Monday, 06 March 2017 00:00

ከድርቅና ከረሃብ መላቀቅ ያልቻልነው ለምንድነው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • ምርጥ ቦታዎች ላይ ምርጥ አርሶ አደሮች ሄደው መስራት አይችሉም
                • ዩክሬን ድርቅ ቢኖርም ከራሷ አልፋ ለውጪ ገበያ ስንዴ ታቀርባለች
                • ከፖሊሲ ችግር ውጪ ሌላ ሰበብ ሊፈጠርለት አይችልም
                        አቶ ግርማ ሠይፉ (የምጣኔ ሃብት ባለሙያና ፖለቲከኛ)

     ድርቅ በመጣ ቁጥር ለምንድን ነው የረሃብ ስጋት ውስጥ የምንወድቀው?
ይሄ ግልፅ ነው፡፡ የፖሊሲ ችግር ነው፡፡ በኒውክለር ሳይንስ ላንራቀቅ እንችላለን፣ የተለያዩ ነገሮች ላይ ስኬት ላናስመዘግብ እንችል ይሆናል፤ በምግብ ራሳችንን ላለመቻላችን ጉዳይ ግን ከፖሊሲ ውጪ ሌላ ሰበብ ሊገኝለት አይችልም፡፡ ከሌሎች ሃገሮች አንፃር ሲመዘን ድርቅ በሚሆንበት ጊዜ እንኳ መሬታችን ከፍተኛ እርጥበት ነው የሚኖረው፡፡ ይሄን የእርጥበት ሁኔታ ወደ ምግብ አምራችነት መቀየር አለመቻል ሌላ ምንም አይሆንም፤የፖሊሲ ችግር ነው፡፡
የፖሊሲ ችግር ያለው ምኑ ላይ ነው?
ዋናው የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ ከመሬት ፖሊሲው ጋር ተያይዞ፣ ያለንን መሬት በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም፡፡ የገበሬውን ባለቤትነት የማያረጋግጥና ዋስትና የማይሰጥ ፖሊሲ ነው ያለን፡፡ በዚህ የተነሳ ገበሬው ዘላቂ ልማትን በመሬቱ ላይ ለማሠብ አይችልም፡፡ ሌላው የሰው ሃይል ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ሃይሉ በብጥስጣሽ መሬት ላይ እንዲጣበቅ ተደርጓል፡፡ ትክክለኛ ወደ ከተሜነት የመለወጥ የፖሊሲ አቅጣጫ ስለሌለን፣ ገበሬው ያችኑ መሬቱን እየደጋገመ ለማረስ ይገደዳል። አንድ ሰው ሶስት ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ብቻውን ኳስ ሊያንቀረቅብ ይችላል፤ ሶስት ሰው ግን በዚያች ቦታ ላይ ሊያንቀረቅብ አይችልም፤ የመሬቱም ጉዳይ እንደዚሁ ነው፡፡ ገበሬው ትንሽ መሬት ላይ እርስ በእርስ እየተጠባበቀ እንዲኖር ነው የተደረገው። በአጠቃላይ ምቹ የአየር ፀባይ፣ በቂ መሬትና በቂ የውሃ አቅም ባለበት፣ ለምግብ እጥረት መጋለጥ ማለት የምንም ሳይሆን የፖሊሲ ችግር ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ወደ ኢንዱስትሪና ከተሜነት ፈጥነን አለመግባታችን ነው ተጋላጭ ያደረገን?
የድሮውን መርህ ተከትለን መጀመሪያ የብረት ኢንዱስትሪ ከዚያም የግብርና ኢንዱስትሪ የምንልበት ዘመን አብቅቷል፡፡ አብዛኛው ህዝብ መሣተፍ ያለበት በትንንሽ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ መኪናን ሳይሆን ጎማውን ወይም ብሎኑን ማምረት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ሃገሮች እኮ በአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ነው የሚኖሩት። ለምሳሌ ዱባይ የምን ኢንዱስትሪ ነው ያለው? የአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ነው ያላቸው፡፡
ሌላው ባለሃብትም ሆነ ማንኛውም ዜጋ በአገሪቱ እንደ ልቡ ተዘዋውሮ መስራት የሚችልበት ሁኔታ አለመኖሩ እንቅፋት ነው፡፡ ምርጥ ቦታዎች ላይ ምርጥ አርሶ አደሮች ሄደው መስራት አይችሉም። አስታውሳለሁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት አንድ መድረክ ላይ አንድ ባለሃብት፣ መንግስት ስንዴ ለመግዛት ከ10 ወር በላይ እንደሚወስድበት ጠቅሶ፣ ”ስንዴ የምትገዙበትን ገንዘብ ለኛ ድጎማ ብትሠጡን፣ በሃገር ውስጥ አምርተን በአጭር ጊዜ ውስጥ እናደርስ ነበር” ብሏል፡፡ መንግስት ግን ይሄን ለማድረግ አይደፍርም፡፡
ከድርቅ ስጋት ለመውጣት ምንድን ነው መደረግ ያለበት?
