Sunday, 26 February 2017 00:00

“የስንብት ቀለማት”

Written by  ሙሉጌታ አለባቸው
Rate this item
(12 votes)

  (ዘመን፣ አገርና ማንነት)

              “--እስከ ዛሬ ድረስ በአገራችን የፈጠራ ሥነጽሑፍ ውስጥ በልቦለድ፣ በግጥም ወይም በተውኔት ይሄን ጉዳይ ዋና ጭብጥ አድርጎ የተነሳ ሥራ አላገኘሁም፡፡ እርግጥ ነው ብሔርተኝነትን የሚያነሳሱ የኪነት ሥራዎች አ ሉን፡፡ አዲስ አ ገር ምሥረታንና አዲስ ብ ሔራዊ ተረክ መፍጠርን ዓላማ አድርጎ የተነሳ የልቦለድ ሥራ አላጋጠመኝም፡፡---”
                    
     ደራሲው ማስተዋወቅ አያስፈልገውም፡፡ ለበርካታ ዓመታት የተጠበቀው “የስንብት ቀለማት” ዘጠነኛው መጽሐፉ ነው፡፡ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ገጾች አሉት፡፡ በዐማርኛ ሥነጽሑፍ ረጅሙ የልቦለድ መጽሐፍ ነው፡፡ ደራሲው ከልቦለድ ሥራዎቹ በተጨማሪም ጥልቅ ማብራሪያዎችን የሚሰጥበት ሕጽናዊነት የተሰኘ የአጻጻፍ ስልቱ በየጊዜው ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡
መጽሐፉ በስምንት ዓቢይ ምዕራፎችና በ46 ንዑስ ምዕራፎች ተከፋፍሏል፡፡ በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ ዳሰሳ - “ድሕረ ቃል” ተካቷል። በደራሲው ቀደምት ሥራዎች ውስጥ የሚገኙት ዓይነት ምስሎች፣ ቻርቶች፣ ግራፊክ ዲዛይኖችና ሰንጠረዦች በአዲሱ መጽሐፍ ውስጥም ይገኛሉ፡፡ የግርጌ ማስታወሻዎቹም በቀይ ቀለም ሰፍረዋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ “የስንብት ቀለማት” ውስጥ ስለ ዘመን፣ ስለ አገርና ስለ ማንነት የተነሱት ጉዳዮች ላይ የተሰማኝን ለማካፈል ነው፡፡
የሦስት ዘመን ሥዕል
“የስንብት ቀለማት” ውስጥ ያሉትን ዘመናት ጨከን ብለን ብናጠቃልል በትንሹ ሦስት የተለያዩ ዘመናትን ጨምቀን ማውጣት እንችላለን፡፡ ቀዳሚው ጥንታዊ ኢትዮጵያ የነበረችበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ዘመን ራሱን “ያ ትውልድ” ብሎ የሰየመው ትውልድ የነበረበት ዘመን ሲሆን ሦስተኛውና የመጨረሻው ከድርሰቱ መቼት ከአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ መጨረሻ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ያለው ዘመን ነው፡፡
ቀዳሚው ዘመን፡ ይሄም ከአምስት ሺህ አምስት መቶ አመታት በፊት ይጀምራል፡፡ ንግሥት ሳባ በፊትና ከታሪክ ሁሉ አስቀድሞ እስከ መካከለኛው ዘመንና እስከ ንጉሡ ዘመን መጨረሻ ያለውን ያካትታል፡፡ ከጊዜ መጀመሪያ አንስቶ በጥንታዊ ግዛቶቻችን ላይ ይመላለሳል፡ ከአባይ ዳር ከናፓታ እስከ ካናርክ፤ ከጋፋትና ከወንጌ ነገዶች እስከ ጋሞ፣ ሀድያ እና ደሸት፡፡ ከኤውላጥ (ኡጋዴን) እስከ ማጂ፡፡ በንጉሥ አጋቦስ ዘመን የነበረው ጥንታዊው ባንዲራችን ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴና