Monday, 06 March 2017 00:00

የታላቅነት ጥያቄ?!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

    ታላቅነት ምንድነው? አገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ሆና ታውቅ ነበር ወይ? ታላቅ ከነበረች ታላቅ የሆነችው በየትኛው አስተሳሰብ ነበር? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ከነበርን ታላቅነታችንን መቼ፣ እንዴትና በምን ምክንያት አጣነው? አግኝተን ያጣነው ከሆነ ታላቅነታችንን ዳግም ማምጣት እንችላለን ወይ፤ ከቻልን መቼና እንዴት?
ከላይ በቀረቡት ስድስት ጥያቄዎች ዙሪያ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተከታታይ መድረኮች ለመወያየት ያቀደው ‹‹ነገረ ጥበብ ማዕከል››፤ ቅዳሜ የካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ የመጀመሪያውን ስብሰባ አካሄዷል፡፡
‹‹ነገረ ጥበብ ማዕከል›› በተቋም ደረጃ መንቀሳቀስ ከጀመረ አራት ዓመቱ ቢሆንም በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ በግላቸው ጥናትና ምርምር በማድረግ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ አባላት እንዳሉት ተገልጧል፡፡ በዕለቱ መድረኩን ይመሩ የነበሩት ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ እና መምህር መኮንን ፀጋዬ እንዳብራሩት፤ አስተሳሰብን ማዕከል አድርገው በብዙ ጉዳዮች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡
በጥንቱ ዘመን የሰው ልጅ በእጽዋት ምን ሲጠቀም እንደቆየ ማጥናት አንዱ ሥራቸው ነው፡፡ ከከርሰ ምድር ጋር በተያያዘ በሚያደርጉት ጥናት ያገኙት አንድ የ‹‹ዘይት›› ዓይነት ድንጋይን ወደ ጭቃነት እንደሚለውጥ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡ ‹‹የአክሱም ሐውልትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ድንጋይ በመፈልፈል ሳይሆን ድንጋዩን ወደ ጭቃ በሚለውጠው ‹ዘይት› እየተቦካ ተገንብተዋል የሚል እምነት አለን›› ብለዋል፤ አጥኝዎቹ፡፡
በዚህ ዘርፍ ባደረግነው ፍተሻ 364 የድንጋይ ዓይነቶች እንዳሉ ደርሰንበታል ያሉት የማዕከሉ አባላት፤ በከርሰ ምድር ጥናታችን ያገኘነው ነው ያሉት ሌላው የ‹‹ዘይት›› ዓይነት ፀሐይ የተሠራችበትን ተፈጥሯዊ ሚስጥር አመላካች መሆኑን ሲገልጹ፣ ‹‹ከውሃ ጋር ሲቀላቀል ባህሪውን የሚለውጠው ይህ ተፈጥሯዊ ‹ዘይት›፣ አንድ የቡና ሲኒ መጠን ያለው ፈሳሽ ብቻ ለሁለት ዓመት ያህል ያለማቋረጥ ይነዳል፡፡ በመጨረሻ የሚቀረው አመድም ደረጃው ከፍተኛ የሆነ ማዳበሪያ ይሆናል›› በማለት ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡
ከጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸው መሐል የፊደልና ቁጥር ሚስጥራትን መመርመር፣ጥበብና ዕውቀት የሚሰጡ ምግብና መጠጦች ላይ ጥናት ማድረግ ሲሆኑ በዋሻዎች የሚገኙ የፍጥረታትና የጥበብን ምንነት የሚገልጹ መጻሕፍትን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹ነገረ ኢትዮጵያ አንዱ የጥናታችን ክፍል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ኢትዮጵያን የተመለከተ ጥያቄ አንስተን ለመነሻ እንዲሆነን ‹ታላቅነት ምንድነው?› በሚለው አወያይ ሀሳብ ዙሪያ፤ የእኛን መረዳት ጨምሮ የተለያየ አመለካከት እንዲንሸራሸር ይህንን መድረክ ያዘጋጀነው፡፡›› ብለዋል፡፡   
