Monday, 06 March 2017 00:00

ኦባማ ለፈረንሳይ ፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ የጠየቁ ከ42 ሺ በላይ ደርሰዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ኦባማ እና ሚሼል አዳዲስ መጽሃፍትን ለማሳተም ከ65 ሚ. ዶላር በላይ ይከፈላቸዋል
    የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦማባ በዘንድሮው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ የሚጠይቅ የድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ በድረገጽ አማካይነት መጀመሩንና እስካሁን ድረስም ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች ሃሳቡን በመደገፍ ፊርማቸውን ማስፈራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዘመቻው አስተባባሪዎች ኦባማ በመጪው ግንቦት ወር  በሚካሄደው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመሩት፣ ሃሳባቸው ህጋዊ ተቀባይነት እንደማያገኝ ቢያውቁም፣ ለምርጫው በዕጩነት የቀረቡት የአገሪቱ ዜጎች ይህ ነው የሚባል ብቃት የሌላቸው መሆናቸውን ለማስመስከር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሳምንቱ መግቢያ  ላይ በተጀመረውና ለቀናት በዘለቀው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች ድጋፋቸውን መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አስተባባሪዎቹ 1 ሚሊዮን ያህል ለማድረስ አቅደው በስፋት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ኦባማ 2017 የሚል መፈክር የተጻፈባቸው ፖስተሮች በስፋት መሰራጨታቸውን አመልክቷል፡፡
ኦባማ ለፈረንሳይ ፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ የሚጠይቀው የድጋፍ ድምጽ ከሚሊዮን አልፎ ቢሊዮንና ትሪሊዮን ፊርማዎችን ቢያሰባስብም፣ የአገሪቱ ህግ የውጭ ዜግነት ያለው ሰው ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንደማይችል የሚደነግግ በመሆኑ ከንቱ ድካም ሆኖ እንደሚቀር ዘገባው አስረድቷል፡፡
በሌላ በኩል፣ ባራክ ኦባማ እና ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ፤ ሁለት አዳዲስ መጽሃፍቶቻቸውን ለንባብ የሚያበቁበትንና ከ65 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያገኙበት የተነገረለትን የህትመት ስምምነት ውል መፈጸማቸው ባለፈው ማክሰኞ ተዘግቧል፡፡
ኦባማ በዋይት ሃውስ የነበራቸውን የስምንት አመታት ቆይታ የሚዳስሱበትን፣ ሚሼል ደግሞ አነቃቂ ይዘት ያለው ነው የተባለውን መጽሃፍት ለንባብ ለማብቃት ከታዋቂው አሳታሚ ኩባንያ ፔንጉዊን ራንደም ሃውስ ጋር በድምሩ ከ65 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስምምነት መፈጸማቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ የመጽሃፍቱ ርዕሶችም ሆነ ለገበያ የሚበቁበት ጊዜ ይፋ አለመደረጉን ጠቁሟል።
ኦባማ እና ሚሼል ከአሳታሚው ኩባንያ ከሚከፈላቸው ገንዘብ ዳጎስ ያለውን ለበጎ አድራጎት ስራ ለማዋል ማቀዳቸውን ያስታወቀው ዘገባው፤ መጽሃፍቶቹን ለማሳተም በርካታ አሳታሚ ኩባንያዎች መወዳደራቸውንና  ፔንጉዊን ራንደም ሃውስ የተጠቀሰውን ገንዘብ በማቅረብ ውድድሩን ማሸነፉንና ይህ ዋጋ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የማስታወሻ መጽሃፍ ክፍያ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን አመልክቷል፡፡
የስልጣን ዘመናቸው ማብቃቱን ተከትሎ ለንባብ ባበቋቸው መጽሃፍት ከፍተኛውን ክፍያ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዘው የቆዩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ክሊንተን በ2004 ለንባብ ላበቁት ማይ ላይፍ የተሰኘ መጽሃፍ ከአሳታሚያቸው የተከፈላቸው ገንዘብ 15 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርም  ጠቅሷል፡፡
ኦባማ ከዚህ ቀደም ለንባብ ያበቋቸው ድሪምስ ፍሮም ማይ ፋዘር እና ዘ ኦዳሲቲ ኦፍ ሆፕ የተሰኙ ሁለት መጽሃፍት በሚሊዮኖች ቅጂ መቸብቸባቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የሚሼል ኦባማ ብቸኛ መጽሃፍ ደግሞ በ2012 ያሳተሙት አሜሪካን ግሮውን የተባለ በምግብ ዝግጅትና በተክሎች እንክብካቤ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሃፍ መሆኑን አስረድቷል፡፡

Read 1089 times