Monday, 06 March 2017 00:00

ገራገሩን ስለ ሮበርት ሙጋቤ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አዛውንቱ ፕሬዚዳንት
ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 21, 1924 ዓ.ም ነው የተወለዱት - በዚምባቡዌ ደቡባዊ ርሆዴዥያ ግዛት፡፡ ሮበርት ሙጋቤ አሁን 91 ዓመታቸው ሲሆን በመላው ዓለም ከሚገኙ መሪዎች ሁሉ በዕድሜ አዛውንቱ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
በእናት ያደጉት ሙጋቤ
ሰዎች አምባገነን ተፈጥሮአቸውን በመመልከት ብቻ ሙጋቤ በፈላጭ ቆራጭ አባት ነው ያደጉት ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ እውነቱ ግን ሌላ ነው። የሙጋቤ አባት አናጢ ነበሩ፡፡ ትንሹ ሙጋቤ ባልተለመደ መልኩ ሥርዓት ያለውና ጥብቅ ታዳጊ ነበር፡፡ በርግጥ አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜ ነው ያሳለፈው፡፡ ሁለቱንም ታላላቅ ወንድሞቹን በሞት ያጣው ገና በህጻንነቱ ነበር፡፡ አባቱ በደቡብ አፍሪካ የጄሱይት ሚሽን ዘንድ ለመስራት ከቤተሰቡ ከተለዩ በኋላ ወደ ቤት አልተመለሱም፡፡ በዚህም የተነሳ መምህር የነበሩት እናቱ፣ሙጋቤንና ሦስት ወንድሞቹን ለብቻቸው ማሳደግ ነበረባቸው። ሙጋቤ ከብት በመጠበቅና ገንዘብ በሚያስገኝ የጉልበት ሥራ በመሰማራት፣ እናቱንና ቤተሰቡን እየደገፈ ነው ያደገው፡፡  
ብቸኛው የነፃነት ማግስት መሪ
ሙጋቤ እ.ኤ.አ በ1963 የብሪቲሽን ቅኝ አገዛዝ የሚታገለውን ZANU የተሰኘ የተቃውሞ ንቅናቄ መሰረቱ፡፡ በ1980 የብሪቲሽ አገዛዝ ሲያከትም የአዲሲቷ የዚምባቡዌ ሪፐብሊክ ጠ/ሚኒስትር ሆኑ። በ1987 የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመረጡ። ሙጋቤ አገሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ብቸኛው የዚምባቡዌ መሪ ናቸው፡፡  
ለረዥም ዓመት በወህኒ ቤት
ሙጋቤ የወግ አጥባቂውን አናሳ - ነጭ የርሆዴዥያ መንግስት የሚቃወም ንቅናቄ መሪ ነበሩ፡፡  ይሄን ተከትሎም ወህኒ ቤት ተወርውረዋል። ከ1964-1974 ለአስር ዓመት ያህልም ታስረው ነበር፡፡ በወህኒ ቤት ሳሉ ታዲያ ሥራ አልፈቱም። ሌሎች እስረኞችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተምሩ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከለንደን ዩኒቨርስቲ በርቀት ትምህርት ሁለት የህግ ድግሪዎችን አግኝተዋል፡፡
ከፖለቲካ በፊት መምህር
ምንም እንኳ በደቡባዊ ርሆዴዥያ ብዙ ሰዎች ከሰዋስዎ ትምህርት ባያልፉም ሙጋቤ ግን ደህና ትምህርት ለማግኘት ዕድል ቀንቷቸዋል፡፡ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ድረስ በሚሲዮናውያን የተማሩት ሙጋቤ፤በ1945 ዓ.ም ከካቱማ ቅዱስ ፍራንሲስ ዛቪዬር ኮሌጅ ተመርቀዋል፡፡ ለቀጣዮቹ 15 ዓመታትም በርሆዴዥያና በጋና ያስተማሩ ሲሆን ተጨማሪ ትምህርታቸውንም በደቡብ አፍሪካው ፎርት ሃሬ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡
ህዝባቸውን አስተምረዋል
በአምባገነኑ ሙጋቤ ላይ በርካታ ትችቶች ቢሰነዘሩም የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ የአገራቸውን የትምህርት ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ መቀየራቸው ግን ማንም የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡ በሳቸው የአገዛዝ ዘመን ማንበብና መጻፍ የሚችለው የዚምባቡዌ ህዝብ ወደ 90 በመቶ ገደማ ደርሷል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ትምህርት ወዳድነታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገራል፡፡ ሙጋቤ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች 7 ድግሪዎችን የተቀበሉ ሲሆን ኢኮኖሚክስ፣ ትምህርት፣ አስተዳደር፣ህግና የመሳሰሉትን ያካልላል፡፡