ሰማያዊ ሲውለበለብ ይታያል፡፡ ንጉሡን የገደለችው የንጉሥ ተዋስያ የልጅ ልጅ ማክዳ ዘውድ ስትደፋም። የመጀመሪያው ጤፍ እንጀራ ሲጋገር፤ ተጋግሮም ሲበላ፡፡ ከታሪካችን ልንማር የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ተሥለውበታል፡፡ ጥበብ የጎደላቸው ንግሥቶቻችን ስም ተዘክሮበታል፡ ቅንዳቅስ በናፓታ ነግሣ ሲሶ አገሪቱን ለእስክንድር ስትሰጠው፤ማክዳም ኢየሩሳሌም ሄዳ የወይን ቦታዋን ለሰለሞን እጅ መንሻ ስታቀርብ፡፡ የጥበበኛ ንግሥቶቻችን ስምም ተወስቶበታል፡ ከኔት ሜር እስከ ዳዲ፡፡ ለምሳሌ ዳዳዊ ማለት “…እናት መሆን ካልቻልሽ እናት መሆን ለምትችል ቦታ መልቀቅ፣ ማስተዳደር ካልቻልክ ማስተዳደር ለሚችል ቦታ መልቀቅ፣ ማፍቀር ካልቻልክ ማፍቀር ለሚችል ቦታ መልቀቅ…” ማለት ነው፡፡ በስንብት ቀለማት እንደተገለፀው፤ ዳዲ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የነገሡት የአጼ አምደ ጽዮን ሚስት ነች፡፡ መካን በመሆኗ ንጉሡ ከሌላ ሴት ወልዶ ሥልጣኑን የሚረከበው አልጋ ወራሽ እንዲያመጣ መክራው እንደዚያው ያደርጋል። በዚህ ለማስረዳት የሚሞክረው፣ የማትችለውን ነገር ለሚችለው ሰው ልቀቅለት የሚለውን ሀሳብ ከታሪካችን መማር እንደምንችል ነው፡፡ ቃሉንም ከመካኗ ንግሥት ስም ተውሰን፣ “ዳዳዊ” ልንለው እንችላለን ይለናል፡፡
በድርሰቱ ውስጥ ልዕለ ሰብዕ ኃይል ተላብሶ የመጣው የተረት ዓለሙ ስንዝሮ፣ ራሱን ማየት እንዳይችል እርግማን አለበት፡፡ “የራስህን ምስል በመስታወት ውስጥ ካየህ ሕይወትህ ታልፋለች” ተብሏል፡፡ እኛም እንደ ስንዝሮ እርግማን አለብን? ታዲያ ምነው ወደ ራሳችን ማየትን ይሄን ያህል ፈራን? ያለፈው ዘመን እንደሚጠላ ሕልም፤ እንደ ቅዠት ሆነብን? “…ታሪክ ምኑ ቅዠት ነው? ያለፈው ዘመን ምኑ ቅዠት ነው?....” ሲል ይጠይቃችኋል፤ ስንዝሮ፡፡
በዘመን ውስጥ የሚጓዘው ይሄ መለኮታዊ ፍጡር፤ በታሪካችን ውስጥ እየተጓዘ ወደ ዛሬ በተጠጋ ቁጥር የሚያጋጥመውን ሰው ሲወርፍ፣“ባረጀሁ ቁጥር የሚያጋጥመን ታሪክ የማያውቅ ደንቆሮ ነው” ይላል። በአጭሩ ወደዚህ ዘመን እየቀረበ ሲመጣ፣ ዜጎች ለታሪክ የሚሰጡት ቦታ እየቀነሰ መጥቷል ነው። ዛሬ ስንቶቻችን ነን የታሪክ ጉዳይ ግድ የሚለን?
 “እዚህ አገር ላይ መርዝ በፈረንጆች እንደተነሰነሰ አላውቅም፡፡ እንዴት ሰለጠነ የተባለው አውሮፓ መርዝ ይነሰንሳል?” ይላል ዮሴፍ፡፡ ልብ በሉ፤የተማረ ይግደለኝ የሚባልለት (እንዲባልለት ያስደረገ) የያ ትውልድ፤ ምሁር የሕክምና ዶክተር ነው እንግዲህ… ምን እንደ ዶክተር ዮሴፍ የተማርን ብንሆን መቃብራችን የሚቆፈረው ታሪካችንን በመዘንጋታችን ባድማ ላይ ነው! When a nation goes down or a society perishes, one condition may always be found – they forget where they come from እንዲል በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው Carl Sandberg የተባለ ገጣሚ፡፡
