Monday, 06 March 2017 00:00

ዎተርኤይድ ኢትዮጵያ 1.3 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የቀጣይ 6 አመታት የፕሮግራም ስትራቴጂውን ይፋ አድርጓል
     በኢትዮጵያ በውሃ፣ የአካባቢ ንጽህና እና የስነ ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ብቸኛው መንግስታዊ ያልሆነ አለማቀፍ ድርጅት የሆነው ዎተርኤይድ ኢትዮጵያ፤ ባለፉት ስድስት አመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባከናወናቸው ተግባራት 1.3 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን ከ2016 እስከ 2021 ባሉት ቀጣይ አመታት የተጠናከረ ስራ ለማከናወን የሚያስችለውን አዲስ የፕሮግራም ስትራቴጂ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ አድርጓል፡፡
ለስድስት አመታት በዘለቀውና ዘንድሮ በተጠናቀቀው የፕሮግራም ስትራቴጂ ዘመን ከአጋር አገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በአገሪቱ አምስት ክልሎች የሚገኙ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የውሃ፣ የአካባቢ ንጽህናና የስነ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጸው ዎተርኤይድ ኢትዮጵያ፤ በቀጣይም አገልግሎቶቹን በስፋት ለማዳረስ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን አስታውቋል፡፡
የውሃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በካፒታል ሆቴል በተከናወነው የድርጅቱ የፕሮግራም ስትራቴጂ ማስተዋወቂያ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የውሃ፣ የአካባቢ ንጽህናና የስነ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን እ.ኤ.አ እስከ 2030 በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሁሉም ዜጎች በተሟላ መልኩ ለማዳረስ የተያዘውን አገራዊ እቅድ በማሳካት ረገድ ዎተርኤይድ ኢትዮጵያ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ውስጥ የተካተተውን የውሃ አቅርቦት ግብ ማሳካት ችላለች ያሉት ወ/ሮ ፍሬነሽ፤ የአካባቢ ንጽህና ግብን ለማሳካት በተደረገው ጥረት መልካም ውጤት ቢመዘገብም፣ ግቡን ለማሳካት ተጨማሪ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ በመጥቀስ፣ ለዚህ ደግሞ ዎተር ኤይድን ጨምሮ በመስኩ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚያደርጉት የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የውሃ፣ የአካባቢ ንጽህናና የስነ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን አጠቃላይ አቅርቦት ፍትሃዊና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማሟላት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ወ/ሮ ፍሬነሽ፤ ለዕቅዱ መሳካት ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዎተርኤይድ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ቤተልሄም መንግስቱ በበኩላቸው፤ ባለፉት 20 አመታት በአገሪቱ የውሃ፣ የአካባቢ ንጽህናና የስነ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን አጠቃላይ አቅርቦት ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ጉልህ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሰው፣ ዎተርኤይድ ኢትዮጵያም በመስኩ የተመዘገቡ ውጤቶችን በተቀናጀ አሰራር የበለጠ በማሳደግና የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችለውን የቀጣይ አመታት የፕሮግራም ስትራቴጂ መቅረጹን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይም በመስኩ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮችን በመቅረፍ፣የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የዘላቂ ልማት ግቦችንና በሴክተሩ የተቀመጠውን የ”ዋን ዋሽ” ብሄራዊ ፕሮግራም ግቦችን ለማሳካት በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝም አስረድተዋል፡፡
የዎተርኤይድ ኢትዮጵያ አገልግሎቶችን በፍትሃዊና በዘላቂነት ለማዳረስ የሚያስችሉ የስርዓት ቀረጻ ስራዎችን እንዲሁም በብሄራዊ፣ በክልላዊና በወረዳ ደረጃ በመስኩ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማድረግ ከጀመረ 30 አመታትን ያህል ያስቆጠረ ሲሆን አለማቀፉ ዎተርኤይድም በ37 የተለያዩ የአለማችን አገራት ሰፋፊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

Read 1035 times