Saturday, 17 March 2012 10:59

የኡጋንዳው አማፂ ቡድንና አቻ ያልተገኘለት አረመኔያዊ ተግባሩ

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(0 votes)

“የተቆለፈውን አፍህን ሙሴቪኒ ይክፈትልህ!”

ላለፉት 20 ዓመታት በሰሜን ዩጋንዳ ጫካ ውስጥ ሸምቆ በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ፍዳቸውን ሲያበላ የኖረው “ሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚ” ከባእድ አገር የመጣ አማፂ አይደለም፡፡ ከዚያው ከኡጋንዳ አብራክ ከሰሜን ዩጋንዳ የወጣ ነው፡፡ የዚህ አማፂ ቡድን መሪ ጆሴፍ ኮኒ፤ ለማሰብ እንኳ የሚያዳግቱ አረመኔያዊ ድርጊቶችን በነዋሪው ላይ ሲፈፅም ራሱን በፈጣሪ እንደተላከ አድርጐ በመቁጠር ነው፡፡“ፈጣሪ እንድቀጣው የሰጠኝ ህዝብ ነው፤ ለሠራው ጥፋት መቀጣት ይገባዋል” የሚለው ህዝብም ሌላ ሳይሆን በሰሜን ዩጋንዳ የሚገኝ የአቾሊ ህዝብ ነው፡፡ ጆሴፍ ኮኒ ባለፉት ዓመታት በሰሜን ዩጋንዳ የፈፀመው ግፍና በደል ለጆሮ የሚዘገንንና በማንም ቢሆን ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ነው፡፡ የጆሴፍ ኮኒና የተከታዮቹ ዋነኛ ኢላማዎች ህፃናት ሲሆኑ አማፂ ቡድኑ የስድስት ወር ህፃን ልጅ ሳይቀር አፍኖ ይወስዳል፡፡ መታዘል ያልጠገቡ ህፃናትን የጦር መሳሪያ እንዲያነግቡ ያደረገው ቡድኑ፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በሌሊት አፍኖ በመወሰድ ለውትድርና ያሰማራል፡፡