ሁለተኛው ዘመን፡ ዘመነ “ያ ትውልድ”፡፡ ደራሲው በስንብት ቀለማት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ልቦለዶቹም በተደጋጋሚ የሚያነሳው ዘመን ነው። ለምሳሌ በ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” በተባለው መጽሐፉ ውስጥ “ያለፈው ዘመን ከአሁኑ ለምን ከፋ?” ሲል ይጠይቃል፡፡ በተቃራኒው የዚህ ዘመን ሰዎች ስለ ጀብዷቸው ሲሰብኩን ራሳቸውን ከቅዱሳን ተራ ሊያሰልፉ ምንም ያህል አይቀራቸውም፡፡
እንደዚህ አብዝተው የሚነጨንጩንን ክሽፍ ቅዱሳን ሁሉ “የስንብት ቀለማት” ኩም አድርጓቸዋል። ያኔ በባሩድ ዛሬ በቀለም፤ በአፈሙዝ አልሆን ሲል በመንጎል የሚተነኩሱንን ማለቴ ነው፡፡ ያ ትውልድ ሰባት አይነት ደዌ እንዳለበት ተገልጧል። ደዌ አንድ፡ “የተማረ ይግደለኝ ሲባል ሰምቶ ተደሰተ እንጂ ቀስ በሉ አላለም”፡፡ ደዌ ሁለት፡ “ዞር ብለው የደርግን እና የንጉሡን የትምህርት ስርዐት ቢሰድቡም ያኔ ያገኙት ዶክትሬት ግን ይሞካሻል”፡፡ […] ደዌ ስድስት፡ “ሁሉም ያለ ምህረት ያለ በቂ ትንታኔ የዛሬውን ወጣት ያማሉ፡፡ … ወጣት ድሮ ቀረ አንዱ ወሬያቸው ነው፡፡ ድሮ ሲሉ እኛ ማለታቸው ነው፡፡” ስለ ያ ትውልድ የተባለው ብዙ ነው፡፡ ቀሪዎቹን ደዌዎች በዝርዝር ለማየት “የስንብት ቀለማት”ን ይመልከቱ። (ከገጽ 428-430)
ሦስተኛው ዘመን፡ አሁን፡፡ “የስንብት ቀለማት” የሚተረከው አስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ዛሬ የምንኖረው ሕይወት ይብዛም ይነስም የተመሰረተው ያኔ ነው፡፡ በቀላሉ ካፒታሊዝምና የብሔረሰቦች መብትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሀያ አመታት ከርመው ዛሬ የተባባሱ ሳንካዎቻችን፤ በስፋትና በጥልቀት እየጎለበቱ የመጡ ችግሮቻችን ሁሉ ያኔ ቡቃያ ነበሩ፡፡ መጽሐፉ ያን ዘመን ሲገልጽ፤ ስለ ዛሬ እየነገረን ቢመስለን የደራሲውን የትንቢት ችሎታ ማድነቅ ግድ ይለናል፡፡
ዘመን፣ሞትና የስንብት ቀለማት
በስንብት ቀለማት ውስጥ ሞት አብዛኛውን ጊዜ ትዕምርታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ የሚሞቱና በሕይወት የሚቀጥሉት ገፀ ባሕርያት ሁሉ የሚወክሉት ነገር መሞቱን (ወይም እየቀጠለ መሆኑን) የሚያመላክቱ መጠቁም ናቸው፡፡ የተኮላ ያለ ምንም ሀሳብ መኖር፣ ካሻው ሴት ሁሉ እየተራከበ፤ ልቡ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ በሕይወት መቀጠሉ ይሄን ዘመን ያሳያል። በአንፃሩ ደሞ ከላስታ የወለደው ልጁ ተስፋዬ በስመ ሞክሼነት መሞቱ/መገደሉ ያን ዘመን ያሳያል። “ተኮላ የመጨረሻው የአዲስ አበባ እረኛ ነው፡፡ … ከአንድ ቅጥ መረጃ አንድ ቅጥ መደምደሚያ ማግኘት የለመደ ባለ ጠፍጣፋ አንጎል ነው…” የሚለውን ስናነብ እየተነገረን ያለው ተኮላ ስለሚባል አንድ ግለሰብ ሳይሆን ስለ ዘመናችን ብዙ ተኮሎች እንደሆነ ብናስብ የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ላይ በ”እቴሜቴ ሎሚ” ሽታ ውስጥ የሚገኘውን “አሸራዊነት” የተሰኘ ፅንሰ ሀሳብ ማውሳት ተገቢ ነው፡፡
