Sunday, 26 February 2017 00:00

ገቢና ወጪ - (ወግ)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  “መቼም ያለ ፈጣሪ መኖር የማይሆንልን ከሆነ … መቼስ ምን ማድረግ ይቻላል?” ብሎ ዝም አለ፤ የክሪስቶፈር ሂችንስን መፅሐፍ ከአዛውንቱ ተውሶ ሲያነብ የቆየው ወጣት፡፡ መፅሐፉን በእጁ ላይ ይዞ እየደባበሰው ነው፡፡
አዛውንቱ ወፍራሙን ጋቢያቸውን ለብሰው፣ በቀዝቃዛው የክረምት ጭጋግ ውስጥ ቆመዋል፡፡ ወጣቱ በአዛውንቱ ግቢ ውስጥ ከጎናቸው ቆሟል። እጁን በአክብሮት ከጀርባው አጣምሮታል፡፡ በእጁ ላይ መፅሐፉን ይዞ ይደባብሰዋል፡፡ አዛውንቱ ነባር ሳይንቲስትና ኢ-አማኒ ናቸው፡፡ ኢ -አማኒ ናቸው ይባልላቸዋል እንጂ የሚያምኑት የሌላቸው አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በህይወት ያምናሉ፡፡ ባያምኑ እስከዚህ እድሜ ድረስ መኖር አይችሉም ነበር … ብሎ አሰበ ወጣቱ፤መፅሐፉን እየደባበሰ፡፡
“ያለ ፈጣሪ መኖር የማይሆንልን ከሆነ፣ የሚመጥነንን ፈጣሪ መፍጠር ነዋ!” አሉ አዛውንቱ። አፍንጫቸውን የማሸት ባህርይ አላቸው፡፡ በመደባበስ ብዛት መፅሐፉ በወጣቱ እጅ ላይ እንዳረጀው .. የአዛውንቱ አፍንጫ ደግሞ ከሌላው የፊታቸው ቅላት ተለይቶ ጠቁሯል፡፡
“ፈጣሪ ባይኖር ኖሮ ልንፈጥረው እንገደድ ነበር ---- እንዳለው ማለትዎ ነው?” አለ ወጣቱ፤ ከእርስዎ ባላውቅም በሚል ትህትና፡፡
“አዎ በትክክል … ግን ቮልቴር መፍጠር ያለብን ምን አይነቱን ፈጣሪ ነው ብትለው መልስ የለውም … እኔ ደግሞ የምለው መፍጠር የማትችለውን ፈጣሪ ለምን ወደዛ አትተወውም … ከአቅምህ በላይ ከሆነ … መተው አይሻልም?!” ብለው አፍንጫቸውን መፈተግ ቀጠሉ፡፡ ጣታቸው በአፍንጫቸው ቀዳዳ ገብቶም እንደማፅዳት ይልና፣ ከዛ ደግሞ ወደ ላይና ወደ ታች እየተመላለሰ መፈተጉን ይቀጥላል። የማሰላሰያ ጊዜ ለመግዛት የሚያደርጉት ሙከራ ሳይሆን አይቀርም ብሎ ወጣቱ ጠረጠረ፡፡ እሱም የራሱ የማሰላሰያ ቴክኒክ አለው፡፡ በልማድ ሁለት እጆቹን እያጨባበጠ መፈተግ ይቀናዋል፡፡ አሁን በእጆቹ መሀል ያለው መፅሐፍ ስለሆነ፣ የመፅሐፉ ገፆች ወደ መላላጥ ቀርበዋል፡፡
ወሬውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመቀየር “ዛሬ ልደቴ ስለሆነ አንዳች ነገር ማድረግ አሰኝቶኛል” አለ ወጣቱ፤ መፅሐፉን ለአዛውንቱ እያቀበላቸው። ለመቀበል ፍላጎት ያላቸው አልመሰሉም፡፡ የተዘረጋው እጁ ተንከርፍፎ በአየር ላይ ቀረ፡፡
