Monday, 27 February 2017 08:16

ንግድ ባንክ በ6 ወር ከታክስ በፊት 7.8 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘንድሮ የግማሽ ዓመት (6 ወራት) የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ውጤት በአብዛኛው መልካም እንደሆነ ገልጿል፡፡ ባንኩ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ ስለ ዕቅዱ ባይጠቅስም የባንኩ ማኔጅመንት ከጥር 18-20 2009 በሀዋሳ ከተማ ባካሄደው የሥራ እንቅስቃሴ ግምገማ፣ በግማሽ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት፣ 416.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን፤ ካደረገው አጠቃላይ እንቅስቃሴ 15.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንና በ6 ወር ከታክስ በፊት 7.8 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ 31.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን የጠቀሰው ባንኩ፤ይህም ክንውን የባንኩን ጠቅላላ ተቀማጭ ሰኔ 30 ቀን 2008 ከነበረበት 288.5 ቢሊዮን ብር ወደ 320.2 ቢሊዮን ብር እንዳሳደገው ገልጿል፡፡ ከተቀማጭ ገንዘብ እንዲሁም ከብድር አሰባሰብ የተገኘውን ገንዘብ መልሶ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በብድር መስጠት የባንኩ ተግባር እንደሆነ ጠቅሶ፣ በግማሽ ዓመት 28.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና 40.4 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች መስጡን አመልክቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ በ6 ወር ውስጥ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን፣ ከዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ ድርሻ 332.5 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በሀዋላ ወደ ሀገር ውስጥ የተላከው 1.9 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን ከተጠቃሚው ኅብረተሰብ በቅርብ ርቀት ለማድረስ በሚያደርገው ጥረት በግማሽ ዓመቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት ብዛታቸውን 1150 ማድረሱን፣ የኤሌክትሮኒክስ የባንክ አግልግሎትን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን፣በግማሽ ዓመቱ 266 ኤቲኤምና 239 የፖስ ማሽኖችን በመገበያያ ስፍራ በማኖር፣ የኤቲኤሞችን ቁጥር 1155፤ የፓስ ማሽኖችን 6,508 ማድረሱን አስታውቋል፡፡ በ6 ወራት ውስጥ 807,831 ካርዶችን በመስጠት የባንኩን ካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር 3,298,826 በማድረስ በቅርጫፎች አካባቢ የሚታየውን የተገልጋዮች ቁጥር መቀነስ መቻሉን፤ 377,7849 አዲስ የሞባይል ባንክ አገልግሎት ፈላጊዎችን በመመዝገብ ጠቅላላ የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች ቁጥር 1,262,399፣ የኢንተርኔት ባንክ ተጠቃሚዎችን 19,144 ማድረሱን አስታወቋል፡፡

Read 1728 times