በብዙ አገሮች ከፍተኛ ድርቅ ይከሰታል ግን እነሱ ጋ ድርቅን ተከትለው የሚመጡ ችግሮች አይከሰቱም። እኛ ወደዚህ ደረጃ ለመምጣት ያለንን ጥሩ አየር ተጠቅመን፣በቂና የተትረፈረፈ ምርት መያዝ ነው ያለብን፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ምቹ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል፡፡ ግብርናው   ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ ጥቂት ምርጥ ገበሬዎች ናቸው ድጋፍ ተደርጎላቸው፣ የህዝብ ቀላቢ መሆን ያለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ መከተል ያለበት የዩክሬንን ልምድ ነው። ዩክሬን ድርቅ አለ ግን ከራሷ አልፋ ለውጪ ገበያ ስንዴ ታቀርባለች፡፡ ኢትዮጵያም ወደዚህ ደረጃ ነው መምጣት አለባት፡፡

--------------------

              • የባለሀብቶችን በራስ መተማመን የሚያበለፅግ የመሬት ፖሊሲ የለንም
              • ለእርዳታ እጅን እየዘረጉ፣ በምግብ ራሳችንን ችለናል ማለት አስቸጋሪ ነው
              • ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ሰፋፊ መካናይዝድ እርሻዎች ናቸው
                       አቶ አቢስ ጌታቸው (የምጣኔ ሀብት የፒኤችዲ ተማሪ)     
      ኢኮኖሚው በፍጥነት እያደገ ነው ቢባልም ድርቅ ዛሬም ለሀገሪቱ ስጋት የሆነው ለምንድነው?
ይሄ እጅግ በጣም ሰፊ ጉዳይን ያዘለ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲሁ ጠቅለል አድርገን እንየው ከተባለ፣ ኢኮኖሚያችን በራሱ መሰረት ያደረገው ግብርናውን ነው፡፡ ለምን ግብርናው ላይ ጥገኛ ሆንን ካልን፣ ሀገሪቷ አሏት ከሚባሉት ሀብቶች ውስጥ መሬት ዋነኛው ነው፡፡ ካፒታል፣ የሰው ኃይል (የተማረ)፣ መሬት ---- እነዚህ መሰረቱን በግብርና ላይ ላደረገ ሀገር ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች አቀናጅቶ መጠቀም አለመቻላችን ነው እስከ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለን ያለው፡፡ ካፒታልና የተማረ የሰው ኃይል የለንም፤ የሀገሪቱ ብቸኛ ሀብት አሁን ላይ መሬት ነው፡፡ መሬት፣ ተስማሚ የአየር ፀባይና በርካታ ወንዞችና ኃይቆች ቢኖረንም፣ ይሄን አቀናጅቶ መስራት የሚችል የሰው ኃይልና ማሰራት የሚችል ካፒታል ባለመፈጠሩ የተነሳ ግብርናችን ዘምኖ ከድርቅ ሊታደገን አልቻለም፡፡
