Sunday, 26 February 2017 00:00

የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ ድርድር ሊካሄድ እንደማይገባ ‹‹አረና›› አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   ‹‹በተለይ ዶ/ር መረራ ጉዲና መፈታት አለባቸው››
                           
     በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮች ሳይፈቱ ተቃዋሚዎች ከገዥው ፓርቲ ጋ የሚያደርጉት ድርድር ተቀባይነት እንደማይኖረው አረና ትግራይ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በተለይ ከአረና ጋር የመድረክ አባል የሆነው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ም/ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የፖለቲካ አመራሮች በእስር ላይ ሆነው ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት ድርድር ግቡን አይመታም ብለዋል፡፡
ፓርቲያቸው አረና መድረክ ይህን ቅድመ ሁኔታ እንዲያጤን ግፊት እንደሚያደርግ የጠቆሙት አቶ አብርሃ፤ እውነተኛ ድርድር የሚካሄድ ከሆነ፣ የታሰሩ ፖለቲከኞች በቅድሚያ ከእስር መፈታት አለባቸው ብለዋል፡፡ የኦፌኮ አመራር አባል የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገሞታ በበኩላቸው፤ በአሁን ወቅት ዶ/ር መረራን ጨምሮ የፓርቲያቸው ከግማሽ በላይ አመራር በእስር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ አድማስ ጠቁመው፤ ፓርቲያቸው በድርድሩ በሙሉ ስሜትና አቅም እየተሳተፈ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲው በአሁኑ ወቅት መደበኛ የፖለቲካ ተግባሮቹንም ለማከናወን መቸገሩን አቶ ጥሩነህ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 4117 times