Monday, 06 March 2017 00:00

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በድርድሩ አላማ ላይ ተስማሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  በቀጣዩ ቀጠሮ በድርድሩ እነማን ይሳተፉ በሚለው ላይ ይነጋገራሉ
                       
       ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ለ4ኛ ጊዜ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትናንት ተገናኝተው “በክርክርና ድርድሩ አሰራር ደንብ” ላይ የተነጋገሩ ሲሆን በድርድሩ አላማ ላይ እንደተስማሙ ተገልጿል፡፡ የንግግራቸው ሂደት ምን ተብሎ ይጠራ በሚለው ላይ ግን መስማማት ሳይችሉ በይደር አቆይተውታል።
በገዥው ፓርቲ መድረክ መሪነት በተካሄደው የትናንቱ ውይይት ላይ፣ የሂደቱ አላማ ወይም “ከገዥው ፓርቲና ከተቃዋሚዎች የንግግር ሂደት ምን ውጤት ይገኝ” በሚለው ላይ ከየፓርቲዎች የቀረቡ 4 ነጥቦችን፣  የድርድሩ አላማ እንዲሆኑ ተስማምተዋል፡፡
በድርድሩ ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ነጥቦችን እንደ ግብአት በመጠቀም፣ መሰረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ህጎችና ድንጋጌዎች እንዲሻሻሉ ማድረግ፣ የፓርቲዎችን ዲሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር፣ ለሀገራችን ሰላም ዲሞክራሲና እድገት የሚኖራቸውን ሚና ማጎልበት፣ ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሀሳብ ተገንዝቦ በእውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት፣ የመድብለ ፓርቲ ስርአቱ እውን እንዲሆንና እንዲዳብር ማድረግ… የሚሉት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው የድርድሩ አላማ ሆነዋል፡፡
በትናንቱ የፓርቲዎቹ ድርድር ሰፊ ጊዜ የወሰደው፣ የሂደቱ መጠሪያ ምን ይሁን የሚለው ሲሆን መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና መኢአድን ጨምሮ አብዛኞቹ ፓርቲዎች፤ “ድርድር” መባል አለበት ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ “ውይይት” እና “ክርክር” መባልም አለበት ብለው ተከራክረዋል፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ፤ “ውይይት፣ ክርክር፣ ድርድር… ሶስቱም ይስማማኛል” ብሏል፡፡
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ ባለመደረሱም የክርክርና የአሰራር ረቂቅ ደንቡ ላይ ከተነጋገሩ በኋላ መጠሪያው ሊወሰን ተስማምተው፣ ጉዳዩን በይደር አቆይተዋል፡፡  በቀጣይ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ለመገናኘት የተቀጣጠሩ ሲሆን በእለቱም በተያዘው አጀንዳ ቅደም ተከተል መሰረት፣ በድርድሩ የትኞቹ ፓርቲዎች ይሳተፉ በሚለው ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

Read 2252 times