Monday, 27 February 2017 08:14

አዲስ አበባ የቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ቀዳሚ ሆናለች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  · ሀዋሳና ቢሾፍቱ ይከተላሉ
                    · 12 ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ሊገነቡ ነው
                              
     ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት እያሳየ ነበር፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በአገሪቱ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ለመዝናናትና ለኮንፈረንስ ለሚመጡ ቱሪስቶች ዋነኛ ስጋት ሆኖ እንደነበር “ጁሚያ ትራቭል” አስታውቋል፡፡
ጁሚያ ትራቭል “የእንግዳ አቀባበል (Hospitality)” በሚል ርዕስ፣ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታዩ ስኬቶችን፤ ድክመቶችንና ያልተነካ የወደፊት ዕጣ ፈንታዎችን የዳሰሰበትን  ሪፖርት ባለፈው ሳምንት በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ይፋ ባደረገ ወቅት የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ፓል ሚዲ፤ ‹‹በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ብዙ ናቸው፤ ነገር ግን ለወደፊት ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ይታያሉ፡፡ አገሪቷ ለቱሪስቶችና ለዜጎቿ ደህንነት ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ስለሆነ ስጋቱ እየተቀረፈ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም የሚፈለገውን ዕድገትና ብልፅግና እውን ለማድረግ እንሠራለን›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በዘርፉ የተደረገው ኢንቨስትመንት የ3.7 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የጠቀሰው ጁሚያ ትራቭል፣ በዓመቱ ከ800 ሺህ በላይ ቱሪስቶችን ኢትዮጵያን ጎብኝተው 128 ቢሊዮን ብር (5.6 ቢሊዮን ዶላር) መገኘቱን አመልክቷል፡፡ ነገር ግን የጎብኚዎቹ ቁጥር በወዲያኛው ዓመት (2015) ከነበረው 900 ሺህ መቀነሱን አልሸሸገም፡፡
በቱሪስቶች የሆቴል ፍላጎት አዲስ አበባ 39 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ናት፡፡ ሀዋሳ በ11.2 በመቶ ሁለተኛ፣ ቢሾፍቱ ደግሞ 8.1 በመቶ በመያዝ ሦስተኛ ናት፡፡ ባህር ዳር 7.5 በመቶ፣ ጎንደር 5 በመቶ፤ አዳማ 4.6 በመቶ፣ መቀሌ 4.1 በመቶ፣ ላሊበላ 3.8 በመቶ፣ አክሱም 3 በመቶ በመያዝ ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ከእነዚህ ጎብኚዎች 31 በመቶ በመያዝ አፍሪካውያን ቀዳሚ ናቸው። 30 በመቶ ቱሪስቶች አውሮፓውያንና ሰሜን አሜሪካውያን ሲሆኑ ያገር ውስጥ ቱሪስቶችም ቁጥር እየጨመረ ነው ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
ኢትዮጵያውያን አገር ጎብኚዎች የሚመርጡት 37 በመቶ ባለ 2 ኮከብ ሆቴሎችን ነው፤ 36 በመቶ ደግሞ ባለ 3 ኮከብ ሆቴሎች ሆኗል፡፡ ወጪ ለመቀነስ የሚጥሩ ጎብኚዎች ጧት ቁርስ፤ ዋይ ፋይ፤ የመዋኛ ገንዳ፣ ጂምና አውሮፕላን ጣቢያ የሚያደርሳቸው መኪና ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ከፍተኛውን ገንዘብ - 68.7 በመቶ የሚከፍሉ የውጭ አገር ጎብኚዎች ሲሆኑ ከአገር ውስጥ ጎብኚዎች የሚገኘው ክፍያ 31.3 በመቶ ነው፡፡ አብዛኞቹ ቱሪስቶች - 59 በመቶው ገንዘብ የሚከፍሉት በኢንተርኔት አልጋውን ሲይዙ ነው፡፡ 41 ከመቶዎቹ ግን ገንዘብ የሚከፍሉት ሆቴል ሲደርሱ ነው፡፡
ሪፖርቱ ስለቱሪስቶች ማረፊያ ሆቴሎችም አትቷል፡፡ ባለፈው ዓመት (2016) ወደ ገበያው የገቡት ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች ሁለት ሲሆኑ እነሱም ራማዳ አዲስና ማሪዮት አፓርትመንት ናቸው፡፡ እንዲሁም አምስት ዓለም አቀፍ ብራንድ የሆኑ ሆቴሎች እየተገነቡ ነው፡፡ አገሪቷ በቅርብ ዓመታት 58,000 ክፍሎች ያላቸው ሆቴሎች ለመክፈት እየሠራች ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 2,460 ክፍሎች ያላቸው 12 ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ወደ ገበያው ለመግባት እያኮበኮቡ ናቸው፡፡
አምና (2016) በአማካይ 14 ደረጃቸውን የጠበቁ ክፍሎች ያላቸው 67 የእንግዳ ማረፊያዎች በአዲስ አበባ  ከተማ ተሠርተዋል፡፡ የእነዚህ እንግዳ ማረፊያዎች የያዙት ትልቅ መኝታ 32 ክፍሎች ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ 22 ደረጃቸውን የጠበቁና ቅንጡ ሎጆች በኢትዮጵያ እንዳሉ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ባለፈው ዓመት ዓለም አቀፍ ብራንድ የሆኑ ክፍሎች ያላቸውን ሆቴሎች በብዛት በመገንባት ኢትዮጵያና ኬንያ ከ10 የአፍሪካ አገራት አንዱ ሆንዋል፡፡ በኢትዮጵያ 12፣ በኬንያ ደግሞ 16 ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች እየተገነቡ ነው። ኢትዮጵያ የኮከብ ደረጃ የላቸውን ሆቴሎችና ሎጆች ቁጥር ለማሳደግና 1000 ለማድረስ ኢንቨስተሮችን የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በማቅረብ እማለለች ነው፡፡ አንደኛው ዘዴ ታክስ ነው፡፡ የውጭ ኢንቭስተሮች የውጭ ምንዛሪ (ካፒታል ጉድስ) ይዘው ሲገቡ ከታክስ ነፃ ናቸው። መሬትም ይዘጋጅላቸዋል፣ የባንክ ብድርም ይመቻችላቸዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝምና ሚ/ርም በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰሩ 2,620 ኩባንያዎች የጥራት ደረጃ ሰርተፌኬት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በ2016 ዓ.ም የአፍሪካ ኅብረትን ትልቅ ሆቴል ጨምሮ፣ ለ1,800 አዲስ ኢንቨስትሮች፣ ለክራውን ፕላዛ፣ ለፑልማን፣ ለውንድሃም ሆቴል ግሩፕ፣ ለአኮርድ ግሩፕ፣ ለቤስት ዌስተረን ቅንጡ ሆቴሎች እንዲሰሩ ፈቃድ ተሰቷል፡፡
በኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት የሚበዛው ከኅዳር እስከ ጥርና ሐምሌና ነሐሴ እንደሆነ የጠቀሰው ሪፓርቱ ዋናው ምክንያት ለመዛናናትና በዓላትን ለማክበር እንደሆነ አመልክቷል፡፡

Read 1209 times