በአሁን ዘመን በሉላዊነት (በግሎባላይዜሽን) ምክንያት ብዙ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ሃሳብ እያጡ ነው፡፡ አንድ ሰው የራሱ የሆነ ሀሳብ ከሌለው የራሱ የሆነ ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም፡፡ ትውልዱ የራሱ ሀሳብ እንዲኖረው ከተፈለገ የማሰብና የመናገር ነፃነት መፈጠር አለበት፡፡ አንድ ሀሳብ ትልቅ ሀሳብ ነው ማለት የሚቻለው ሁሉንም አመለካከት ማክበር የሚችል ከሆነ ነው፤ያከብራል ማለት ይቀበላል ማለት አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ገዥ ሀሳብ የመሆን ዕድል አለው…ሲሉ አብራርተዋል፡፡
‹‹ታላቅ ነበርን ታላቅ እንሆናለን እንላለን። ይህን አባባል በመጀመሪያ የተናገረው ቋረኛው አጼ ቴዎድሮስ ነበር፡፡ አሁን እኛም ይህንኑ ኃይለ ቃል  ደጋግመን እንፈክረዋለን፡፡ የኢትዮጵያን ሕዳሴ እናረጋግጣለንም እንላለን፡፡ የዚህ ታላቅ ጉዳይ ባለቤት ነበርን ካልን ታላቅነት ለእኛ ምንድነው? በትልቅ ፎቅ ቤት ውስጥ መኖር? ከሰማይ መና የሚወርድለት ሕዝብ መሆን? ብዙ መብላት፣ መጠጣትና በፈንጠዚያ መኖር?›› በማለት ጥያቄዎችን ደርድረው፣ የ‹‹ነገረ ጥበብ ማዕከል›› ለጥያቄው ያስቀመጠው መልስ ነው በማለት፣ በስድስት ክፍሎች የዘረዘሩትን ትንታኔ አቀረቡ፡፡
1ኛ - ታላቅ የሆነ የራሱ የሆነ ሕልውና አለው። በራሱ የቆመ ነው፡፡ ጫካ ውስጥ ገብተን ሚዳቆ ብንጠራ አንበሳ አይመጣም፡፡ ሚዳቆ የሚመስል አንበሳ ከመጣ የሚዳቆው ሕልውና በአንበሳው ተውጦ ጠፍቷል ማለት ነው፡፡
2ኛ - ታላቅ የሆነ ለራሱ መጠቀሚያ እንዲሆነው (ከፈጣሪ ወይም ከተፈጥሮ) የተሰጠው በረከትና ሀብት አለው፡፡ ሚዳቆ የሚመገበው ሣርና የሚጠጣው ውሃ ተችሮታል፡፡ ይህንን በረከት ካጣና በሌሎች እርዳታ መኖር ከጀመረ ታላቅነቱን አጥቷል።
3ኛ - ታላቅ የሆነ የራሱ የሆነ አቅም አለው። አንድ ነገር ለማድረግም በራሱ አቅም ይወስናል፡፡ ሚዳቆ ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላኛው ለመንቀሳቀስ ፈልጎ ረጂ ካሻው፣ ታላቅ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱን አጥቷል ማለት ይቻላል፡፡
4ኛ - ታላቅ የሆነ ተጽእኖ የማሳደር አቅም አለው፡፡ የራሱ የሆነ ሥልጣንም አለው፡፡ ሚዳቆ የበላያቸው እንዲሆን የተፈቀዱለትን እንስሳት “ከፊቴ ዞር በሉ” ሲላቸው ገሸሽ ካሉለት፣ የራሱ የሆነ ሥልጣን እንዳለው ማሳያና ሥልጣኑንም በአግባቡ መጠቀሙን ያመለክታል፡፡
5ኛ - ታላቅ የሆነ ሕብረት አለው፡፡ ሚዳቆ አየርን ቢጠላ፣ ወንዝን አልይ ቢል፣ እጽዋት ድራሻቸው እንዲጠፋ …ቢመኝ ይችላል፤ በውጤቱ ግን ቀድሞ ጠፊው ሚዳቆው ይሆናል፡፡
6ኛ - ታላቅ የሆነ ጥበብ አለው፡፡ ሚዳቆ ከእሱ በታች ላሉ ፍጥረታት የበላይ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ከእሱ በላይ ላሉት፣እሱ የበታች መሆኑን ከተረዳ፣ የመኖር ዘዴና ብልሀቱ ገብቶታል ማለት ይቻላል፡፡
