Monday, 06 March 2017 00:00

መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 መኢአድ አባላቱ እንዲፈቱለት ለኮማንድ ፖስት አቤቱታ አስገብቷል
                                
     የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮችን በመፍታት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስተካከል የገባውን ቃል እንዲፈፅም የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ “ሂውማን ራይትስ ዎች” ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ፡፡
በሀገሪቱ የተከሰተውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ መንግስት የፖለቲካ ለውጦችና ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቃል መግባቱን ያስታወሰው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ሆኖም የገባውን ቃል እየጠበቀ አለመሆኑን ጠቁሞ፣ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ምክትላቸው አቶ በቀለ ገርባን በእስር ማቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የጀመረው ድርድር ሀቀኝነት በዚህ ምክንያት አጠያያቂ መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ መሰረታዊ የፖለቲካ መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮችን ከእስር በመልቀቅ ቁርጠኝነቱን እንዲያረጋግጥ ጠይቋል፡፡
“በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ከሰሞኑ የቀረበው ክስም፣ መንግስት አሁንም የተለያዩ አስተሳሰቦችን በቀናነት ለማስተናገድ ፍላጎት እንደሌለው ያመላክታል” ብሏል፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፡፡
ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ በበኩላቸው፤ በአባሎቻቸው መታሰር በእጅጉ መማረራቸውን ገልፀው ባለፉት 3 ወራት ከአስር በላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና የወረዳና የዞን አስተባባሪዎች መታሰራቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የታሰሩባቸውን አመራሮች ስም ዝርዝር ከሰሞኑ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በደብዳቤ በማሳወቅ እንዲለቀቁላቸው ጠይቀው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አቶ አዳነ ጥላሁን ለአዲስ አድማስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“መኢአድ በድርድሩ ሁሉንም እድሎች አሟጦ ለመጠቀም ወስኗል” ያሉት አቶ አዳነ የፓርቲው አመራሮች እስራት የሚቀጥል ከሆነ፣ በድርድሩ ላይ ጥላ ያጠላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ ከአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማት ጋር ባደረገው ውይይት፣ አሁንም በርካታ አባሎች እየታሰሩበት እንደሚገኝ አስታውቆ፣ አባሎቹም ሆነ የፖለቲካ እስረኞች ካልተፈቱ ወደ ድርድር እንደማይገባ ገልጿል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች መፈታትን የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ እንደሚያስቀምጥ ፓርቲው በአፅንኦት አስገንዝቧል።
ሂውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሚያወጣቸውን ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሪፖርቶችና መግለጫዎችን መንግስት በተደጋጋሚ “ከእውነት የራቀ ነው” በሚል ማጣጣሉ አይዘነጋም፡፡

Read 2246 times