Monday, 06 March 2017 00:00

አፍሪካ ዘንድሮም ለሽልማት የሚበቃ መሪ አላገኘችም

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የሞ ኢብራሂም የ5 ሚ. ዶላር ሽልማት፣ ብቁ መሪ በመታጣቱ ለ5 አመታት አልተሰጠም

    የላቀ የአመራር ብቃት ላሳዩ ውጤታማ የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች በየአመቱ የ5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚያበረክተው ታዋቂው ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ ዘንድሮም እንደ አምናው ሁሉ ለሽልማት የሚመጥንና መስፈርቱን የሚያሟላ መሪ አለማግኘቱን አስታወቀ፡፡
አምና ባካሄደው ውድድር መስፈርቱን የሚያሟላ መሪ በማጣቱ ሽልማቱን ሳይሰጥ የቀረው ፋውንዴሽኑ፤ ዘንድሮም ከአህጉሪቱ የቀድሞ መሪዎች መካከል ለሽልማት ብቁ የሆነ ሰው ባለማግኘቱ ለ2016 ያዘጋጀውን ሽልማት ለማንም ሳይሰጥ ለማለፍ መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተቋሙ ሽልማቱን መስጠት ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ ባሉት አመታት፣ ያወጣውን መስፈርት የሚያሟላ ብቁ መሪ በማጣቱ ሳቢያ የዘንድሮውን ሽልማት ጨምሮ ለአምስት ጊዜያት በተመሳሳይ ሁኔታ አመታዊ ሽልማቱን ሳይሰጥ መቅረቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከዚህ ቀደም መስፈርቱን በአግባቡ አሟልተው የተቋሙን ሽልማት ለመቀበል ከበቁ የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች መካከል የሞዛምቢኩ ጆኣኪም ቺሳኖ እና የቦትስዋናው ፌስቱስ ሞጋኤ እንደሚገኙበትም አክሎ ገልጧል፡፡
የቀድሞ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከሚገመገሙባቸውና ለሽልማት ከሚበቁባቸው የተለያዩ የተቋሙ መስፈርቶች መካከል በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጦ ስልጣን መያዝ፣ በህግ ከተቀመጠው የስልጣን ዘመን ገደብ በላይ አለመግዛትና የተለየ የአመራር ብቃት ማሳየት የሚሉት እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አመራርን የማስረጽና ውጤታማ የቀድሞ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን የማበረታታት አላማ ያለው ተቋሙ፤ በቴሌኮም ዘርፍ አለማቀፋዊ ስኬትን ባስመዘገቡት ታዋቂው ሱዳናዊ ሞ ኢብራሂም ተቋቁሞ አመታዊ ሽልማት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

Read 1838 times