ህፃናቱ ጭካኔን እንዲማሩ እርስ በርሳቸው በማታኮስ እንዲገዳደሉ ማድረጉም ይነገርለታል፡፡ ሀይማኖታዊ ተልዕኮ እንዳለው የሚናገረው ኮኒ፤ ከእግር ውጪ በሌላ ተሽከርካሪ ሲዘዋወር የተገኘን ግለሠብ እግር እንደሚቆርጥ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ባል በቢስኪሌት፣ ሚስት በእግር ሲጓዙ ያገኙት የአማፂያኑ ጎረምሶች፤ ሚስትየዋ የባሏን እግር እንድትቆርጥ መጥረቢያ ይሰጧትና አላደርገውም ካለች ግን የሁለቱም እጣፈንታ ሞት እንደሚሆን ይነግሯታል፡፡ ምንም ምርጫ ያልነበራት ሚስት፤ የባሏን እግር በመጥረቢያ ቆረጠች፡፡ አያችሁ ጭካኔ! አማፂያኑ በሌሊት በሚፈፅሙት ሰሜን ዩጋንዳውያንን የማሸበር ስራ ላይ ሳሉ፣ አንድ የአስራ አራት አመት ልጅ በቁጥጥራቸው ሥር ያውሉና ወደ ካምፓቸው ይዘውት ከመሄዳቸው በፊት፣ የአባቱን አፍ በስቶ በቁልፍ እንዲቆልፍ ያዙታል፡፡ ልጁ የተባለውን ባይፈፅም የሚከተለውን ቅጣት ስለነገሩት፣ እየሰቀጠጠውም ቢሆን የታዘዘውን ፈፀመ፡፡ ከዚያም አባቱን “የተቆለፈውን አፍህን ሙሴቬኒ ይክፈትልህ” ሲሉ አላግጠውበት ልጅየውን ይዘው ሄዱ፡፡ በሰሜን ዩጋንዳ በምትገኘው ጉሉ ከተማ በሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የምትኖር አንዲት ሴት፣ የደረሰባትን ግፍ “ሰው በሰው ላይ ሊፈጽመው የማይችል አረመኔያዊ ድርጊት” ስትል ገልፃዋለች፡፡ በኮኒ እና በአዛዦቹ ትዕዛዝ ከዚያው አካባቢ ተጠልፈው አረመኔያዊ ድርጊት እንዲፈጽሙ የተላኩ ህፃናት አማፂያን፤ ወደ ቤቷ ይሄዱና አፍንጫዋን ከቆረጧት በኋላ እንድትበላው አዘዟት፡፡ በደም ከሰከሩትና በውስጣቸው ቅንጣት ታህል ርህራሄ እንዳይኖር ተደርገው ከተቀረፁት የልጅ ልጆቿ የሚሆኑ ህፃናት፣ የሚሰጣት ምላሽ ሞት መሆኑን የምታውቀው ሴት የተባለችውን ፈፀመች፡፡ የተቆራረጠውን የአፍንጫዋን ስጋ ቆመው አስበሏት፡፡ ቡድኑ ህፃናትን ጠልፎ በሚወስድ ወቅት ዳግመኛ ስለቤተሰቦቻቸው እንዳያስቡ የዘየደው መላ ራሱ አሰቃቂ ነው፡፡ ህፃናቱ ወላጆቻቸውን እንዲገድሉ ያደርጋል፡፡ ይሄም ካልሆነ የአማፂው አባላት ወላጆቻቸው ላይ አረመኔያዊ ድርጊት ይፈፅማሉ - ህፃናቱ እያዩ፡፡ ይሄ አማፂው ቡድን ህፃናቱ ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸውን ስሜታዊ ትስስር ለመበጠስ የሚጠቀምበት ዋነኛ ስትራቴጂ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አለም ደንታዬ ያለው በማይመስለው የሰሜን ዩጋንዳ ግዛት፣ ጆሴፍ ኮኒ እና ተከታዮቹ የዘረፉትን ዘርፈውና የገደሉትን ገድለው ወደ ካምፓቸው ሲመለሱ፣ የጠለፏቸው ህፃናት ሴቶች ለብቻቸው ተለይተው እንዲቆሙ ይደረግና በመጀመሪያ የአማፂ ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ሚስት እንዲመርጡ ይደረጋሉ፡፡ ከዛ ውጪ ያሉት “ሎተሪ” በሚባል የመረጣ ስርዓት፣ ለተቀሩት የቡድኑ አባላት በሚስትነት ይከፋፈላሉ፡፡ “ሎተሪ” የሚባለው የጋብቻ ስርአት ለህሊና የሚከብድ ቢሆንም የቡድኑ የጫካ ህግ ሆኖ ሲሰራበት ብዙ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ሥርዓቱ እንዲህ ነው፣ የአማፂው ወታደሮች ሸሚዛቸውን ወይም ጃኬታቸውን አንድ ቦታ ያስቀምጣሉ፡፡ ከዛም ሴቶቹ ያሻቸውን እንዲያነሱ ይደረጋል፡፡ ያነሱት ጃኬት ባለቤትም ባላቸው ይሆናል፡፡ የሎተሪ ጋብቻ ማለት ይሄው ነው፡፡ ጆሴፍ ኮኒ እና የቡድኑን አዛዦች ለመያዝ፣ የዩጋንዳ ጦር በየጊዜው የተለያዩ ሙከራዎችን ያደረገ ቢሆንም ጥረቱ ፍሬ አልባ ነው፡፡ በሰሜን ዩጋንዳ ጫናው የበዛባቸው ኮኒ ግን ለተወሰኑ ጊዜያት በኮንጎ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ እና በደቡብ ሱዳን አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ይሄ  አማፂ ቡድን፣ በአልበሽር መንግስት ድጋፍ ይደረግለት የነበረ ሲሆን የዩጋንዳ መንግስት በበኩሉ የደቡብ ሱዳን አማፂ የነበረውንና አሁን የደቡብ ሱዳን መንግስትን የመሠረተውን ቡድን ይደገግፉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን “አፍሪካን ዩዝ ኢኒሼቲቭ ኔትወርክ” በሚባል ድርጅት ስለ ጆሴፍ ኮኒ ተሠርቶ የተለቀቀው ዶክመንታሪ ፊልም በመላው አለም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ፊልሙን ከ77 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የተመለከተው ሲሆን ዶክመንታሪውን በተመለከቱ የአማፂ ቡድኑ የጥቃት ሠለባዎች ዘንድ የፈጠረው ስሜት ግን የተዘበራረቀ ነው ተብሏል፡፡ ሊራ በተባለችው የሰሜን ዩጋንዳ ግዛት የሚኖረውና ዶክመንታሪውን የተመለከተው የአማፂ ቡድኑ የጥቃት ሰለባ አሞደ “ለምን ስቃያችንን እንድናስታውስ እንደረጋለን? ስለ ሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚና ስለ ኮኒ መርሳት እንፈልጋለን” ሲል ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ ንዳንድ ተመልካቾች ፊልሙን ተመልክተው ሲጨርሱ፣ ሲንቀጠቀጡና በመጥፎ ስሜት ተውጠው ታይተዋል፡፡ የሰዎችን አካል በአሰቃቂ መንገድ በመቆራረጥ፣ ህፃናትን ለውትድርናና ለወሲብ ባርነት በመዳረግ ኢ-ሰብአዊ ተግባራቸው ዓለም የሚያውቃቸው ጆሴፍ ኮኒ እና አዛዦቹ፣ በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተፈላጊ ቢሆኑም  አሁንም ድረስ በመሸጉበት ጫካ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አማፂያኑን በቁጥጥር ስር ለማዋል አሜሪካ የኡጋንዳ ጦር ሠራዊትን የሚያማክሩ ባለሙያዎችን

