጥ ተዛዙሬ ለማየት ፈልጌ ነበር አይቻልም እንዴ?” አልኩት በተምታታ ስሜት ውስጥ ሆኜ፤

“በጣም ጥሩ ለሥራ አስኪያጁና ለባለቤቱ ለእግዚአብሔር እነግርልህና የሚያስጐበኝህ መልአክ እንዲመደብልህ አደርጋለሁ፤ እባክህን እዚሁ ጠብቀኝ” አለኝና በብርሃናዊ ፍጥነት ከአጠገቤ ተሰወረ፡፡

“እንዲህ ነው እንጂ መስተንግዶ!” አልኩኝ በልቤ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከወደ ጀርባዬ በኩል አንድ ጣት ትከሻዬን ነካ አደረገኝ፤ ዞር አልኩኝ፡፡ ግርማ ሞገሱ በቃላት ለመግለፅ የሚያስቸግር፣ ፂሙ እንደ በረዶ ነጭ የሆነ ሽማግሌ በፈገግታ እየተመለከተኝ ነው፡፡  ረዥም ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሷል፡፡ በጭንቅላቱ ዙሪያ የሚያስደንቅ ብርሃን አለ፡፡

“የኔ ልጅ፤ ተዛዙረህ ማየት እንደምትፈልግ መልአኩ ነገረኝ”

አቤት ድምፅ! እንዴት ደስ ይላል! እያወራኝ እያለ የማስበው ይሄንን ነበር፡፡

“መላዕክቱ በሙሉ ሰው በማስተናገድ ላይ ስለሆኑ እኔ እራሴ ላስጐበኝህ መጣሁ፤

የሱፐር ማርኬቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ እግዚአብሔር ነኝ” አለኝ አይኖቼን እያየ፡፡

ቃላቶች በሙሉ አፌ ውስጥ ሟሙ፤ “አመሰግናለሁ እግዚያብሔር ይስጥልኝ

አይቸገሩ ሌላ ጊዜ እመጣለሁ” ብዙ ነገር ላወራ አስቤ ነበር፤ ግን በምን ቋንቋ ላውራ?  ምላሴ አፌ ውስጥ ደረቀ፣ ከንፈሬ ተንቀጠቀጠ፡፡

“አይዞህ” አለና እጆቹን ትከሻዬ ላይ አደረገ፡፡

“ብዙዎች የሚፈልጉትን ወስነው ነው የሚመጡት፤ አንተ ለምን አልወሰንክም?” አለኝ

“እንደዚህ አይነት ቦታ መኖሩን አላውቅም ነበር” አልኩኝ እየተንተባተብኩኝ፡፡

“ለማንኛውም እድለኛ ነህ የኔ ልጅ፤ ሁሉንም ተዟዙረህ አይተህ የምትፈልገውን በጥንቃቄ ትመርጣለህ” አለኝ መራመድ እየጀመረ፤ ተከተልኩት፡፡

“ይህ ዕቃ ቁሳቁስ/ማቴሪያል የምናቀርብበት ክፍለ ነው፤ ተመልከት አለኝ፤ ከምግብ ጀምሮ የተለያዩ ልብሶች፣ የቤት ዕቃዎች፣ መኪና፣ ቤት፣ ህንፃ፣ የጦር መሣሪያ፣ አይሮፕላን፣ ባቡር፣ በምድር ላይ ያለ ቁሳቁስ አልቀረም፡፡

ሁሉም ቦታ ላይ ሰዎች ይሻማሉ፣ ይቀማማሉ፣ ይገፈታተራሉ፡፡ ሶስት ቤት ያለው አንድ ሰው፣ አንድ ቤት ያለውን ለመቀማት አንገቱን አንቆ ሲገፈትረው ተመለከትኩ፡

“ለሁሉም የሚበቃ ዕቃ የለም እንዴ? ለምንድነው የሚሻሙት?” አልኩኝ፤ ድምፄ ውስጥ መንቀጥቀጥ ይሰማኛል፡፡

“እንደዚህ ናቸው፤ ይሰበስባሉ ያግበሰብሳሉ፤ ተረጋግተው ቁጭ ብለው ሳይበሉት ሞት ይቀድማቸዋል” አለኝ፤ ሽማግሌው ፊቱ ላይ የሀዘን ፈገግታ እየታየ፡፡

አበሻ መኪና ላይ ይረባረባል፤ አንዱ በሁለት እጁ ሁለት መኪና ይዞ ሌላ ሦስተኛ መኪና በእግሩ ለመቀበል እየታገለ ነው፡፡

“ይሄ ደግሞ ገንዘብና ጌጣ ጌጥ የምናቀርብበት ክፍል ነው” አለኝ፤ የአንድ ክፍል በር እየከፈተ፡፡ እዚህ ደግሞ ከበፊቱ የበለጠ ግፊያና ግርግር፣ ጉሽሚያና መገፈታተር አለ፡፡  በአለም ላይ ያለ የገንዘብ፣ የጌጣጌጥ አይነት በሙሉ አለ፡- ብር፣ ዶላር፣ ዩሮ፣ ድርሃም፣ ዬን፣ ወርቅ፣ አልማዝ፣ ብር ወዘተ …