“ስንተኛ ዓመት ልደትህ ነው? … የሚገርም ነው፤ እኔ በአንተ እድሜ ሳለሁ ስለልደቴ ምንም አላውቅም ነበር፡፡ ለመወለድና ለልደት ቀን ከፍ ያለ ግምት እንዲኖር፣ የኑሮ ደረጃም ከፍ ማለት አለበት። … እኔ ወጣት ሳለሁ ዋነኛው ነገር ሚስት አግብቼ፣ ልጆች ወልዶ ማስተማር ነበር ቁም ነገሩ” ብለው ድንገት ዝም አሉ፡፡ ወደ ትዝታ፣ ወደ ኋላ ዘመን ሲሸመጥጡ … አፍንጫቸውን ተወት አደረጉት፡፡ ሀሳብ ከአፍንጫ ጋር ያለው ትስስር ጠንካራ መሆኑ ወጣቱን በድጋሚ ተሰማው፡፡
“አሁን አንተ የምታነበውን አይነት መፅሐፍ፣ እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ የማንበብ ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ በዛ ዘመን የማምንበት ፈጣሪ መጠኔ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነበርኩኝ፡፡ ፈጣሪና እኔ ተስማምተን ነበር የምንኖረው፡፡ ከመስማማታችንም በላይ በጥልቅ የምንነጋገር፣ የምንቀራረብ ይመስለኝ ነበር፡፡ ታውቃለህ አይደል፤ መስማማት ማለት ባለህበት መርገጥ ማለት ነው፡፡ … እኔና ፈጣሪዬ ባለንበት ብንረግጥም … ተፈጥሮና የህይወት ሂደት ግን ይለወጣል፡፡ … ለውጥ መጣ፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ይዞ የመጣው ሀሊዮ፣ በእኔና በፈጣሪ መሀል አለመግባባትን ፈጠረ፡፡ የፈጣሪ ንግግር ለሚያድገው አእምሮዬ ጠበበኝ፡፡ ልክ የልጅነቴን ልብስ በሚያድገው አካላቴ ላይ አምጥተው እንዳጠቀለቁልኝ ጠበበኝ፤ … ጥበቱን ለማስፋት አንድም የበለጠ ሀይማኖተኛ መሆን አልያም … የጭንቅላቴን መጠን አስፍቼ የበለጠ ማሰብና ማወቅ ነበር ያለኝ አማራጭ፡፡ ከዚህ በላይ አማራጭ መኖሩን ለማወቅ ራሱ ማወቅና የአስተሳሰብን አድማስ ማስፋት … ቀዳሚ ግዴታዬ ነበር ..” … ብለው እንደገና ወሬያቸውን አቋረጡ፡፡
ወጣቱ አንዳች ነገር ጠረጠረ፡፡ አዛውንቱ የሆነ ማስረጃ ለማቅረብ እየሞከሩ እንደሆነና … ከጥንቱ ፈጣሪያቸው ጋር የነበራቸው መግባባትና ቅርርብ እንደገና እየናፈቃቸው እንደሆነ ጠረጠረ፡፡ ዝም ብሎ ማድመጡን ቀጠለ፡፡ በመሀል ቀስቃሽ ጥያቄዎችን ይሰነዝርላቸዋል፡፡
“እርስዎ የሚያምኑት ፈጣሪ፣ በምን ሀይማኖት ውስጥ የሚገኝ ነበር?”