በምሳሌያዊ አገላለጽ የቀረበውና የታላቅነት መገለጫ ናቸው ያሏቸውን ስድስቱን ማሳያዎች፤ ሚዳቆውን በሰው፣ እንስሳቱን በሕዝብ፣ መልክዐ ምድሩን በአገር በመለወጥ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ሌሎች በደከሙበት ላይ ተንተርሶ፣ የሌሎችን ሀሳብና እውቀት የራሱ ለማድረግ የሚሞክር መቼውንም ቢሆን የራሱ የሆነ ሕልውና እንደማይኖረው፤ የራሱ የሆነ ሀብትና ንብረት የሌለው ቤተሰብ፣ ታላቅ ቤተሰብ ለመባል የሚጎድለው ነገር እንዳለ፤ አንድ ሥራ አቅደው ለመተግበር በራሳቸው ተቸግረው የሌሎች መንግሥታትና ሕዝቦችን እርዳታና ትብብር የሚጠይቁ አገራት የራሳቸው አቅም እንደሌላቸው ያሳያል በሚል ማብራራታቸውን ቀጠሉ፡፡
አንዱ አገር በሌላኛው በቀላሉ እጁ ከተጠመዘዘ ተጽእኖ አሳዳሪ ሳይሆን ተጽእኖ የሚያርፍበት ተሸናፊ አገር መሆኑን ፤የራሱ የሆነ ሀሳብ፣ እውቀትና አቋም ቢኖረውም ጠቅላይና ገዥ ለሆነ ሀሳብ ክብርና እውቅና የሚሰጡ ግለሰቦች፣ ህዝብና አገራት ለሕብረት መዳበር ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን፤ ድምፅ በአየር እንደሚጓዝ የተረዱ ሕዝቦች ሞባይል ስልኮችን መፍጠራቸው የጥበብ ሚስጥር የገባቸው መሆኑን እንደሚያሳይ …  ማብራሪያና ገለጻ ሰጡበት።
‹‹ነገረ ጥበብ ማዕከል›› ለታላቅነት ካስቀመጠው ትርጉም አንጻርም ሆነ የዕለቱ ስብሰባ ታዳሚዎች ከግል መረዳታቸው በመነሳት ‹‹ታላቅነት ምንድን ነው?›› በሚለው የመወያያ ርዕስ ላይ ያላቸውን ምላሽ፣ አስተያየትና ጥያቄ እንዲያቀርቡ መድረኩ ክፍት ሆነ፡፡
ሁሉም ታላቅ አይሆንም፤ሁሉም ታናሽ አይሆንም፡፡ ሀብትና እውቀት ኖሮት በተግባሩ ታናሽ የሚሆን አለ፡፡ ሀብት፣ ዝናና እውቅና ሳይኖረው እውነተኛና ሐቀኛ በመሆኑ ምክንያት ብቻ ታላቅ የሚሆን አለ፡፡ ለእኔ ታላቅነት ለአገር መስዋእት መሆን ነው፡፡
ሰውን በግል፣ ሕዝብን በጋራ፣ አገርን በጥቅል ታላቅ የሚያደርጋቸው ያስቀመጡት ዓላማና ሊደርሱበት የሚመኙት ግብ ነው፡፡
አቅምንና ችሎታን ማወቅ ነው ታላቅነት፡፡
የሰውንና የተፈጥሮን ታላቅነት ማወቅና ማክበር በራሱ ታላቅነት ነው፡፡
ባቀዱትና በለፉበት ጉዳይ ውጤታማና ስኬታማ መሆን መቻል በራሱ ታላቅነት ነው፡፡
በጠዋት በጣም ሰፊና ብዙ ሀሳብ ውስጥ ነው የገባነው፡፡ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜትም ተሰምቶኛል፡፡ ትውልዱ የራሱ የሆነ ሀሳብ የለውም ተብሎ በየዘመናቱ እንደተወቀሰ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን እያጥላላው ነው ለዛሬ የደረስነው፡፡ ወጣቱ በግሎባላይዜሽን ተጽእኖ ስር መሆኑ በማሕበራዊ ድረ ገጾች መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ አንስታይንን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የፈጠራ ሥራቸውን ማሳካት የቻሉት ከቀደማቸው ትውልድ ባገኙት እውቀት በመታገዝ ጭምር ነው፡፡ ወጣቱ የራሱ የሆነ ሀሳብ የለውም በሚለው ጉዳይ አልስማማም፡፡ ወጣቱ የራሱ የሆነ ሀሳብ አለው፡፡ የትኛውን ታላቅነት ስለሚያስገኘው ሀሳብ ነው የምንነጋገረው? የፖለቲካ፣ የሀይማኖት፣ የሳይንስ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል…ስለ የትኛው ሀሳብ ነው እየተነጋገርን ያለነው ?
