በኮንፌደሬሽን ካፕ የሚሳተፈውና የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካን የሚያስተናግደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የግብፁን አልአሃሊ የሚገጥመው ኢትዮጵያ ቡና ይሆናል፡፡ በ27 ነጥብ ፕሪሚዬር ሊጉን መምራት የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን ቡና ደግሞ በሊጉ በ19 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ሁለቱም ክለቦች በሜዳቸው ለሚያደርጉት ወሳኝ ኢንተርናሽናል ግጥሚያ በፕሪሚዬር ሊግ ወቅታዊ አቋም ዝግጅታቸው ተወስኗል፡፡ ቡና ከሱዳኑ ክለብ አልሜሪክ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ፈልጎ ነበር፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ሁለተኛ ዙር መጀመሩ፤ የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት ላለማስተጓጐልና የጥሎ ማለፍ ውድድር ለመጀመር በተያዙ እቅዶች ሳቢያ በአዲስ አበባ ስታድዬም ጨዋታውን የማስተናገድ እድል በፌዴሬሽኑ ተከልክሏል፡፡ በሌላ በኩል በሊጉ ከአየር ኃይል ጋር የሚያደርገው ተስተካካይ ጨዋታ ጊዮርጊስን አስጨንቆታል፡፡ በገለልተኛ ሜዳ ይደረጋል የተባለው ጨዋታው በድሬዳዋ እንዲካሄድ በፌደሬሽን መወሰኑ ደስተኛ አይደለም፡፡ ይሄው ተስተካካይ ጨዋታ ሃዋሳ ቢደረግ እያለ ነው፡፡ በተስተካካይ ጨዋታ የሚደረግ ረጅም ጉዞ መከናወኑ ተጨዋቾቹ ለኢንተርናሽናል ግጥሚያ የሚኖራቸው ብቃት ያዳክማል በሚል አማርሯል፡፡