Print this page
Monday, 06 March 2017 00:00

የፓርቲዎቹ ውይይትና ድርድር ተስፋ የለውም!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

 • ነገር የተበላሸው፤...መንግስት፣ “ዘበኛ” እንዲሆንልን ሳይሆን፣ “ጌታ” እንዲሆንብን የተስማማን ጊዜ ነው።
 • የአገራችን ፖለቲካ - “ለመጣላት መስማማት”!
  • ስልጣን የያዘ፣ የአገሬው ጌታ ይሆናል። እዚህ ላይ ውይይትና ክርክር የለም። ብዙዎቻችን የተስማማንበት ጉዳይ ነው (“አገራዊ    መግባባት” ልንለው እንችላለን)።
   • የፖለቲከኞች ውይይትና ድርድር፣ ውዝግብና ግጭት ደግሞ፣... “ማን መንግስት ይሁን? እንዴት ስልጣን ይያዝ?” የሚሉ  ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ነው።
                     
     የፓርቲዎቹ ውይይትም ሆነ ድርድር፣... ፈፅሞ አንዳችም ጥቅም የለውም እያልኩ አይደለም። ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን፣ ትንሽ ለመረጋጋትና ለመስከን፣ “መነጋገርና መወያየት... እንደ ምፅአት አስፈሪ እንዳልሆነ” በእውን ለማየት ይጠቅማል። ነገር ግን፣ በአገሪቱ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚም ሆነ ባህል ላይ፣ መልካም የመሻሻል ለውጥ ይፈጥራል ወይም መልካም ጅምር ይሆናል ብሎ ማሰብ፣ የዋህነት ነው። ለምን?
ያው፣ አዳሜና ሔዋኔ... ዋናውን የችግር መንስኤ፣... ጨርሰው ዘንግተውታል። እንዲያውም፣ “ዘንግተውታል” ከማለት ይልቅ፣... ዋናውን የችግር መንስኤ፣ እንደ ዋና እምነት፣ የሙጢኝ ይዘውታል - ብዙዎቹ። በቃ! “መንግስት መሆን ማለት፤ ጌታ መሆን ማለት ነው” ብለው ያምናሉ። በእርግጥ፣ ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት ሊለያይ ይችላል።
መንግስት ጌታ የሚሆነው፣ “የብዙሃኑን ሕዝብ የበላይነት ለማረጋገጥ”፣ “የድሆችንና የሚስኪኖችን ጥቅም ለማስከበር”፣ “የአገርን ወይም የብሄር ብሄረሰብን ክብር ለመጠበቅ”፣ “ልማትን ለመምራት”፣... ወዘተ በምርጫ ስለበለጠ፣ በአመፅ ስላሸነፈ፣ በፈጣሪ ስለተሰየመ፣ በትውልድ ሐረግ ንግስናን ስለወረሰ... እያሉ ብዙ አይነት ማመካኛ ይደረድራሉ። ማመካኛዎቹ ቢለያዩም፣ ማከኛዎቹ አዳሜን ለብዙ አመታት በጠላትነት ቢያወዛግቡም፣ በመሰረታዊው ጉዳይ ላይ ግን፣ ለአመታት ብቻ ሳይሆን፣ ለበርካታ መቶ አመታት፣ በድርቅና የዘለቀ ስምምነት በጉልህ ይታያል። ማመካኛው ምንም ሆነ ምን፤ “መንግስት፣ የአገሬው ጌታ ነው” የሚለው እምነት፣ የአብዛኛው ሰው፣ የአብዛኛው ፖለቲከኛ እምነት ነው።
ይህንን አሳዛኝ ኋላቀርነትና ስምምነት፣ በየእለቱ ማየትና በቀላሉ ማረጋገጥ ትችላላችሁ። ከእውነት ጋር የሚያጣላ፣ የፕሮፖጋንዳ ሱስን ተመልከቱ። ብዙ ሰው፣ ፕሮፓጋንዳን የሚጠላ ይመስላችኋል?... ኧረ በጭራሽ!
በእርግጥ፣ መንግስት፣ ፕሮፓጋንዳን ሲያወግዝ ትሰማላችሁ። “በኢንተርኔት የሚሰራጩ የውሸት መረጃዎች፣ በየአገሩ የጥፋት ቀውስን እየፈጠሩ ነው” በማለት ተቃዋሚዎችንና ተቺዎችን ይኮንናል - መንግስት። ብዙ ተቃዋሚዎችም በፊናቸው፣ የመንግስትን የእለት ተእለት የሚዲያ ፕሮፓጋንዳን ያማርራሉ። ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ደጋፊ በመሆን፣ ፕሮፓጋንዳን (ውሸት ላይ የተመሰረተ ጭፍን ቅስቀሳን) ያወግዛሉ። ግን፣ የፓርቲ ፕሮፓጋንዳን አይጠሉም። የሚያስጠላቸው፣ ፕሮፓጋንዳው፣ ከተቀናቃኝ ፓርቲ ሲመጣ ብቻ ነው። የመንግስትን ፕሮፓጋንዳን አይጠሉም። የሚያስጠላቸው፤ ፕሮፓጋንዳው፣ በማይደግፉት መንግስት አማካኝነት የሚዘወር ሲሆን ነው።
በአጭሩ፣ አዳሜና ሔዋኔ፣... አብዛኞቹ የአገሬ ሰዎች፣... በአንድ ነገር ይስማማሉ። መስማት የማይፈልጉትን መረጃና ሃሳብ፣ የሚያጠፋላቸውና የሚከለክልላቸው ሃይለኛ ጌታ፣ ሃይለኛ መንግስት እንዲኖር ይመኛሉ። “ጌታ መንግስት” ሊኖረን ይገባል ብለው ያምናሉ። በዚህ ተግባብተው፣ “የመንግስት ስራ፣ ጌትነት ነው” ብለው በሙሉ ልብ ከተስማሙ በኋላ ነው፣ ወደ ፀብ የሚገቡት። “ማን መንግስት ይሁን?” በሚለው ጥያቄ ላይ ክፉኛ ይጣላሉ። መጣላታቸው አይገርምም። “መንግስትነት” ማለት፣ “ጌትነት” ማለት ነው ብለው ከተስማሙ በኋላ፣ ጌታ ለመሆን መራኮታቸውና መጣላታቸው አይቀሬ ነው።
መንግስት፣ ‘ጌታ’ እንዲሆንባቸው የተስማሙ ጊዜ ነው፣... ነገር የተበላሸው። ግን፣ ለአፍታ ቆም ብለው፣ ሃሳባቸውን እንደገና ለመመርመር አይሞክሩም። በዚያው ይቀጥላሉ። በቃ... ገናና መንግስት ይናፍቃቸዋል። የሚቀኑበትን የስራ ስኬት የሚያፈርስላቸው፣... በሰዎች ንብረትና ሕይወት ላይ እንዳሻው ማዘዝ የሚችል “ጌታ መንግስት” እንዲኖር ነው የሚፈልጉት። ባሻው ጊዜ ድጎማ የሚሰጥ፣ ያሰኘውን ያህል ታክስ የሚወስድ፣ ገንዘቡንም ወስዶ “ለህዝብ ጥቅምና ለአገር ልማት” በሚሉ ሰበቦች በየቦታው የመንግስት ቢዝነስን እየከፈተ... ‘እንደፈቀደው’ ሃብትን የሚያባክን፣ ገናና መንግስትን ነው የሚመኙት።
“እያንዳንዱ ሰው፣ የሕዝብን ጥቅምና የአገርን ልማት ማስቀደም አለበት” በሚለው ኋላቀር የሃሳብ ስምምነት ላይ በመመስረት፤ ዜጎችን እንደ አገልጋይ ባሪያ የሚቆጥር፣ ጡንቻማ መንግስትን ነው የሚመርጡት። እያንዳንዱ ሰው የሕዝብ አገልጋይ፣ ወይም የአገር ባርያ ስለሆነ፣ ታዛዥ መሆን ይኖርበታል። እናም፣ “ይህንን ስራ፣ ያንን አትስራ” ብሎ እንደልቡ ማዘዝና መከልከል የሚችል መንግስት እንዲኖር ይጠብቃሉ። የእያንዳንዱ ሰው ንብረትና ሃብት፣ የግል ሳይሆን፣... “የአገር ሃብት”፣ “የጋራ የሕዝብ ንብረት” መሆን ይገባዋል ብለው ያምናሉ። ለዚህም ነው፣ “ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል” የሚለውን ጠማማ ፈሊጥ የሚያዘወትሩት።
