Monday, 06 March 2017 00:00

የፓኪስታን አየር መንገድ 7 ትርፍ ሰው መጫኑን አመነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      የፓኪስታን አለማቀፍ አየር መንገድ ባለፈው ጥር ወር ላይ ከካራቺ ወደ ሳኡዲ አረቢያዋ ከተማ መዲና ባደረገው በረራ፣ መጫን ከሚገባው የመንገደኛ ቁጥር በላይ 7 ትርፍ መንገደኛ መጫኑን እንዳመነ ኒውስ 18 ድረ-ገጽ ዘግቧል፡፡  የአየር መንገዱ ሰራተኞች ጥር 20 ቀን በረራውን ባደረገውና 409 ሰዎችን የማሳፈር አቅም ባለው ቦይንግ 777 አውሮፕላን ውስጥ ተጨማሪ 7 መንገደኞችን በማሳፈር፣ ለአደጋ የሚያጋልጥ ጉዞ እንዲደረግ በመፍቀዳቸው በህግ እንደሚጠየቁና አየር መንገዱ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝም ዘገባው ገልጧል፡፡
  በትርፍ የተጫኑት መንገደኞች ረጅም ሰዓታት የሚፈጀውን ጉዞ ያለምንም መቀመጫ፣ ቆመው እንደጨረሱት የአገሪቱ ጋዜጦች ቢዘግቡም፣ አየር መንገዱ ግን ይህን ማስተባበሉንና በረራው ያለምንም ችግር እንደተጠናቀቀ ማስታወቁን ድረ ገጹ ጠቁሟል።  አውሮፕላኖች መጫን ከሚገባቸው የመንገደኛ ቁጥር በላይ እንዲጭኑ መፍቀድ፣ የኦክስጂን አቅርቦት ካለመኖር፣ ከመተፋፈግና ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አውሮፕላኑንና ተሳፋሪዎቹን ለከፋ አደጋ እንደሚያጋልጥና በአቪየሽን ህግ መሰረት ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያስጥልም ዘገባው አስታውቋል፡፡

Read 1113 times