ሀገሪቷ ያላት መሬትና የመሬት ፀጋዎች ብቻ ናቸው ከተባለ፣ ይሄን ለመጠቀም የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲ ያስፈልገናል፤ እንዳለመታደል ሆኖ ግን እስከ ዛሬ አላገኘንም፡፡ ከንጉሱ ጀምሮ በደርግም ሆነ አሁን፣ለአገሪቱ የተፈጥሮ ፀጋ ተስማሚ የሆነ ፖሊሲ የለንም፡፡ የሚቀረፁ ፖሊሲዎችም ቢሆኑ ወጥነት የላቸውም፡፡ የባለሀብቶችን በራስ መተማመን የሚያበለፅግ የመሬት ፖሊሲ የለንም። ይህ አይነት ፖሊሲ ባለመኖሩ በየዘመናቱ ከሚፈጠረው የድርቅና የረሃብ ስጋት መውጣት አልቻልንም፡፡
ለምሳሌ አሁን ባለበት ሁኔታ መሬት የሚገኘው ሳይንሳዊ እውቀት በሌለው አርሶ አደር እጅ ነው፡፡ እርግጥ ነው መጠነኛ የእውቀት ሽግግር እየተደረገ ነው፤ግን ይሄ አካሄድ በምግብ ራስን ለመቻል በቂ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት Large scale mechanized farm ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሩም እውቀቱም ያለው ጠንካራ ባለሀብት፣ ዋስትና አግኝቶ ኢንቨስት የሚያደርግበት ምቹ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አውስትራሊያ በድርቅ ትጠቃለች ግን ድርቅ ራስምታቷ ሆኖ አያውቅም፡፡ ያለ ስጋት ተቋቁማ ታልፈዋለች፡፡ ምክንያቱም ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ትክክለኛና ውጤታማ የሆነ የመሬት ፖሊሲ አላት፡፡ አሁን ባልተማረና ገንዘብ በሌለው የሰው ኃይል በተያዘ መሬት የሚለማው አዋጪ አልሆነም ካልን፣ ወደ ሌላ መዛወር የምንችልበት ምን አማራጭ አለን? የለንም፡፡ በንጉሱ ጊዜ ባለሀብቱ መሬት እየተከራየ ሰፋፊ እርሻዎችን የሚሰራበት ሁኔታ ነበር፡፡ መሬት ለባለሀብቱ የሚሰጥበት ሁኔታም ነበር፡፡
ባለሀብቱ በሙሉ የራስ መተማመን፣ ምርት ያመርት ነበር፡፡ አሁን ለባለሀብቱ መንግስት መሬት የማከራየት ነገር አለ፤ ግን ይሄ በሚፈለገው መጠን አይደለም፡፡ 90 ሚሊዮን ህዝብን ሊቀልብ በሚችል መልኩ አይደለም እየተሰራ ያለው፡፡
በሌላ በኩል መንግስት “በምግብ ራሳችንን ችለናል” ሲል ይደመጣል… ይሄ ምን ማለት ነው?
በምግብ ራሳችንን ችለናል ማለት እርዳታ ላይ ጥገኛ አለመሆን፣ ራስ አምርቶ በበቂ መጠቀም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ትርጓሜ ስንነሳ፣ ስንዴ ከውጭ እያመጡ፣ ለእርዳታ እጅን እየዘረጉ፣ በምግብ ራሳችንን ችለናል የሚለው አስቸጋሪ ነው። ጉዳዩ ምንም አከራካሪ አይደለም፤ አልቻልንም። ስንዴ ከውጭ እያመጣን ነው፡፡ የጅቡቲ ወደብን እያጨናነቀ ያለው ከውጭ የሚመጣ ስንዴ ነው። ይሄ በሆነበት ሁኔታ እንዴት በምግብ ራሳችንን ችለናል ልንል እንችላለን፡፡
እርስዎ እንደሚሉት ግብርና ውስጥ ገብተው መስራትና የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚችሉ ባለሀብቶች አሉን?