“እምነት በመሰረቱ እንደ ባህል ከአፈራህ ማህበረሰብ የምትወርሰው ነው፣ መጀመሪያ፡፡ ዝግ ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ፈጣሪና የሰለጠነ ወይንም ሰፊ አመለካከትን ያዳበረ ማህበረሰብ ያለው ፈጣሪ ይለያያል፡፡ … ግን መለያየቱ … ሔዶ የሚገናኝበት ቦታ ይኖረዋል፡፡ ሁሉም ፈጣሪን በሰው አምሳል … ወይንም ለሰው የተሳለ ማድረጋቸው ላይ ዞረው ዞረው ይግባባሉ፡፡ … ስለዚህ ፈጣሪ ራሱ የሚኖረው ገፅታ እንደ ሰው ገፅታ ከመሆን አይወጣም፡፡ ልክ ፈረንጅ ሰውና በአፍሪካ ጫካ ያለ የቡሽሜን ኋላ ቀር ሰው .. ሆነም ቀረ ሰው መሆናቸው ላይ እንደሚስማሙት ይሆናል፤ፈጣሪም … እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው … ሰው ራሱን ከሰው በላይ አድርጎ ካልፈጠረ … ፈጣሪውም ከሰውኛ ባህርይ የተላቀቀ ሊሆን አይችልም፡፡”
“በእጅ አዙር የተነሳንበትን ጥያቄ መለሱልኝ። መፍጠር ያለብን ሰውን ነው ማለታቸው ነው፡፡ ሰውን አንድ ማድረግ እስካልተቻለ፣ፈጣሪም ይህንኑ የሚከተል ነው፡፡ …. ከባህላዊው እስከ ዘመናዊው …. ከጨካኙ እስከ ክርስቶሳዊው፣ ትሁት ፈጣሪ ያሉት ሀይማኖታዊ ትርክቶች … ስለ ፈጣሪ ከሚነግሩን ይልቅ ስለ ሰው ልዩነት የሚነግሩን መረጃ የበለጠ ነው፡፡”
“ስለ እድሜ ሊነግሩኝ የሚፈልጉት ነገር ነበር ልበል?” እያለ ወጣቱ በግድ መፅሐፉን አስጨበጣቸው፡፡ መቀበል የፈለጉ ግን አይመስሉም። … መፅሐፉ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ አልፈውት የሄዱ መሰለው፡፡ አልፈው ሄደው የት እንደደረሱ ግን እርግጠኛ አልነበረም፡፡ የደረሱበት ቦታ ከጠፋቸው ደግሞ አደገኛ ነው፡፡ በጠፋው መልስ ፋንታ ትዝታ በክፍተቱ መሀል ይገባል፡፡ የጥንቱ የፈጣሪ ዕምነት ከብዙ ጥንታዊ የልጅነት ትዝታ ጋር የተሳሰረ ስለሆነ ... ወጣትነቱን የሚመኝ ማንም ሰው … በወጣትነቱ ዘመን ያመልክ የነበረውን አምልኮ … ያፈቅራት የነበረችውን (አግብቶ ያስረጃትን) ኮረዳ መልሶ ለማግኘት ቢናፍቅ አይገርምም፡፡
ሰውዬውም ወደፊት ሄደው በስውር መስመር ወደ ጥንቱ ኋላቀርነታቸው እየተመለሱ መሰለው፤ ወጣቱ፡፡ እሱ ለማጣት እየተፍጨረጨረ ያለውን እምነቱን … ሽማግሌው መልሰው ለመጨበጥ እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡ ግን ችግር አለው፡፡ ሰውዬው የሚታወቁት በተራማጅነታቸው ነው፡፡ ኋላቀር እምነትን በመሞገት ስማቸው የገነነ … ገናና መፅሐፍት አበርክተው ብዙውን ያነቁ ናቸው፡፡
መጀመሪያ ትዝታ ወደ ኋላ … ወደ ቀድሞው እምነታቸው እንዲመለሱ እንዳበረታታቸው ሁሉ … ይሉኝታ ደግሞ ወደ ኋላ መመለሻውን ዘግቶ አጠረባቸው፡፡ ወጣቱ ድንገት ሰውዬውን እየተመለከተ፣ይሄ ሁሉ የገቡበት አጣብቂኝ ወለል ብሎ ታየው፡፡ ተገለጠለት፡፡
ነገር ግን፤ ቢገለጥለትም፤ እሱ የሚወስደው ትምህርት የለም፤ከሰውዬው ተሞክሮ፡፡ እኔም ለመተው ወደፈለኩት እምነት አንድ ቀን ማጣፊያ ሲያጥረኝ መመለሴ አይቀርም ብሎ አላሰበም። ወጣት ነው፡፡ ዞሮ መግቢያው ቢታወቀውም ከመውጣት አያግደውም፡፡ ማመፅ አለበት፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡
“የልደት ቀኔ የሚያስታውሰኝ … ጊዜው የእኔ መሆኑን ነው” አላቸው፤ ለአዛውንቱ፡፡ የፈለገ ቢፈትጉትም ግን የሚሰጣቸው መፍትሄ አይኖርም። ወጣቱ ሽማግሌውን ወደ መተንኮስ ድንገት አመራ። በእሳቸው ሞት የእሱ ትንሳኤ ወይንም የእሱ ዘመን እንደሚጀምር አንዳች መገለጥ ሹክ ብሎታል፡፡
“ጊዜው የእኔ መሆኑንና መፅሐፉ ለእርሶ እንደማያገለግል ነው የልደቴ ቀን የገለጠልኝ … ይኼ አባባሌ የድፍረት አይሁንብኝና … በአባባሉ ከተስማሙ ለምን መፅሐፉን እንደ ልደት ቀን ስጦታ መርቀው አያበረክቱልኝም?!”