የማንቀላፋት ልማድ ተጠናውቷቸዋል
ለበርካታ ዓመታት ዚምባቡዌን በመምራት የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤በተለያዩ ስብሰባዎችና ኮንፍረንሶች ላይ ሲያንቀላፉ በተደጋጋሚ በካሜራ ተይዘዋል፡፡ አንዳንዶች ይሄን የማንቀላፋት ሱሳቸውን ከዕድሜ ጋር ሲያገናኙት፣”ብዙ ስለሚያስቡ ነው” ብለው ምክንያት የሚሰጡም አሉ፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ግን እሳቸው በተለያዩ አቀማመጦች እንቅልፋቸውን መለጠጥ ይችሉበታል፡፡ አገራዊ ጉባኤ ይሁን ዓለም አቀፍ ለሳቸው ለውጥ የለውም፤ ጉባኤው እስኪጠናቀቅ ድረስ የእንቅልፍ ሱሳቸውን በቅጡ ይወጡታል፡፡
በቅርቡ የተያዙት የናይጄሪያ አዲሱ ፕሬዚዳንት ጀነራል ሙሃማዱ ቡሃሪ ሲመተ - በዓል ላይ ነበር። እንደተለመደው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ በሰሃራ ሪፖርተሮች የካሜራ ዓይን ውስጥ ወድቀዋል - ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፡፡
የክብር ድግሪዎችን ተነጥቀዋል
ሙጋቤ በተለይ በ1980ዎቹ ዓመታት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የክብር ድግሪዎችንና ማዕረጎችን ተቀብለው ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል----በአገራቸው ከነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የዲሞክራሲያዊ ሂደት መጨናገፍ ጋር በተያያዘ ቢያንስ ሦስቱን ተነጥቀዋል፡፡
በጁን 2007 ዓ.ም የእንግሊዙ ኢድንበርግ ዩኒቨርሲቲ በ1984 ዓ.ም የሰጣቸውን የክብር ድግሪ ሰርዞባቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዓለም አቀፍ ታዋቂ ሰው ላይ የሰጠውን የክብር ድግሪ ሲነጥቅ ሙጋቤ የመጀመሪያው ነበሩ ተብሏል፡፡ በጁን 2008 ዓ.ም የማሳቹሴት ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ በ1986 ዓ.ም የሰጣቸውን የህግ የክብር ድግሪ ነጥቋቸዋል፡፡ በሴፕቴምበር 2008 ደግሞ የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በ1990 ዓ.ም የሰጣቸውን የህግ የክብር ድግሪ መልሶ ወስዶባቸዋል፡፡ ምን ይሄ ብቻ ---- በ1994 ዓ.ም ከእንግሊዟ ዳግማዊት ኤልዛቤት የተሰጣቸውን የክብር ማዕረግም በጁን 2008 ዓ.ም ተነጥቀዋል፡፡
ከሥልጣን የመውረድ ሃሳብ የላቸውም
ሮበርት ሙጋቤ ለ7 ጊዜ ያህል በምርጫ ያሸነፉ ቢሆንም ምርጫዎቹ ግን በማጭበርበርና መራጮችን በማስፈራራት የተካሄዱ እንደነበር ይነገራል፡፡ ብዙዎች “ሙጋቤ እንዴት ሥልጣን አይሰለቻቸውም?” ብለው ይጠይቁ ይሆናል፡፡ የሚገርመው ግን እሳቸው ከሥልጣን የመውረድ ሃሳቡ እንኳን የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ በመጪው የ2018 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመወዳደር ዕቅድ እንዳላቸውም በቅርቡ አረጋግጠዋል፡፡ የዕድሜዬ መግፋት ጥንካሬዬን አልቀነሰውም ብለዋል - የ91 ዓመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ፡፡
 መጻህፍት አሳትመዋል  
ሙጋቤ በርካታ መጻህፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን ከእነሱም መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-
The Third Chimurenga: Inside the Third Chimurenga (2001)
War,Peace and Development in Contemporary Africa (1987)
The Role of the University in the process of Social Transformation (1983)
Our War of Liberation (1983)

Read 4535 times