አሸራዊነት ማለት “ሆን ተብሎ አስሩ መረጃ እንዳለ እየታወቀ  አንዱን ብቻ እንደ ታላቅ ወካይ ጉዳይ አንስቶ መሟዘዝ” ማለት ነው፡፡ አሸራዊያን የሚለው ሀሳብ “ዐሹራ” ከሚለው ቃል የመጣ ይመስላል፡፡ ዐሹራ ደግሞ በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ፡ ዓሥራት፣ ከዐሥር አንድ እንደ ማለት ነው። በዚህ ዘመን አብዛኞቻችን ከአንድ የመረጃ ቅንጣት ተነስተን አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ የምንደርስ “የከተማ እረኞች” አይደለንም ትላላችሁ? እመኑኝ ብዙዎቻችን ተኮላዊያን ነን፡፡ ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስና… የተኮላ ልጅ፤ ሟቹ ተስፋዬ ደግሞ ባልገባውና በማያውቀው ነገር የሞተው፣የዚያ ዘመን ወጣት ወኪል መሆን ይችላል፡፡
በስንብት ቀለማት ሌላዋ ሟች ዘውዲት ናት። ነገር የገባት የልጅ አዋቂ፤ ዘውዲት ኅሊና ናት፡፡ ሠዓሊና ገጣሚ ወርቁ፣ እንቁ ባህሪ እንደሚላት “…የሚረዳት አጃቢ የማትፈልግ መንገደኛ ዐይነት ናት፣ አልፋን/አልፋኝ/አልፋችሁ የምትሄድ” የዘውዲት ራሷን ማጥፋት ማለት ዘመኑ ኅሊናውን በገዛ እጁ ገድሏል እንደ ማለት ነው፡፡ ኢብሳም ሞቷል። ሳላይሽ እንኳን “ልዋሸው የማልችለው ነገር ለልጃቸው ለኢብሳ ያለኝ ፍቅር ነው፡፡ ምን ክፋት እነሱ ላይ ልስራ፤ በጣም እወደዋለሁ” ያለችው ኢብሳ፣የልብ ንጽሕና ነው፡፡ ይሄ ባለ ትላልቅ ዐይኖች ንጹሕ ብላቴና በሞት ተወስዷል። ማሕበራዊ ሕጸፆችን በጽሑፉ የሚሟገተው፣ ማንነትና አገር ላይ የሚፈላሰፈው የቀለም ቀንዱ ዮሐንስ ወላይሶ፤ እሱም ሞቷል፡፡ ብናጠቃልለው፤ የዋህነት፣ ኅሊና፣ ንጽሕና እና ጭንቅላት ሞተዋል፡፡ በተቃራኒው በሕይወት የሚቀጥሉት እነ ቤላ፣ እነ ፊያሜታ፣ እነ ተኮላ ናቸው፡፡ እነዚህ ገጸ ባሕሪያት ደሞ እንደ አገር እንድንታመም ላደረጉን ለብዙዎቹ ማሕበራዊ ደዌዎቻችን መንስዔዎችና አስፋፊዎች ናቸው፡፡
ማሕበራዊ ደዌያችን
ማሕበራዊ ደዌያችን ዝቅጠት ነው፡፡ ወይም ደራሲው በሌላኛው ረጅም ልቦለዱ በ“መረቅ” ውስጥ  ያስተዋወቀንን የግዕዝ ቃል ልጠቀምና ማሕበራዊ ደዌያችን “ሐሲር” ነው፡፡ “የተማራችሁትም ያልተማራችሁትም በሐሲር ጎዳና ሰከም ሰከም ስትሉ እንደ አንድ ዜጋ ወንድማችሁ ታዘብኳችሁ።” ይለናል፡፡ (ሐሲር የእንግሊዝኛውን decadence ይተካል)፡፡
በስንቱ ዘቅጠናል? የቱን አንስተን የቱን እንተዋለን? “የስንብት ቀለማት” ግን  አስቀያሚውን ዝቅጠታችንን ሁሉ በውብ የታሪክ ቅንብር በስፋት አሳይቶናል፡፡ ከቋንቋችን ቢጀመር፣ “ያ ያ ማለት፣ከ አዎ ይበልጣል” ይለናል፡፡ ይሄስ የዘመናችን አንዱ ደዌ አይደለም? እንዲያውም “አዎ” የሚል መልስ ሰጥተህ ብትሳሳትና ሌላ ሰው ደሞ ለተመሳሳይ ጥያቄ “ያ” ብሎ መልሶ ቢሳሳት፣ እሱ በትክክል እንደመለሰ ሳይቆጠር ሁሉ አይቀርም ልበል?