የንግግሩ ድፍረት በሽማግሌው ውስጥ የተሸሸገ ንዴት ቀሰቀሰ … ግን ንዴታቸው በማሸት ብዛት የጠቆረ አፍንጫቸውን በኃይል ከማቅላት በላይ ሌላ መፍትሄ ሊፈጥርላቸው አልቻለም፡፡ ጋቢያቸውን በመላጣው ጭንቅላታቸውና ሽበቶቻቸው ላይ አልብሰው ወጣቱን ትክ ብለው ብቻ መመልከት ቀጠሉ፡፡ “ምናልባት በመቃብሬ ላይ ነው እንጂ በህይወት ቆሜ አንተ የእኔን መፅሐፍ አትወስድም” እንደ ማለት ፍርጥም አሉ፡፡
“በእናንተ ትውልድ ባህል መሰረት … እድሜህን ባትገልጥልኝም … መልካም ልደት ተመኝቼልሀለሁ … መፅሀፍቶቼን ግን አልሰጥህም … የማልሰጥህ ደግሞ እኔ በሄድኩበት መንገድ እንድትጓዝ ስለማልሻ ነው፡፡ ቀስ ብለህ ኑር … ቀስ ብለህ አስብ፡፡ ቀስ ብለህ አስተውል፡፡ እና ለራስህ እምነት የሚመጥን ፈጣሪ ላይ ድረስ፡፡ መድረስ ባትችል እንኳን ወደ ኋላህ ተመልሰህ “ተሳስቼ ነበር” የማያስብልህን መንገድ ያዝ፡፡ በፍጥነት ቸኩሎ መውጣት ወደ ወጣህበት በስተርጅና የሚመልስህ ከሆነ፣ መሄድ የዜሮ ድምር ዋጋ ነው የሚኖረው … በሰዓቱ መጥተህ መፅሐፉን ስለመለስክልኝ ሳላመሰግንህ አላልፍም …” አሉና ወጣቱን አሰናበቱት፡፡ ወጣቱ የተናገሩትን አልሰማም፡፡ የሚጋልብ ደሙ ጆሮውን ደፍኖታል፡፡ ዋናው ፍላጎቱ ማንበብ ነው። ማንበብና አዛውንቱ ተጉዘው የደረሱበት ላይ ደርሶ ተስፋ አለመቁረጥ። የሽማግሌውን ስህተት በትኩስ ኃይልና ተስፋ ማደስ። መታደስ እንደሚችል እርግጠኛ ነበር። ሽማግሌው ገና ባይሞቱም በወጣቱ አይን ግን እንደ አስከሬን ተቆጥረዋል፡፡ ባይሞቱም ሞተዋል። ሐውልት ሊሆኑለት እንኳን አይችሉም። ከሽማግሌው የሚፈልገው ነገር መፅሐፎቻቸውን ብቻ ነበር፡፡ ምናልባት ሲሞቱ ያወርሱኝ ይሆናል የሚል የተስፋ ጭላንጭል በውስጡ ተቀጣጥሏል። መፅሐፍቱን ሊያወርሱት እንዲችሉ የስሜት ቀብድ በሰውዬው ውስጥ ማሳደር ይኖርበታል፡፡ ሰውየው የሀሳብ እንጂ የአካል ልጅ አላፈሩም፡፡ ምናልባት የአካል ልጅነትን ተውኔት ለራሱ ፅፎ እስኪሞቱ ቢጫወት መፅሐፍቱን ጥለውልን ይሞታሉ ብሎ በማሰብ የልደት ቀኑን አሳለፈው፡፡
… ከዚህ ባሻገር የልደት ትርጉም ለእሱ የተለየ ፍቺ አልነበረውም፡፡ እድሜው 25 ---- ደሙም የስሜት የደም ግልቢያ የፈጠነ ነበር፡፡ ሰክኖ ለማሰብ የሚያስፈልገው እድሜ ስንት እንደሆነ የማወቂያ አቅም አልነበረውም፡፡    

Read 1888 times