የጎዳና ተዳዳሪውን ጉዳይ ብናነሳ፤ በጎዳና እየኖሩ የልጅ ልጆቻቸውን ያዩ የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ፡፡ በየትኛው አስተሳሰብ ነው እነዚህ ችግሮች የተፈጠሩት? የትኛውስ እሳቤ እነዚህን ችግሮች ይቀርፋቸዋል? በቅድሚያ መጥፋት ያለበት እሳት፣ መቀረፍ ያለበት በርካታ ችግር … እያለብን በዚህ ሰዓት ስለ ታላቅነታችን መነጋገሩ ምን ጥቅም አለው?
የሰውን ልጆች ችግር ለመቅረፍ የተፈጥሮና የሕብረተሰብ ሳይንስ ምሁራን ብዙ ለፍተው የታሰበው ውጤት ሳይገኝ ደክሟቸው ቆመዋል። በሀይማኖት ሰበብ የሰው ልጆች ደም እየተቃቡ ለዘመናት ስለኖሩ በዚህ መንገድ ከዚህ በላይ መጓዝ እንደማይችሉ ግልጽ ሆኗል፡፡ ሕይወት ቀጣይ ነው። ከቀጠለ አዲስ፣ ሁሉን የሚያግባባና የሚያስማማ ሀሳብ ያስፈልጋል፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት በባቡር ቢመሰል፣ ሳይንስ አንዱ ፉርጎ ነው፤ ሀይማኖት ሌላው ፉርጎ፡፡ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው … ተቀጣጥለው ስለሚጓዙ ካሰቡበት ለመድረስ በልዩነት ውስጥ ጠቅላይ ለሆነ ሀሳብ ተገዥ መሆን የግድ ይሆናል። ገዥ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች፣ ሕዝቦችና አገራት ‹‹ታላቅ›› የመሆናቸው ዋነኛ ማሳያ ነው በሚለው ማጠቃለያ የዕለቱ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
‹‹ታላቅነት ምንድን ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ከዕለቱ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከተሰጠው ትርጉም ይልቅ በ‹‹ነገረ ጥበብ ማዕከል›› የቀረበው ትንታኔ፣ ለአምስቱ ጥያቄዎች ምን መልስ ይኖራቸው ይሆን? በሚል ጥያቄ የሚያጭር ብቻ ሳይሆን ጉጉትም ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹አገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ሆና ታውቅ ነበር ወይ? ታላቅ ከነበረች ታላቅ የሆነችው በየትኛው አስተሳሰብ ነበር? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ከነበርን ታላቅነታችንን መቼ፣ እንዴትና በምን ምክንያት አጣነው? አግኝተን ያጣነው ከሆነ ታላቅነታችንን ዳግም ማምጣት እንችላለን ወይ፤ ከቻልን መቼና እንዴት ?›› መልሶቹ እንደመጠየቁ ቀላል ይሆኑ ይሆን? የከርሞ ሰው ይበለን!!  

Read 1527 times