ሌላው ደዌ የገንዘብ አምልኮ ነው፡፡ ቹቹ አንዱን ዝቅጠታችንን ከባዕድ በተዋሰ አንደበት (ይሄም ራሱ ሌላ በሽታ ነው!) አስቀምጣዋለች፡- “ዋት ኢዝ ሆሊየር ዛን ካሽ?” መጽሐፍ ቅዱስ፤ “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” ይላል፡፡ በስንብት ቀለማት ደሞ ቹቹ “ፍቅር ሀይለኛ ብትሆንም ግን ካሽ የበለጠ ሀይለኛ ነው። ካሽ ፈጣሪ ነው። … አማኙ ሁሉ ጆቫ፣ እየሱስና አላህ እያለ ካሽ ካላየ ይደበራል” ትለናለች፡፡ በልቦለዱ ነዋይ “አዲሱ አምላክ” ሆኖ ቀርቧል፡፡ ሃይማኖት የለውም፡፡ “ሲፈልግ ክርስቲያን ይሆናል፣ሲፈልግ ሙስሊም፡፡” ይሄም የዘመናችን እውነት ነው፡፡
ሕመማችን ኁልቆ መሣፍርት ነው፡፡ ቋንቋና ማንነትን ማጣት፤ ገንዘብን ማምለክ ብቻ አይደሉም። ጎሰኝነት፣ ታሪክን መጥላት፣ ወዘተ፡፡ በወል ታመናል፤ በቡድን ደዌ ተጭኖናል፡፡
በአንዱ ምዕራፍ፤ የራሱ እና የሌሎችም ሕመም ሁሉ ተደምሮ በተኮላ ሬብ ፈስ መስሎ ይወጣል። ቁናሱ ብርቱ ነው፡፡ የአባላዘር በሽታ ለመታከም ካልሆነ በስተቀር ሐኪም ቤት ሄዶ የማያውቀው ተኮላ፤ እንደዚህ እንግዳ አይነት ሕመም ሲጠናወተው ሐኪም ቤት ሄዶ ሲታይ፣“ሰምቶት የማያውቀው በአንደበቱ አጥርቶ ሊደግመው የማይችል ከአንጎሉ ተጣብቆ የቀረ የእንግሊዝኛ ስም” ይሰጡታል፡፡ በሽታህ ʻግሩፕ ሂስቴሪያʼ ነው ይሉታል፡፡ የእሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሁሉ የቃዡት አንድ ላይ ተደምሮ ሕመም ሆኗል፡፡ ይሄ የቡድን ቅዠት ነው፡፡ Group hysteria ወይም collective delusion!
Group hysteria ወይም collective delusion በመንጋ መታመም፤ ማሕበራዊ ደዌ ነው፡፡ ይሄ አይነቱ ሕመም ደሞ ዛሬያችንን ማበላሸት ብቻ ሳይሆን ነጋችንንም ይወስናል፡፡
ሌላኛው ችግራችን የእነ ፊያሜታና የእነ ቤላ በሽታ ነው፡፡ ሱዶሎጂያ ፋንታስቲካ! ስሙ ደስ አይልም? (በሽታ እንኳን በእንግሊዝኛ ሲጠራ መልካም ነገር ይመስለናልና)፡፡ በልቦለዱ እንደተባለው የመዋሸት በሽታ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ስሞቹ mythomania, ወይም pathological lying ናቸው፡፡
“ለፊያሜታ መዋሸት ታለንት ነው”፡፡ (ይቺኛዋን ከፊያሜታ ጊላይ ጋር ማነፃፀር ሌላ ጽሑፍ ይወጣዋል!) ለቤላም እንደዛው፡፡ አንድ የተሟላ የውሸት ኤምፓየር አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡ ውሸት ይፈጥራሉ፤ የፈጠሩትን ውሸት የሚያሰራጩበት መንገድና የሚሸከምላቸው አካል አለ፡፡ የሚዋሹትም ለአገራችንና ለሕዝቡ ያላቸውን ጥላቻ በድርጊት ለመመንዘርና ጉዳት ለማድረስ ነው፡፡ ደራሲው ሁኔታውን ለማብራራት ተገን ያደረገው ሚሜቲክስ ሳይንስን ነው፡፡ ሚሜቲክስ ማለት በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ቲዮሪ ላይ ተመሥርቶ፣በማሕበረሰብ ውስጥ የመረጃ ስርጭት ሂደትን የሚያጠና ሳይንስ ነው፡፡
በዚህ የሳይንስ ዘርፍ ሚም (በአማርኛ ጭም ወይም ጉም) “የመጨረሻ ትንሿ የመረጃ አሃድ” ናት፡፡ ሁለትና ከሁለት በላይ ጭም” በአንድ ላይ ሲሆኑ ደሞ ጭምጭም ወይም ጉምጉም፣ በሳይንሱ memotype ይባላል፡፡ ታዲያ የመዋሸት ደዌ የተጠናወታቸው ቤላና ፊያሜታ የሚያመርቱትን ጭምጭምታና ጉምጉምታ “ከቦታ ወደ ቦታ የሚያመላልሳቸው የታመነ ተሸካሚ” ያስፈልጋቸዋል፡፡  ምክንያቱም “በማሕበራዊ ተራክቦ ጉሞች [ወይም ጭሞች] ከቦታ ቦታ፣ ከሰው አፍ ወደ ሰው ጆሮ እየተሸጋገሩ መጓዝ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ሕልውና አይኖራቸውም፡ ይደክማሉ፣ ይታመማሉ፣ ይለወጣሉ እናም ይሞታሉ”፡፡ እነዚህ ታማኝ ተሸካሚዎች “ጀልባ” ወይም “ደንገል” የተባሉት memeboats ከሚለው ሀሳብ በመነሳት ነው፡፡
ታዲያ ሁለት እንስቶች እየፈጠሩ በከተማው የሚያሰራጩት ወሬ ትልቅ ቁምነገር ሆኖ እንደዚህ መጽሐፍ አስገልጦ፣ ሳይንስ አስጠቅሶ ማነጻጸር ያሻዋል? አዎ! ምክንያቱም ጉዳዩ የሁለት ሴቶች ብቻ አይደለም፡፡ ይሄን የሚጠራጠር ካለ “አሉ” ተብሎ የተነገረውን ስንት አሉባልታ ሰምቶ ለስንቶችስ እንዳደረሰ ያስብ፡፡ አገሩ በወሬ የሚፈታ መሆኑን እናውቃለንና ውሸትን የሳይንስ ሰሌዳ ላይ አጋድመን አናቶሚዋን ብናጠና ፈውሱን ለማግኘት አይከብደንም ይሆናል፡፡ (ኪነታዊ ፋይዳን ለጊዜው ወደ ጎን ገለል አድርገን ብንጠይቅ፤ አጠቃላይ የመጽሐፉ ጥቅም ራሱ ፈውስን መለገስ አይደል?)