“ይህን ሰውዬ ታየዋለህ” አለኝ፤ ወደ አንድ ቀጭን ሸበቶ ሽማግሌ እየጠቆመኝ፡፡ “ከዚህ ክፍል ወጥቶ አያውቅም፤ ቀንም ሌሊትም እየሰበሰበ ነው፤ ምግብ የሚበላበት ሰዓት እንኳን የለውም”

ሰውዬውን በደንብ አስተዋልኩት፡፡ የደም ስሮቹ ተገታትረዋል፡፡ ፊቱ ላይ ያሉ አጥንቶች  ይቆጠራሉ፡ ማዳበሪያዎቹ ሞልተዋል፡፡ ኪሱ ላይ የሉት ቀዳዳዎች ሞልተዋል፡፡ ካፖርቱን እስከ አንገቱ ቆልፎ ወደ ውስጥ ብር ይጨምራል፡፡ ከታች በኩል ብሩ ይንጠባጠባል፡፡ ራሴን በመገረም ነቀነቅኩኝ፡፡

“የኔ ልጅ” አለኝ፤ ፊቱን ወደ እኔ አዙሮ በፈገግታ እያየኝ፡ “ብዙዎች ላስጐበኛቸው እጀምርና ገና ሳይጨርሱት ወደ ሽሚያው ዘለው ይገባለ፤ አንተ ግን እስከ መጨረሻው ስለተመለከትክ በጣም ውድ ስጦታዬ የሆነውን ወርቃማውን ክፍል አስጐበኝሃለሁ” አለኝ፤ ተከተልኩት፡፡

ወደ አንድ አቧራማ ጥግ ወዳለ በር ወሰደኝ፡፡ ሰው ወደዚህ ብዙ እንደማይመጣ በአቧራው ያስታውቃል፡፡ በሩን ሲጢጥ አድርጐ ከፈተውና ወደ ውስጥ ገባን፡፡

በየጥጉ ላይ አቧራ የጠጡና የዛጉ ሳጥኖች ተቀምጠዋል፡፡ ከተከፈቱ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው ያስታውቃሉ፡፡

“አይ ወርቃማ ክፍል! አልኩኝ፤ ከልቤ፡፡ ፈገግ ብሎ አየኝና “ሂድና ምን እንደሆኑ እላያቸው ላይ ካለው ፅሁፍ አንብበህ ተረዳ” አለኝ፤ በጣም ካረጀውና ላዩ ላይ አቧራ  እተከመረበት ሳጥን ሄድኩኝና አቧራውን በእጄ ጠረግኩት፡፡ በአፌ እፍ ስለው አፌ ላይ አቧራው ተከመረ፡፡ “ፍቅር” ይላል፡፡ ወደሚቀጥለው ሄድኩኝ “ሰላም” ይላል፡፡ በየተራ   አነበብኳቸው “ጤና”፣ “እውቀት”፣ “ትዕግስት”፣ “ደግነት”፣ “እምነት”፣ “እራስን መግዛት” አንብቤ ስጨርስ አቧራዬን ከእጄ ላይ እያራገፍኩ፣ ፊቴን በአይበሉባዬ እየጠረግኩ ወጣሁ፡፡ ፈገግ ብሎ እየተመለከተኝ ነው፡፡

“እሺ የኔ ልጅ የትኛውን መረጥክ?” አለኝ

“ይቅርታ ግን..” አልኩኝ ፈራ ተባ እያልኩኝ

አይዞህ በሚል ስሜት ፈገግ አለልኝ …

“ሁሉንም ነው የምፈልጋቸው” አልኩኝ፡፡

“በጣም ጥሩ! ከሁሉም የሚበልጠውን ከመረጥክ ሌሎች በሙሉ ይጨመርልሃል” አለኝ

ደነገጥኩ፡፡ ከሁሉ የሚበልጠው የቱ ነው? ፍቅር፣ ሰላም፣ ጤና?  በደንብ ማሰብ አለብኝ  “እ…እ…እ”

“አጅሬ! እዚህ በጨለማ ድንጋይህ ላይ ቁጭ ብለሃል፤ እኔ ደግሞ ወጥተሃል ብዬ ለልጆቹ ቁርስ የሚሆን እንቁላልና ዳቦ ከሸምሱ ሱቅ ገዝቼ ልመጣ ነበር፤ አንድ ሃያ ብር አለህ?”

ባለቤቴ ነበረች ከተመስጦዬ የቀሰቀሰችኝ፡፡

 

 

Read 3192 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:41