Sunday, 26 February 2017 00:00

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ የድንበር ግጭት እንደቀጠለ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)


      - በየቀኑ የሰው ህይወት እየጠፋ ነው
     - የኦሮሚያ ክልል ጥቃት እየተፈፀመብን ነው ብሏል
       - ተቃዋሚዎች የኦሮሚያና የሱማሌ ክልል ድንበር ግጭት አሳስቦናል አሉ
                       
     በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ድንበር አዋሳኝ ወረዳዎች የተፈጠረው ግጭት አሁንም ቀጥሎ በየቀኑ የሰዎች ህይወት እየቀጠፈ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል “ጥቃት እየተፈፀመብኝ ነው” ብሏል፡፡
በአሁን ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት የማረጋጋት ስራ እየሰራ መሆኑንም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ ምንጮች በግጭቱ ከ70 ሰው በላይ ህይወት ማለፉን የገለፁ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግስት በበኩሉ፤ የጠፋውን የሰው ህይወትና የወደመውን ንብረት በተመለከተ ኮማንድ ፖስቱ እየተከታተለው ነው በማለት የጠፋውን የሰው ህይወት መጠን ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡
እስከ ሐሙስ ድረስ ጥቃቱ ቀጥሎ የሰው ህይወትም እየቀጠፈ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ “የሰው ህይወት መጥፋቱ በእጅጉ ያንገበግበናል፣ ችግሩ በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል፡፡
ጥቃቱን የሚፈፅሙ ኃይሎች መነሻቸውን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያደረጉ መሆናቸውን የገለፁት የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ፤ በተለያዩ 14 ወረዳዎች ጥቃት እየፈፀሙ ንብረት እየዘረፉ፣ የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ሲደርሱ አካባቢውን ለቀው እንደሚሄዱ አስረድተዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎች ማለትም በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ቁምቢ፣ ጭናቅሰን ሚደጋ ቶላ፣ ጉርሱም፣ መዩ ሙሉቄና ባቢሌ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ቦርደዴ ወረዳ፣ በባሌ ዞን ዳዌ ሰረር ሰዌና፣ መደወላቡ እና ራይቱ ወረዳዎች፣ በጉጂ ዞን ጉሚ፣ ኢዲሎና ሊበን ወረዳዎች በቦርና ዞን ሞያሌ ወረዳዎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑን አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡
የጥቃት ፈፃሚዎቹ አላማ ወሰን የማስፋፋትና ኢኮኖሚያዊ ዘረፋ መሆኑን የገለፁ አቶ አዲሱ፤ “ጥቃቱ በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል አይችልም፤ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ድንበሮች ለተፈጠረው ግጭት እስካሁን መፍትሄ አለመበጀቱ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልፀው አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር፣ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስና የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ የተባሉ 4 ድርጅቶች ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ፤ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ የተቀሰቀሰውና ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ያለው ግጭት ከድብቅነት ወጥቶ ወደ ግልጽ ወረራ እየተሸጋገረ ነው ብለዋል፡፡ አላማውም የኦሮሞን መሬት መያዝ እንደሆነ ፓርቲዎቹ ጠቅሰው፤ ለድርጊቱ የሶማሌ ክልል መንግስት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ በታጠቁና ወታደራዊ ዩኒፎርም በለበሱ ኃይሎች ታግዞ የሚካሄድ መሆኑንና የሶማሌ ክልል ባንዲራን በመትከል እንደሚከናወን በመጥቀስ፤ የሶማሌ ክልል መንግስት እጅ አለበት ብለዋል፡፡
ግጭቱ የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች የድርቅ አደጋ የተከሰተባቸውና የሰውና የእንስሳት ህይወት አደጋ ላይ የወደቀ በመሆኑ፣ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚያደርገው ፓርቲዎቹ በአቋም መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ ግጭቱ የህዝብ ለህዝብ አለመሆኑን በአፅንኦት ያስታወቁት ፓርቲዎቹ፤ የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ለችግሩ እልባት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ለተጎጂዎቹ ካሳ እንዲከፈልና እርቀ ሰላም እንዲወርድ እንዲሁም ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ሰላማዊ ድርድር መካሄድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፤ ግጭቱ በታጠቁ ኃይሎች የታገዘ፣ የድንበር ማስፋፋት ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት ጋር ባደረገው ውይይት፣ የክልሉ መንግስት ድንበር የማስፋፋት ፍላጎት እንደሌለውና የታጠቁ ኃይሎቹንም እንደማያውቃቸው ማስረዳቱን ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስትን አቋም ለመጠየቅ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ወደ ክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡

Read 11484 times