በስንብት ቀለማት የተነሳውን አንድ ሌላ ማህበራዊ ደዌ ለማሳየት ሁለት ምሳሌዎች ላንሳና ወደ ቀጣዩ ክፍል ልሻገር፡፡ ይሄኛው ደዌ ጎሰኝነት ነው፡፡ “በክርስቶስ አምናለሁ የሚል ጎሰኛ ቢያጋጥመኝ የክርስቶስ ሰው እንዳልሆነ አውቃለሁ። ረቂቅ ምርመራ አያስፈልግም፡፡ ቀኖና መመርመር ግድ አይደለም፡፡ ሺህ ጊዜ እንጥልህ በመዝሙርና በቅዳሴ ቢነድ ጎሰኛ ነህ፤ ክርስቲያን አይደለህም፡፡ ቀላል ነው፡፡” ይላል በድንግልና የፀነሰችው የምትኬ እጮኛ/ጠባቂ ዶክተር ዮሴፍ፡፡ (ኦ! ስም አወጣጥ!)
የጎሳ ነገር ከተነሳ ከሳላይሽ ንግግር ይቺን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ “ይሄንን አባይ በማዝዳ ኤስ ዩ ቪ የማቋርጠው ስለ ብሄረሰቦች እኩልነት በማሰቤ አይደለም፡፡ ማን ከማን ነጻ ይወጣል፡፡ አንዱም ቅማላም፡፡ ሁለተኛውም ቅማላም፡፡ ሁሉም ያልቀናው ቅማላም ነው፡፡ አንዱ በአንዱ እያሳበበ ይታሽ፡፡ እንተዋወቃለን በየቦታው፡፡ ረጋሚም ተረጋሚም”፡፡ በዚህ ዘመን የዘረኝነት አርማ አንግባችሁ የምትጨቀጭቁን ያልቀናችሁ ጎሰኞች ሆይ! ይሄን ሰማችሁ? እስቲ ለአፍታ እንኳን አንዳችሁ በሌላችሁ ማሳበቡን ተዉና፤ በጎሰኝነት ዐይን-አር የተጨፈነ ዐይነ ኅሊናችሁን ጠራርጉት፡፡ ለጎሳችሁ ያላችሁ ስሜታት አሁንም በጥንታዊው የጋርዮሽ ስርዓት እንደነበረው በደመነፍስ አይገዛ፡፡ በአናሳ የአደን ቡድን ውስጥ እንዳለን አናስብ፡፡ በዚህ ዘመን የዘረኝነት አርማ አንግቦ ለሚጨቃጨቅ ሁሉ ይሄ ጥሩ ማንቂያ ነው። ጸሀፊው እንዳለው፤ “…our emotions are still governed by the instincts appropriate to the small hunting band›; ‹the savage in us still regards as good what was good in the small group” (F.  A. Hayek, Law, Legislation and Liberty) በትንንሽ መንጋ ቡድኖች ከመቆራቆዝ ይልቅ ከፍ ብሎ ስለ ሀገር ማሰብ አይበጅም?
