Print this page
Monday, 06 March 2017 00:00

‹‹የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስን በዓለም አቀፍ ካርታ አስገባለሁ›› - ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

  ከ2 ወራት በፊት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ  ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስን በፕሬዝዳንትነት እንደሾመ ይታወቃል፡፡ የቀድሞው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ በስፖርቱ ላይ አዳዲስ ለውጦች እና ተስፋዎች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከሳምንታት በፊት ከዓለምአቀፉ የቅርጫ ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር FIBA ኦፊሴላዊ ድረገፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስን በዓለም አቀፍ ካርታ አስገባዋለሁ›› በማለት የተናገሩት ዶክተር አሸብር   ‹‹የቅርጫት ኳስ ስፖርት በአዲስ ምዕራፍ ለማንቀሳቀስና ለመምራት ዝግጁ ነኝ፡፡ የመጀመርያው እቅዴ ብሄራዊ ቡድኖችን ማቋቋም ነው›› ብለዋል፡፡ የFIBA አባል አገራት ብዛት 213 ሲሆን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ 124ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የቅርጫት ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን /FIBA/ በ1932 እ.ኤ.አ የተመሰረተ ሲሆን ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ፣ ሚተስ ከተማ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን በዓለም የቅርጫት ኳስ ስፖርት ያሉ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ክለቦች፣ ደጋፊዎች በድምሩ ከ450 ሚሊዮን  የቅርጫት ኳስ ባለድርሻ አካላትን እያስተደዳረ ይገኛል፡፡
ዶክተር አሸብር የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በማደራጀት መነሳቱ ከለውጦቹ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ስፖርት ቁልፍ ቦታ ያለው ናሽናል ባስኬት ቦል አሶሴሽን (ኤንቢኤ) በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
ስለሆነም የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ልዩ ልዩ የሥልጠናና ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎችን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያን ቅርