Monday, 06 March 2017 00:00

ደስ አይበላችሁ ባለምጣዶች፤ ልንጋግረው ያሰብነውን አገነፋነው

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 አንዳንድ ተረት ሲደገም የበለጠ ይገባል፡፡ ምናልባት ልቡናችን ሁሌም እኩል ክፍት ስለማይሆን ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም የበለጠ ወቅታዊ ሁኔታ አግኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ አጣዳፊ ጉዳይ አዕምሮአችን ሲወጠር ጠንከርና በሰል ያለውን ጉዳይ ምን ተደጋግሞ ቢነገረን የማንሰማበት ጊዜ አለ፡፡ ውሎ አድሮ ሁኔታው ሲሻሻል ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ከአስራ አንድ ዓመት በፊት የተረትነውን ዛሬ የምንደግመው ለዚህ ነው፡፡
አንድ የሩቅ ምስራቅ ፌዘኛና ብልህ አዛውንት ነበሩ አሉ፡፡ በጣም ከሚታወቁበት ነገር አንዱ ግማሽ ህይወታቸውን ከሀገራቸው ውጪ ሲሰደዱና በምህረት ሲመለሱ የኖሩ መሆናቸው ነው፡፡
ታዲያ አንደኛው አገር አለቃ ገብረ ሀና ብዙ የሚነገሩላቸው ወጎች አሉ፡፡
አንድ ጊዜ የአገሩ ንጉሥ እኒህን አዛውንት አግንተዋቸው ሁለቱ እንደሚከተለው ያወጋሉ፡፡
ንጉሥ - እንደምን ሰነበቱ አባቴ?
አዛውንቱ - እንደ አገሬው
ንጉሥ - ከየት ነው የሚመጡት?
አዛውንት - ከፀሐይ መውጫ
ንጉሥ - ወደየት ይሄዳሉ?
አዛውንት - ወደ ፀሐይ መውጫ
ንጉሥ - እንዴት? ከፀሐይ መውጫ እየመጡ፣ ወደ ፀሐይ መውጫ ሊሄዱ ይችላሉ? ብለው በመገረም ይጠይቃሉ፡፡
አዛውንቱም - እሱ በሦስት መንገድ ይወሰናል
ንጉሥ - በምን በምን?
አዛውንት - አንደኛ በማንነትዎ ነው፡፡ ማለትም ፀሐይ ልትጠልቅብኝ ነው ብለው የሚያስቡ ከሆነ ወደ ፀሐይ መውጫ እንደሚሄዱ ያምናሉ፡፡ ሁለተኛ/በአነሳስዎ ማለትም መንገድ የጀመሩት በጨለማ ከሆነ መድረሻዎ ሲነጋጋ ስለሚሆን ወደ ፀሐይ መውጫ ሄዱ ማለት ነው፡፡ መንጋቱ አይቀርምና፡፡ ሦስተኛው/ወሳኝ ነገር የአቅጣጫና የእንቅስቃሴ ግንዛቤዎ ነው፡፡ እንዴት ቢባል ዘወር ብለው ፀሐይን ቢመለከቷት እየተከተለችኝ ነው? እያሳደደችኝ ነው? ብለው መጠየቅዎ አይቀርም፡፡” አሉና አስረዷቸው፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚሁ እኒያ አዛውንት ንጉሡ ፊት ይቀርባሉ፡፡
ንጉሡ፡- ምነው ጢምዎ እንደዚህ ረዘመ - ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡
አዛውንቱም - የአገር ነገር ከብዶት - ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
ቀጥሎም ንጉሡ፡- እስከ ዛሬ ካጋጠሙዎት መሪዎች የትኛውን ያደንቃሉ?- ብለው ይጠይቋቸዋል፡፡
አዛውንቱም - ዐይኔን ሳልታወር በፊት ሊመራኝ የቻለውን ነው - ብለው ይመልሳሉ፡፡
ቆይተው ከስደት ሲመለሱ ንጉሡ ያስጠሯቸውና፤
የውጪ አገር ኑሮዎንና የ፣.አገር ውስጥ ኑሮዎትን ሲያወዳድሩት የቱን ወደዱት - ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡
አዛውንቱ - እሱማ እንደቆምኩበት ቦታ ይለያያል፡፡ እዚህ ስሆን ያንን እወደዋለሁ፡፡ እዚያ ስቆም ደግሞ ይሄንን እወድደዋለሁ፡፡
ከርመው ከርመው፣ ደግሞ ከስደት ሲመለሱ፤
ንጉሡ፡- ከስደት ምን ይዘህ ወደ አገርህ ተመለስህ? - ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡
አዛውንቱም - ንጉሥ ሆይ፤ ዱሮ ይዤ የወጣሁትን ችግር ይዤ ነው የተመለስኩት፡፡ ማንም የነካብኝ የለም፡፡ …አሉ ይባላል፡፡
*          *        *
  የስደት ቦቃ የለውም፡፡ በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካ፣ ወይም በማናቸውም ማህበራዊ ችግር፤ ምንም ዓይነት ስም ብንሰጠው፣ አንዴ ከሀገር ከወጣን ስደተኞች ነን፡፡ ስለዚህም የስደትን ገፈት መቅመሳችን አይቀሬ ነው፡፡
“ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ
ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ”
       *    *     *
“ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ”
        *   *  *  
“እረ ሰው እረ ሰው
ዐይኔን ሰው ራበው”
እኒህንና ሌሎችም በቅኔ ባኮ ውስጥ ያሉ ግጥሞች፣ የዚያው የስደት አባዜ አስረጆች ናቸው፡፡ ሁሉም ውስጣቸው የስደት ምሬት ቃና አላቸው፡፡ እነዚህ ላይ ዶናልድ ትራምፕ ሲጨመርባቸው፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል፡፡ ከላይ በተረቱ ውስጥ እንዳየነው፤ “ዱሮ ይዤ የወጣሁትን ችግር ይዤ ነው የተመለስኩት” እንደተባለው ነው፡፡ ስደት የማንነት ጠላት ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን ያስረሳል፡፡ የራሱ አጉይ - መነፅር አለውና አመለካከትን ያንጋድዳል፡፡ ጥንቃቄ ካልተደረገበት፣ ጠባይንም ያስለውጣል፡፡ “ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት” መግባት አሌ አይሉት ሀቅ ነውና፣ ለዘመድ አዝማድ፣ ለወዳጅና ለሀገር ቁም ነገር ልሥራ ማለት ብልህነት ነው፡፡ ከራስ አልፎ ለወገን ማሰብ፣ ለወገን መትረፍ፣ ልብና ልቦና ላለው ሁሉ ታላቅ ተግባር ነው፡፡ በጎ አድራጎትን ማሰብ አያሌ ህፃናትን ለመታደግ በር ከፋች ነው፡፡ ለአያሌ እናቶች መድህን ነው፡፡ የርሀብን ስፋት፣ የድርቅን ብዛት ነግ - ሠርክ ብናወራው ሰቆቃው ውስጥ ላለው ህዝብ ዳቦ አይሆነውም፡፡ ድህነት ሲያወሩት ቢውሉ፣ ያው ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ እንደ ዋና ገብተው ካላዩት አይማሩትም፡፡ ውስጡ ሙስና እያለ፣ ውስጡ ፀረ-ዲሞክራሲነት እያለ፣ ውስጡ ኢ-ፍትሀዊነት እያጠጠ፣ ድህነትን ተረት እናደርጋለን ማለት የአፍ ወግ ብቻ ይሆናል፡፡ ፀሐፌ - ተውኔቱ፤ ድህነት በአፍ አይገባም ያለውን አለመዘንጋት ነው፡፡
ሀገራችን የጀግኖች ሀገር ለመሆኗ ዛሬ ብዙ ምስክር መቁጠር አያሻም፡፡ አድዋ ማግስት ላይ ቆሞ ይህን መጠየቅ የዋህነት ነው፡፡ ይልቁንም የትናንቱን ጀግንነት ለአሁኑ ትውልድ እንዴት እናስጨብጠው ነው ጥያቄው፡፡ ከዘመናዊነት ጋር የትናንቱን ጀግንነት እንዴት እናዋህደው ነው ጉዳዩ፡፡ ባህሉን ያልረሳና ከዓለም ጋርም እኩል የሚራመድ ጀግና ትውልድ እንዴት እንፍጠር ማለት ግዴታችን ነው፡፡ አጓጉል ትውልድ የአባቱን መቃብር ይንድ” እንዳይሆን ምን ዘዴ እንዘይድ እንበል፡፡ ከአንገት በላይ ሳይሆን ከአንጀቱ የሀገርን ጉዳይ የሚያይ ትውልድ እንዴት እናፍራ? ባህሉንና ግብረ ገብነቱን፣ ትምህርቱን አጥብቆና ጠንቅቆ፤ አውቆ እንዲጓዝ ምን ይደረግ? ካልኩ ካለፈው ራስ - ወዳድነት እንዴት እናላቀው? ያለፈ ታሪኩ ባለታላቅ ዝና፣ ነገው ግን ኦና (with glorious past but no future እንዲሉ ፈረንጆቹ) እንዳይሆን ምን እናድርግ? ወጣት የነብር ጣት በማለት ብቻ ወኔ አይጠመቅም፡፡ መራር ሀሞት ከመሬት አይበቅልም፡፡ በተግባራዊ ግንዛቤው፣ ንቃቱ፣ ብቃቱ እና ሽንጥን ገትሮ መንቀሳቀሱ፣ መኖሩን ቀርቦ መመርመር፣ ከሌለም ቀርቦ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ለሀገሩ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል! ስለወጣቱ እኩል እሳቤ ካልኖረንና፤ እኛ ራሳችንም የጋራ ቤት እንዳለን ሳናስተውል መቻቻል ጠፍቶብን ከተናቆርን፤ የምናወርሰውም ያንኑ በቂምና በሸር የተሞላ ሀገር ነው፡፡ ያንኑ አፈ - ቅቤ ልቤ - ጩቤ ሥርዓት ነው፡፡ አንዱ ሲያልፍለት ሌላው ለመመቅኘት እንቅልፍ የሚያጣበትን ህይወት ነው፡፡ ዕድሜ ልካችንን፤ “ደስ አይበላችሁ ባለ ምጣዶች፣ ልንጋግረው ያሰብነውን አገነፋነው” እየተባባልን አንዘልቀውም! ቆም ብለን እናስብ!

Read 5335 times