ስለ አገር ምሥረታና ስለ ኪነት አስተዋጽዖ
እንደ ብዙ የዓለም አገራት ይህቺ አገር የተመሠረተችው በግዛት ማስፋፋት ነው፡፡ ግዛት ማስፋፋቱ ሰላማዊ ነበረ ወይ? የሕዝቦች ግንኙነትስ እውነት የጨቋኝና የተጨቋኝ ነበረ ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለማንሳት አልፈልግም፡፡ የግዛት ማስፋፋት በእኛ አገር ብቻ የተፈጠረ እንግዳ ክስተት አይደለም፡፡ በማዋሃድና በመበታተን ታላላቅ የሥርወ መንግሥት አገራት ይመሠረታሉ፡፡ ልዩ ልዩ ቡድኖች በመዋሃድ ጭንቅት በግጭቶች፤ ለሀይልና ለክብር በሚያደርጉት ትንቅንቅ ውስጥ ያልፋሉ። ቡድኖቹ በዚህ ውስጥ ሲያልፉ አንዱ በሌላው ላይ ጥገኛ መሆኑ ሊያመጣው የሚችለውን ጭቆና ወይም ማውደም ይፈራሉ፡፡ “በቀላሉ ምን መሰለህ? ፍልስፍና አያስፈልገውም፡፡ መደምደሚያው፤ቅኝ አልተገዛሁም” ነው፡፡ (የስንብት ቀለማት)
የልቦለድ መጽሐፍ አንብቤ የተሰማኝን ለማካፈል በማቀርበው ጽሑፍ ውስጥ ስለ አገር ምሥረታ አንስቼ ይሄን ሁሉ የማወራው ለምንድን ነው? ስለ ኪነት እያወራሁ ስለ ፖለቲክ መዘባረቄስ ለምንድን ነው? ምክንያቴ “የስንብት ቀለማት” ዋና ጭብጥ የአገር ምሥረታ መሆኑ ነው፡፡ “ደግሞ ልቦለድ እዚህ ውስጥ ምን አገባው?” ለምትሉ በስንብት ቀለማት መጨረሻ ገጾች ላይ ጥልቅ ትንታኔ ያቀረበውን ቴዎድሮስ ገብሬን በተደጋጋሚ እጠቅሳለሁ…   “ከነጭራሹስ የአገር (የስቴት) ምሥረታ የከያኒው ጉዳይ (በፖለቲካው ቋንቋ “ማንዴት”) ነውን? ለዚህ መልሱ ምን ጥያቄ አለው የሚል ነው” ይላል ቴዎድሮስ፡፡
ኪነት ለአገር ምሥረታ ከምታበረክተው አስተዋፅዖ አንዱን እንጥቀስ ብንል ሚት (myth) ዋነኛው ነው፡፡ በተለይም ፖለቲካል ሚት፡፡ ፖለቲካል ሚትን ደግሞ አብዛኞቹ የሚት አጥኚዎች “necessary fiction” ወይም ደግሞ “supreme fiction” ይሉታል፡፡ (ቴዎድሮስ ገብሬ፡ ድህረ ቃል)፡፡
ሚት በዋናነት አፈ ታሪክ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከውሸት ጋር ይቆራኛል፡፡ “ሆኖም ከእውነታና ከትእምርታዊ ልቦለድ የተዳቀለ፤ ማሕበረሰቡ ለአለም ያለውን አመለካከትና በውስጡ የያዛቸውን እሴቶች የሚያሳይ ታሪክ መሆኑን የሚረዱት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው”፡፡ Few understand myths as stories composed of fact and symbolic fiction, stories that are true in the sense that they truly express the basic worldview and values of the people who tell them. (Mythic America) በተጨማሪም “Mythology: Timeless Tales of Gods and Heroes” በሚለው የግሪክና ሮማን ሚቶሎጂ ልዩ ስብስቧ  የምትታወቀውና፤ ባበረከተችው አስተዋፅዖም የአቴንስ ከተማ የክብር ዜግነት የተሰጣትን ኤዲት ሐሚልተን ብንጠቅስ፡- “What the [Greeks] myths show is how high they had risen above the ancient filth and fierceness by the time we have any knowledge of them” ትለናለች፡፡ ሚት የማሕበረሰቡን እሴት ብቻ ሳይሆን የሀሳብ ልዕልናውንም ያሳየናል፡፡