አዎ አሉን! ፖሊሲው ነው ችግር ያለበት፤ አያሰራም፡፡ አንድ ባለሀብት መተማመን ይፈልጋል። የኛ ፖሊሲ ያንን መተማመን የሚፈጥር አይደለም። ደርግ በአንድ ጊዜ ያንን ሁሉ የባለሀብቶች ንብረት መውረሱ ዛሬም ድረስ ተፅዕኖው አለ፤ አሁን የኢኮኖሚ መረጋጋት አለን ማለት አንችልም። አንድ ባለሀብት ኢንቨስት ለማድረግ ደግሞ የኢኮኖሚ መረጋጋትን እንደ ዋስትና ይመለከተዋል። የዋጋ መረጋጋት ይፈልጋል፡፡ የገንዘብ ዋጋ እየወደቀ በሄደ ቁጥር ባለሀብቱ ይሰጋል፡፡ በዚያው ልክ የፖለቲካ መረጋጋቱንም ይፈልጋል፡፡ በባለሀብቱ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ቀላል ዋጋ አያስከፍሉም፡፡ ሌላው የፖሊሲ ወጥነትን በማስፈን፣ መተማመንን መገንባት አለመቻሉ በዚህች ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ መንግስት ባለሀብቱን መተማመን ላይ የሚያደርስና የሚያበረታታ፣ ግልፅና ወጥነት ያለው ፖሊሲን በተግባር አለማዋሉ ከፍተኛ ክፍተት ነው፡፡
በመንግስት በኩል እስካሁን ያለው ህንፃን የሚያበረታታ ፖሊሲ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ባለሀብቱ መሬት ከመንግስት ወስዶ፣ ምርት ላምርት ቢል ብዙ ማነቆ ነው ያለው፡፡ ብዙም የስራ እድል የማይፈጥር፣ ህንፃ ልገንባ ቢል ግን ሁሉም ክፍት ነው። የፋይናንሻል መሰረተ ልማቱንም ሆነ የፊዚካል መሰረተ ልማቱን ብናየው፣ ያን ያህል ግብርናውን የሚያበረታታ አይደለም። አንድ ባለሀብት ገንዘብ ለግብርና ቢበደር መሰረተ ልማት ሳይሟላለት ቀርቶ ስራው ይጓተትበትና ወዲያው ምንም ሳይሰራ፣ ”እዳህን ክፈል” የሚል ሱሪ ባንገት ትዕዛዝ ይወርድበታል፡፡ መንግስት አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በተገቢው መንገድና ፍጥነት አለማስፋፋቱ ለዚህ ተግዳሮት አስተዋፅኦ አድርጓል። የትራንስፖርት፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ሳይሰሩ፣ ባለሀብቱን “ጫካ መንጥረህ አልማ” ብለን ብድር ብንሰጠው፣ የበለጠ ችግር ውስጥ እንዲገባ ነው የምንጋብዘው፡፡
ባንኮቻችን አቅማቸው ለህንፃ ገንቢዎች ማበደር ድረስ ብቻ የመሆኑ ሀቅ ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ ዋናው ችግር ፖሊሲ ነው ካልን፣ ፖሊሲውንም መፈተሽ ያስፈልጋል። ባለሀብቱ ከህንፃ ግንባታ ወጥቶ ሀገሪቱ ወዳላት ሰፊ ሀብት እንዲገባ አበረታች ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡
ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመግባት ምን ያህል ርቀት ተጉዘናል ማለት ይቻላል?
ኢንዱስትሪው ለምን አላደገም ብንል? ግብአት ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ግብአቱ ግብርና ነው፡፡ ድርቅ መጥቶ ግብርናውን ድባቅ የሚመታው ከሆነ እንዴት ይሰራል፡፡ ሌላው የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ይሄም ግብአቱ ግብርና ነው። ድርቅ መጥቶ ከብቶችን የሚጎዳ ከሆነ፣ጥራት ያለው ቆዳ እንዴት ማግኘት ይቻላል? ጥራት ያለው ቆዳ አይገኝም። ጥራት ያለው ቆዳ ለማግኘት በምግብ ያልተጎዱ ከብቶች ያስፈልጉናል፡፡ በምግብ ራሳችንን ካልቻልን የሆቴል ኢንዱስትሪው እንዴት ይዘልቃል? እነዚህ ነገሮች ተያያዥና ተመጋጋቢ ናቸው፤ መሰረቱ ግብርና ነው ካልን ብቸኛ ሀብታችን መሬቱ ነው፡፡ መሬቱን በትክክለኛ ፖሊሲ በሚገባ መጠቀም አለብን፡፡ አሁን ላይ ትክክለኛ ፖሊሲ አስቀምጠን ሀገሪቱን ወደ መታደግ እንግባ ብንል እንኳ በትንሹ 15 ዓመት ይፈጅብናል፡፡
በአፋጣኝ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት መፍትሄው ምንድነው?
አንደኛ ፖሊሲ ሲቀረፅ ከፖለቲካ አንፃር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ተቋማት መሳተፍ አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው ሀሳቦችን መዝኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የመሬት ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡ ሁለተኛ በመንግስት ስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ፣ የዘመቻ ስራዎች ላይ ደህና ነው፡፡ አንድን ፕሮጀክት ለማስጀመርና ለመስራት ጎበዝ ነው፡፡
ሆኖም እንዲህ ያሉ ሀገርን የመታደጊያ ፖሊሲዎች ግን ጉብዝናን ሳይሆን የባህሪ ለውጥን ይፈልጋሉ፡፡ እኔ ብቻ ነኝ መፍትሄው ማለት አያዋጣም፡፡ ፖሊሲ የሀገር ጉዳይ ነው። ከሀሳቡ ከሚከተለው ርዕዮት ጋርም ባይስማማ፣ እያቅለሸለሸውም ቢሆን ሌሎች አማራጮችን መቀበል አለበት፡፡

----------------------

                   • የምግብ ክምችት ስትራቴጂያችን ግቡን መቷል፣ ለሱማሌ ላንድም እርዳታ መስጠት ተችሏል
                   • የመንግስት ሰራተኛው ከረባቱን አስሮ ሽክ ቢልም ቤተሰቡን መቀለብ አልቻለም
                   • ለሰብል ልማት አልተጠቀምንበትም እንጂ መስኖ ተስፋፍቷል
                           ዶ/ር ደምስ ጫንያለው (የግብርና ምጣኔ ሀብት ምሁር)

      ኢኮኖሚው በፍጥነት እያደገ ነው ቢባልም ድርቅ ዛሬም ለሀገሪቱ ስጋት የሆነው ለምንድነው?
በመጀመሪያ እንደ ባለሙያ ሳየው፣ ድርቅ ለሀገራችን አሁን ስጋት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በድርቅ ለመጨረሻ ጊዜ ተፈትና የነበረው እ.ኤ.አ 2002/03 አካባቢ ነው፡፡ ያን ጊዜ ነው በግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ከዜሮ በታች የተመዘገበው፡፡ በአጠቃላይም ከዜሮ በታች እድገት ነበር የተመዘገበው፡፡ ከዚያ በኋላ በሚገባ የተሰራ ይመስለኛል፡፡ በመረጃም የተደገፈ ነው፡፡ ማንም ሰው መረጃ ቢሰበስብና ቢተነትን፣ የሀገሪቱ ግብርና በየዓመቱ በአማካይ ከ6 በመቶ በታች አልወረደም፡፡ አምና በኤሊኖ ምክንያት የወረደ ቢሆንም እሱም 3 በመቶ የተመዘገበበት ነበር፡፡ እነዚህን ስናይ አሁን ድርቅ ስጋት አይሆንም፡፡ ድርቅ የትም ሀገር አለ፡፡ ዋናው ለሚፈጠረው ችግር ዝግጁ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚያሳስበው ሰዎች በረሀብ እንዳይሞቱ ማድረግ ነው፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም፡፡ ይሄ የሆነው ግብርናው ቢወርድም እንኳ የመግዛት አቅም ተፈጥሮ እህል ተገዝቷል፡፡ ይሄ ስጋትን  መከላከል መቻል ነው፡፡
ዘንድሮ እንኳ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል፤ መንግስት ከዚህ ውስጥ 75 ሚሊዮን ብር ነው መመደብ የቻለው፡፡ የእርዳታ ጥሪም እያቀረበ ነው፡፡ ይሄ እርስዎ ከሚሉት ጋር አይጋጭም?
