Monday, 27 February 2017 08:04

21ኛው የአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተከፈተ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት “ኮንዲዩሲቭ ኢንቫይሮመንት ፎር ኢንሃንስድ ኤክስፖርት ፐርፎርማንስ) በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው 21ኛ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከትናንት በስቲያ ተከፈተ፡፡
አገር ውስጥ ያሉ የንግድ ሰዎችን ከውጭ አገር አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስተዋወቅና የአባላቱን አቅም ለማሳደግ የሚሰራው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ባዘጋጀው 21ኛው የንግድ ትርዒት፤ 100 የውጭ አገራትና 80 የአገር ውስጥ በአጠቃላይ 180 ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከውጭ ኩባንያዎች 50 ያህሉ ከኢጣሊያ የመጡ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከየካቲት 16 እስከ 22 ቀን 2009  በሚቆየው የንግድ ትርዒት፤ ከ27 የውጭ አገራት፣ ኢጣሊያ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሱዳን፣ ዱባይ … እንዲሁም ከአገር ውስጥ የተውጣጡ… 180 ኩባንያዎች በአገልግሎት፣ በንግድ፣ በማኑፋክቸሪንግ በትርዒቱ የሚሳተፉ ሲሆን የኢጣሊያ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው የም/ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሚዲያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ማሞ ገልጿል፡፡
የንግድ ትርዒቱን በክብር እንግድነት መርቀው የከፈቱት የንግድ ሚ/ር ዴኤታው አቶ አሰድ ዚያድ ሲሆኑ የንግድ ም/ቤቱ የቦርድ አባላት፣ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ አባላት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ንግድ ም/ቤቱ በቅርቡ ዓለም አቀፍ የእርሻና ምግብ ትርዒት በሚያዝያ፣ የማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በሰኔ እንደሚያካሂድ ታውቋል፡፡ እንዲሁም የንግድ ም/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንን ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለመገንባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ‹‹ፋይራ ባርሴሎና›› ጋር መስማማቱን አስታውቀዋል፡፡   

Read 1453 times