 

ብትልክም የመሸጉበትን ጫካ የሚደፍር አልተገኘም፡፡ ቀደም ባሉት አመታት ከአማፂ ቡድኑ ጥቃት በመሸሽ፣ በተፈናቃዮች ካምፕ በመኖር ላይ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ምንም የሚተማመኑበት ነገር የላቸውም፡፡ ኮኒ ለጊዜው ከአካባቢው ቢርቅም ተመልሶ መጥቶ እንደፈለገ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ያውቃሉ፡፡ አማፂ ቡድኑ “የአቾሊን ህዝብ እንድቀጣው ከፈጣሪ ትዕዛዝ ተሠጥቶኛል፤ የዚህ ህዝብ መተዳደሪያም አስርቱ ቃላት መሆን አለበት” የሚለውን ማወናበጃውን አንዳንድ ነዋሪዎች ከተስፋ መቁረጥ ብዛት የማመን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ይነገራል፡፡ ነዋሪዎቹ ስለኮኒ ሲያወሩ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ነው፡፡ “ተመልሶ ሲመጣ ሊበቀለን ይችላል” የሚል ከፍተኛ ስጋትና ፍራቻ አላቸው፡፡ ግን አይፈረድባቸውም፡፡ 20 ዓመት ሙሉ የራሳቸው መንግስትም ሆነ ሌላ አካል ከዚህ አረመኔ ግለሰብና ከአማፂ ቡድኑ የጭካኔ ተግባር ማንም አላዳናቸውም፡፡ ስለወደፊቱም ቢሆን በእርግጠኝነት የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ እነዚህን ህዝቦች የሚታደገው ማን ይሆን? መቼ?

 

 

Read 4408 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:46