እያንዳንዱ ሰው፣ በስራ ያመረተው ውጤትና በጥረቱ ያፈራው ንብረት ላይ፣ የባለቤትነት መብት ሊኖረው ይገባል ብለው አያምኑም። “የአገርና የጋራ ንብረት ነው” በሚል ሰበብ፣ የአምራቾችን ሃብት እየተወሰደ፣ ለሌሎች ሰዎች... (ለሕዝብ እንዲመፀወት) ይፈልጋሉ። ይህንን ነው፣ “ፍትሃዊ ክፍፍል” የሚሉት። ይህንኑን ዝርፊያ ተግባራዊ ለማድረግም፣ እንዳሰኘው የዋጋ ተመንን የሚያውጅና... የሚሽር፣... ኮታ እና ራሽን የሚመድብ፣... አድራጊ ፈጣሪ “ጌታ መንግስት” መኖር አለበት።
በአጭሩ፣ ለእውነትና ለነፃነት ያን ያህልም ደንታ ሳይኖረው፣ የሰዎችን ሃሳብ የሚቆጣጠር፣ የሚያፍን፣ በፕሮፓጋንዳ የሚያደነዝዝ፣... ቁጡ እና ነዝናዛ መንግስት እንዲኖር ይፈልጋሉ።
ለጥረትና ለስኬት ደንታ የሌለው፣ ለንብረት ባለቤትነት መብት ቅንጣት ዋጋ የማይሰጥ፣... በሰዎች ንብረትና ኑሮ ላይ ማዘዝ የሚችል፣... የአገሬውን ሃብት... በሰፊው የሚቆጣጠር ገናና መንግስትን ይወዳሉ።
የአገራችን አዳሜና ሔዋኔ፣ በአብዛኛው በዚህ በዚህ ይስማማሉ - “ጌታ መንግስት ያስፈልጋል” በማለት። በዚህ ስለተስማሙም ይጣላሉ። “ማን መንግስት ይሁን?”፣ “ማን ጌታ ይሁን?”... መቋጫ የሌለው ፀብ፣ ውዝግብ፣ ሽኩቻ፣ ግጭት ወስጥ ይገባሉ።
ታዲያ፣ የስልጣን ጉዳይ፣ በጣም፣... እጅግ በጣም፣ “አንገብጋቢ” ቢሆንባቸው ይገርማል? አንገብጋቢ እንዲሆን አድርገውታላ። መንግስት መሆን ማለት፣ “አድራጊ ፈጣሪ ጌታ” የመሆን ጉዳይ ነው። በሰዎች ሃሳብ፣ ንብረትና ኑሮ ላይ እንዳሰኘው ማዘዝ ይችላል - እለት ተእለት በዜጎች ኑሮ ላይ የተሰነቀረ ስለት ነው - እለት ተእለት እያቆሰለ ማንገብገብ... የመንግስት መደበኛ ስራ፣ መደበኛ ስልጣን ይሆናል። ለዜጎች በጣም አንገብጋቢ ሆነባቸው ማለት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይህን “የጌትነት” ስልጣን ለመያዝ፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ጉልበተኞች፣... አጋጣሚው የተመቸው ሰው ሁሉ፣... ይፍጨረጨራል፣ ይንገበገባል - የያዘውን ስልጣን ላለመልቀቅ ወይም በተራው ስልጣን ለመያዝ።
የመንግስት ስራ፣ “ዘበኝነት” ቢሆን ኖሮ፣ ለ“ስልጣን” መንገበገብ... እንዲሁም በስልጣን ሳቢያ መንገበገብ ይቀንስ ነበር።
ለዚህም ነው፣ የፓርቲዎች ውይይትም ሆነ ድርድር፣ “የመንግስት ስራ ምን መሆን አለበት?” በሚለው ጥያቄ ላይ ማተኮር ነበረበት የምለው። የመንግስት ስራ፣ “ዘበኝነት” ከሆነ፣ የትኛውም ፓርቲ፣... የትኛውም ፖለቲከኛ ስልጣን ላይ ቢወጣ፣ ብዙም ጥፋት የመፈፀም እድል አይኖረውም። በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ እንዳሻው ማዘዝ የማይችል “የጥበቃ ሰራተኛ”፣ ያን ያህልም ጉዳት ሊያደርስ አይችልም። “ዘበኝነትን የሙጢኝ እይዛለሁ” ብሎ ማስቸገርም አይኖርም።
ነገር ግን፣ የፓርቲዎቹ ውይይትና ክርክር፣ በአብዛኛው “ማን መንግስት ይሁን?” በሚል የስልጣን ጥያቄ ላይ ያተኮረ ነው።
መንግስት፣ “ዘበኛ” ሳይሆን፣ “የአገር ጌታ ነው” የሚለው ኋላቀር የምዕተዓመታት እምነት፣ አሁንም ይቀጥላል ማለት ነው። መንግስት፣ “አድራጊ ፈጣሪ ጌታ” መሆኑ የማይቀር ከሆነ ደግሞ፣... የትኛውም ፓርቲ፣ የትኛውም ፖለቲከኛ ስልጣን ቢይዝ፣ ያን ያህል የመሻሻል እድል አይኖርም። የሚያዛልቅ ለውጥ አይመጣም። በሌላ አነጋገር፣ ገና ተስፋ የለውም።
እስቲ፣ ከሌላ ሰው ፅሁፍ ትንሽ ላስነብባችሁ። “መንግስትነት” ማለት፣ “ጌትነት” ማለት የሆነበት ኋላቀር አገር ላይ፣ መልካም የነፃነትና የስልጣኔ ለውጥ ሊፈጠር ይችላል? የሊበራሊዝም ፖለቲካ ሊከሰት ይችላል? በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ፣ በ2000 ዓ.ም ምን አይነት ትንታኔና ምላሽ ሰጥተው እንደነበር በማስታወስ፣ በድጋሚ በፅሁፍ አስነብበውናል - “ከአረብ አገራት አብዮት” ማግስት። እንዲህ ይላሉ።... ኋላቀር አገር ውስጥ፣...
“የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ማለት፣ በቀጥታ የአገሪቱን ሃብት በሙሉ መቆጣጠር ማለት ስለሆነ፣ በሊበራል ዴሞክራሲ ስሌት ስልጣን በምርጫ ሊታደል እንደማይቻል ተተንትኖ ነበር። ስልጣን ይዞ፣ ሃብቱን የተቆጣጠረ ሃይል፣ ምንም ቢሆን ይህንን ሃብት፣ በፍላጎት ለሌላ ሃይል ሊያስረክብ እንደማይፈቅድና እንደማይቻል፣... (የፈቃደኝነት ጉድለት ብቻም አይደለም ማለታቸው ነው። አይቻልም እያሉ ነው። ስልጣንን በሰላም ማስረከብና መረከብ... አይቻልም። ግን... ነባሩ መንግስት፣ ቢወድቅስ?)... በሆነ ምክንያት ከስልጣን ቢፈናቀል፣ ስልጣን የያዘው አዲስ ሃይልም እንደገና... ሃብት... ይዞ በስልጣን ለዘለዓለም ለመሰንበት ከመረባረብ ወደኋላ እንደማይል ተመልክቶም ነበር። የፖለቲካ ስልጣንና ሃብት፣ አንድና ያው በሆኑበት አገር፣ ስልጣን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊያዝ የሚችልበት ነባራዊ መሰረት እንደሌለ መፅሄቱ ያትታል።”
ይሄ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። በእነ ግብፅና ቱኒዚያ፣ አመፅ በተቀጣጠለበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ በኢህአዴግ መፅሔት ላይ፣ በ2000 ዓ.ም የፃፉትን ትንታኔ በማስታወስ፣ እንደገና ያቀረቡት ፅሁፍ ነው።
በእርግጥም፣ መንግስት ማለት፣ የአገሬውን ሃብት የመቆጣጠር ስልጣን፣ (ማለትም፣ በዜጎች ንብረትና ኑሮ ላይ እንዳሻው የማዘዝ “ጌትነት”) እንዲሆን የተስማማን ጊዜ፣... ያኔ፣ በቃ... ነገር ተበላሽቷል። አንደኛ ነገር፣ የግለሰብ ነፃነትንና መብትን ወደ ጎን በመጣል ላይ የተመሰረተ ስምምነት ነው። ሁለተኛ ነገር፣ “ጌትነት” የሞት ሽረት ጉዳይ ይሆናል። ሦስተኛ ነገር፤ አንዱ ከስልጣን ወርዶ፣ በቦታው ሌላ “ጌታ” ቢጫንብን፣ ለውጥ የለውም።

Read 2443 times