አይጋጭም! የመንግስት አካላት የራሳቸው አተያይና መንገድ አላቸው፡፡ ተቸግሬያለሁ ካላሉ ማንም አይሰጣቸውም፡፡ አለኝ ካሉ የሚሰጣቸው አያገኙም። ለምሳሌ እኔ ኬንያ በነበርኩበት ጊዜ የኢትዮጵያ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች ጥሩ ውጤት አመጡ፡፡ ያንን ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን ያወቁት ያግዟቸው የነበሩ የውጭ አካላት፤” በቃ ጥሩ ውጤት ካመጣችሁ እገዛ አያስፈልጋችሁም” ነው ያሉት፡፡ ይሄም እንዲሁ ነው፡፡ የእርዳታ ጥያቄ የተለመደ ነገር ነው፡፡ አምና የተፈጠረውን ችግር ግን ሀገሪቷ ራሷ ነበረች የተቋቋመችው፡፡ ችግሩ የተፈጠረ ሰሞን የውጭ መገናኛ ብዙኃን ደውለው፣ ይሄ ነገር እንዴት ነው ብለው ጠይቀውኝ ነበር፡፡ እኔም ትንሽ ሰግቼ ነበር፡፡ ግን ለኛ በሙያው ላይ ላለንና ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹን ለምንከታተል ሰዎች፣ አሁን ሁኔታውን በሚገባ የምንገመግምበት ጊዜ ነው ብለን ነበር፡፡ የሚታየው ውጤትም የአንድ ዓመት ሳይሆን የበርካታ አመታት ውጤት ነበር፡፡ እኛ እንጠብቅ የነበረውም ከዚህ አንፃር ሀገሪቱ ለዚህ ምን ምላሽ ትሰጣለች? የሚለውን ነበር፡፡ እኔ በኋላ ውጤቱን ስገመግመው፣ የምግብ ክምችት ስትራቴጂያችን ግቡን መቷል፣ የመግዛት አቅም ተፈጥሯል፣ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለሱማሌ ላንድም እርዳታ መስጠት ተችሏል፡፡ እኔ ኢትዮጵያ በቆሎ ወደ ውጪ ልትልክ ነው ቢባል አይደንቀኝም፡፡ አሁን አቅማችን እያደገ ነው፡፡ ጉዳዩን ፖለቲካዊ ሳናደርገው መመልከት አለብን፡፡ እውነታው የሚያሳየን በሁሉም ነገር ለውጥ አለ፡፡ ግን በዚያው መጠን ያልተሻገርናቸው ችግሮች የትየለሌ ናቸው፡፡ ከድህነት ቅነሳ አንፃር ብዙ ይቀረናል። አሁንም ከ25 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከድህነት በታች ናቸው፡፡ አሁንም ረሃብን አላጠፋነውም፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ ግን በግልፅ የሚታይ ለውጥ አለ፡፡
በምግብ ራሳችንን ችለናል ብለው ያምናሉ?
አንድ ሀገር በቀን 2100 ኪሎ ካሎሪ ምግብ በነፍስ ወከፍ ማቅረብ ከቻለች ወይም 2.13 ኩንታል በነፍስ ወከፍ ማምረት ከቻለች፣የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣለች ማለት እንደሆነ የዓለም የእርሻ ድርጅት (FAO) አስቀምጧል፡፡ እኛም እንደ ዘርፉ ሙያተኛ፣ ይሄን መሰረት አድርገን ነው ውጤቱን የምንመዝነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገራችን ሁኔታ ከ15 አመት በፊት 1.5 ኩንታል በነፍስ ወከፍ ነበር፡፡ አሁን 3.2 ኩንታል ደርሷል፡፡ በዚህ መመዘኛ ነው መንግስት የምግብ ዋስትናችንን አረጋግጠናል ያለው፤ በዚህ ስሌት እርግጥ ነው አረጋግጠናል፡፡ ይሄ ማለት ግን እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናችንን ብናረጋግጥም፣ በቤተሰብ ደረጃ አረጋግጠናል ማለት አይደለም። የቤተሰብ የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠም፡፡ ገበሬው ለሀገሪቱ የሚበቃውን ያህል አምርቷል ግን ብዙዎች ገዝተው መብላት አይችሉም። ይሄ ነው ያለው ችግር፡፡ ገበሬው የሚያመርተው ሸጦ ኑሮውን ለማሻሻል እንጂ ከተሜው ተርቧል ምርቴን አምጥቼ ልበትን ብሎ አይደለም፡፡ ሊልም አይችልም። ገበሬው ያዋጣኛል ባለው ዋጋ ይሸጠዋል፡፡ ሸማቹም መግዛት ያለበት በዚህ አግባብ ነው፡፡ ለዚህ ነው መንግስት የከተማ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ለመዘርጋት ያቀደው፡፡ አሁን ትልቁ ፍጥጫ ያለው የነፍስ ወከፍ ገቢ ላይ ነው፡፡ አንድ ሰው ገቢው ለሚያስፈልገው ነገር በቂው ነው ወይ የሚለው ነው ትልቁ ችግር፡፡ ዋናው ችግር ያለበት ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው ነው፤ ከረባቱን አስሮ ሽክ ቢልም ቤተሰቡን መቀለብ እየቻለ አይደለም፡፡ በግል ተቋማት ያለው ደህና ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ይሄ የራሱ መፍትሄ የሚያስፈልገው ውስብስብ ጉዳይ ነው፡፡
ኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፉ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት አለማደጉ ወደ ኋላ ጎትቶናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ዋናው መጀመሪያ ፖሊሲው ሲወጣ፣ የግብርና መሬትን፣ ሰፊ የሰው ኃይልን ተጠቅመን በተቻለ መጠን ከውጭ ቴክኖሎጂ እስከምናስገባ የራሳችንን ተጠቅመን እናለማለን የሚል ነው፡፡ መሰረታዊው የኢትዮጵያ የግብርና ፖሊሲ መርህ ማለቴ ነው፡፡ አሁን በፍጥነት አልተጓዝንም ላልከኝ ችግሩ እነዚህን ነገሮች ባለማቀናጀታችን ነው፡፡ እንደኔ ግብርናውንም በቅጡ አልሰራነውም ባይ ነኝ፤ ፈጥነን ግብርናውን መስራት አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ተቀናጅቶ በመስራት በኩል እውነቱን ለመናገር በተደጋጋሚ ወድቀናል፤ አልተወጣነውም። የኛ ሀገር የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ በምግብ ማቀነባበርና በግብርና ውጤት አምራችነት ላይ ነው የሚያተኩረው። ጨርቃጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የስጋና የወተት ውጤቶች፣ የስኳር የመሳሰሉት ላይ ነው ኢንዱስትሪው የሚያተኩረው።
ለእነዚህ ሁሉ ደግሞ ዋነኛ ጥሬ እቃ ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ግብርናው ነው፤ ግን በዚህ በኩል ምን ያህል ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ እውነት ግን እዚህች ሀገር ላይ ይሄ መሆን ነበረበት? ይሄ ለእኔም ጥያቄ ነው። የሆነ የሳትነው ነገር አለ፡፡ ጥጥን የሚያመርተው ተቋም፣ እንዴት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ግብአት ማቅረብ አልቻለም? ቅንጅት ስለሌለ ነው፡፡ ይህ ቅንጅት ባለመኖሩ ዛሬ ጥጥን በጥሬ እቃነት ኤክስፖርት ለማድረግ ተገደናል። በቆዳ ውጤቶችም የሚታየው ይሄው ነው። ኢትዮጵያ በከብት ሀብት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 10ኛ የሚለውን እኔ ከ40 አመት በፊት ጀምሮ የማውቀውና እስካሁንም ልጆቻችን የሚማሩት ነው፡፡ ታዲያ እንዴት በቆዳ ኢንዱስትሪ ነጥረን መውጣት አቃተን? አቃቂ ላይ ግሩም የቆዳ ኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ተዘርግቶ ነበር፡፡ ዛሬ የት ገባ? ቆዳና ሌጦ ዛሬ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? አንዳች ችግር አለ ማለት ነው። ይሄን መፈተሽ አለብን፡፡ ቅንጅት የለውም ያልኩት ለዚህ ነው፡፡
ሀገራችን ለስንዴ ምርት ተስማሚ ተብላ በዓለም የምትታወቅ ነች፤ ስንዴ ለዱቄት ፋብሪካዎች ከውጭ ስታስገባ ያስገርማል፡፡ ምንድነው ችግሩ? እስከ 600 ሺህ ቶን ስንዴ ያስገባንበት ጊዜ አለ። ይሄ ከቅንጅትና ሀብትን በአግባቡ ካለመጠቀም የሚመጣ ችግር መኖሩን የሚያሳይ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፡፡ ይሄን መስመር ለማስያዝ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡
ለምን በምግብ ራሳችንን አልቻልንም ላልከው፣ መስኖ ማስፋፋትና ከዝናብ ጥገኝነት መውጣት አለብን በሚለው መንግስት ይስማማል፡፡ ይሄ እንዲተገበርም አቅጣጫ አስቀምጦ ሲሰራ እያየነው ነው፡፡ ገበሬዎቻችን በመስኖ አመረቱ፤ ገበያ ግን የላቸውም፡፡ ስለዚህ ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን ማምረት ትተው፣ አነቃቂ እፆችን ወደ ማምረት ነው የገቡት፡፡ ግን በመስኖ መስፋፋት ጥሩ ውጤት አስመዝግበናል፡፡ እንዳልኩት ለሰብል ልማት አልተጠቀምንበትም እንጂ፡፡ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ወደ 3 መቶ ሺህ ሄክታር ብቻ የነበረው የመስኖ ልማት ወደ 2.8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደርሷል፡፡ በ GTP 2 ደግሞ ወደ 4 ሚሊዮን ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ ግን ይሄ ቢደረግም በየደረጃው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር የተቀናጀ ባለመሆኑ ውጤቱ ጎልቶ ሊመዘገብ አልቻለም። ምርቱ፣ ቴክኖሎጂው፣ ስርጭቱ መቀናጀት አለባቸው። እነዚህን በሚገባ ካልመራናቸው መቼውንም ቢሆንም ከችግር መውጣት አንችልም፡፡ የትልልቅ ፕሮጀክቶች ውጤት የሚታየው በ2 ዓመት ውስጥ አይደለም፤ ጊዜ ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው፤ ግን ግብርናው ካልዘመነና በሚገባ ካልተሰራበት ጥሬ እቃ ግብአት ከየት ሊመጣ ነው። እኔ ግብርናው ላይ መጀመሪያ በቅጡ መስራት አለብን እላለሁ፡፡ ግብርናው ገንዘብ ካላመጣ ኢንዱስትሪው እንዴትም ሊያድግ አይችልም። በፍጥነት እያደገ ለመጣው የአገልግሎት ዘርፍ 90 በመቶ ግብአት የሚገኘው ከግብርናው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ለኢንዱስትሪና ለማኑፋክቸሪንግ የገንዘብ አቅርቦቱ ሊመጣ የሚችለው ከግብርናው ነው፡፡ ትልቁ ችግራችን ግብርናውን አለማዘመናችን ነው፡፡
አሁን ያለው የነጠፈችን ላም ዝም ብሎ ማለብ ነው፡፡ የወደቅነው ካለው የግብርና ስትራጂ ሳይሆን ከአተገባበሩ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁንም ቢሆን ለዚህች ሀገር ትልቁ የገንዘብ ምንጭ ግብርና ነው፡፡ የወጪ ንግዱን የተቆጣጠረው ግብርና ነው፡፡
አሁን ባለው የመሬት ሥሪት፣በባህላዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ ባልታከለበት እርሻ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ይቻላል?
በአሁኑ ሰአት በዓመት 13 ሚሊዮን ሄክታር ነው በሰብል ተሸፍኖ ያለው፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰፋፊ እርሻዎች የሚባሉት ከ10 ሄክታር በላይ ለግብርና ውሎ፣ ውጤት እየሰጠ ያለው 2 በመቶ አይሞላም፡፡ ስለዚህ ሰፋፊ እርሻዎችን አግዝፈን ማየት የለብንም። በእርግጥ ኢትዮጵያ እንዴት ነው ወደ ዘላቂ ሰፋፊ እርሻዎች መሄድ የምትችለው የሚለው መታሰብ አለበት፡፡ መጀመሪያ የተቀረፀው ስትራቴጂ ጥቃቅን የእርሻ ልማቶች ላይ ስለማተኮር ነበር፤ በኋላ ደግሞ ትናንሽና ትላልቅ የእርሻ ልማቶች ላይ ነው ማተኮር ያለብን የሚል መጣ፡፡ ትላልቅ የተባሉት ቢጀምሩም ውጤታቸው እምብዛም ነው። አሁንም 75 በመቶ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚቀልቡት ትናንሽ መሬት ላይ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ናቸው፤ ስለዚህ የመሬት ስሪቱ የግድ ትላልቅ መሆን የለበትም። ዋናው ትናንሽ ገበሬዎችን ለገበያ የሚሆን ምርት እንዲያመርቱ እያደረግን ነው ወይ? የሚለው ነው። ይሄ ነው መታሰብ ያለበት፡፡ እነዚህን አርሶ አደሮች ምን ያህል አዘምነናቸዋል ነው ቁምነገሩ፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ይቀረናል፡፡ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደሮች እንዲያድጉ እድሉ ሊከፈትላቸው ይገባል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው አሁን ካሉበት ወደ 10 ሄክታር፣ ከዚያም ወደ 20 እያደጉ የሚሄዱበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡

Read 1879 times