ሚት የጥበብ/የኪነት አንዱ ዘርፍ በመሆኑ ኪነት ለአገር ምሥረታ ያላት አስተዋጽዖ ቀላል አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ይሄው የሚሆነው አንድ አገር ከተመሠረተች በኋላ አገር ሆና እንድትቀጥል፤የማሕበረሰቡን እሴቶች የሚያሳይ አንድ (ወይም ከዚያ በላይ) ተረክ ስለሚያስፈልጋት ነው፡፡ ቴዎድሮስ ገብሬ “ያለ ሚት የቆመ አንድም አገር የለም” ሲል የማይታመን ሊመስል ይችላል። አሜሪካን እንኳን ብናይ አገሪቷን አሜሪካ የመሆን ቀለም የሚሰጧት ሁለት ዋና ተረኮች አሉ፡፡ Mythic America በተባለውና ስለ አሜሪካና ብሔራዊ ሚቶቿ መጣጥፎችን ባካተተው የIra Chernus ጦማር ላይ እንደሰፈረው፤አንደኛው የተስፋና የለውጥ ሚቶሎጂ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚቶሎጂ፡፡ እነዚህ ሁለት አብይ ተረኮች አሜሪካ በአገር ውስጥ ራሷን እያሻሻለች እንድትቀጥል ብቻ ሳይሆን ራሷን የዓለም ሁሉ ጠባቂ እንደሆነች አድርጋ እንድትቆጥር የሚያስደርጓት ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡   
ወደ አገራችን እንመለስ፡፡ ጥበብን የተጠማች ንግሥታችን ሳባ ከሰሎሞን የጥበብ ምንጭ ጠጥታ ልትረካ መካከለኛው ምሥራቅ ትሄዳለች፡፡ “የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ [ወደ ኢየሩሳሌም] መጣች… ንጉሡንም አለችው፡- ስለ ነገርህ እና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው… እነሆም እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል…” (መጽሐፍ ቅዱስ) ሳባ ከሰለሞን ጸነሰች፤ ብቸኛ ወንድ ልጇን ምኒሊክ ቀዳማዊን ወለደች። ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ከኢየሩሳሌም ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ (ክብረ ነገሥት)፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የተመሠረተው ሰሎሞን፣ ሳባ እና ሚኒሊክ ቀዳማዊን ሦስት አምዱ ባደረገው በዚህ የክብረ ነገሥት አውራ ተረክ (Grand Narrative) ላይ ነው፡፡ (ቴዎድሮስ ገብሬ፡ ድህረ ቃል)
ይሄ ተረክ አገልግሎት እየሰጠ የቀጠለው ግን እስከ አስራ ዘጠኝ አምሳዎቹ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ “ያ ትውልድ” ያቀጣጠለው አብዮት መጣ፡፡ ይህቺ አገር ከተመሠረተች መቶ አመት እንኳን አልሞላትም የሚሉት ክርክር ነፍስ ዘራ፡፡ አገራዊው ተረክ ወደ ተራ ተረትነት ደረጃ ዝቅ አለ፡፡ በአገሪቷ ታሪክ ላይ ትልቅ ክፍተት ተፈጠረ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ያለ አውራ ተረክ “እየኖርን” ነው፡፡
“የስንብት ቀለማት” ይሄን ክፍተት የሚሞላ ትረካ ነው፡፡ ንግሥተ ሳባ እየሩሳሌም ሄዳ፤ ከሰለሞን ፀንሳ፤ ምኒሊክ ቀዳማዊን ወለደች የሚለው ተረክ በአዲስ ተረክ ተተክቷል፡፡ አዲሱ ተረክ ደግሞ “ከዘመናዊው ዓለም፣ ከዘመናዊው አስተሳሰብ፣ ከአዳዲሶቹ ፊዚካዊ ሳይንሶች፣ ከሥነ ልቡና ሳይንስ እና ከዘመናዊው ኪነ ጥበብ ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት አለው፡፡” (በይነ-ዲሲፕሊናዊ የሥነ ጽሑፍ ንባብ በቴዎድሮስ ገብሬ)   
ይሄም መጽሐፉ ከተራ ልቦለድነት በላይ ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው የቴዎድሮስ ገብሬ ቃል ነው፡- “የስንብት ቀለማት፣ የአዲስ ርእይ፣ የአዲስ ርእዮት፣ የአዲስ አስተርእዮ፣ በጥቅሉ የአዲስ አገር ምስረታ (state formation) መድበል ነው የሚል እምነት አለኝ”፤ እንዲል፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ በአገራችን የፈጠራ ሥነጽሑፍ ውስጥ በልቦለድ፣ በግጥም ወይም በተውኔት ይሄን ጉዳይ ዋና ጭብጥ አድርጎ የተነሳ ሥራ አላገኘሁም። እርግጥ ነው ብሔርተኝነትን የሚያነሳሱ የኪነት ሥራዎች አሉን፡፡ አዲስ አገር ምሥረታንና አዲስ ብሔራዊ ተረክ መፍጠርን ዓላማ አድርጎ የተነሳ የልቦለድ ሥራ አላጋጠመኝም፡፡ ከኢ-ልቦለድ መጽሐፍት መካከል ግን አገራዊ ችግሮቻችንን መርምሮ መውጫ ቀዳዳውን ለመጠቆም በስፋት በማብራራቱ የወደድኩት አንድ የማርቆስ ረታ መጽሐፍ ነው፡፡       ይቀጥላል)

Read 6240 times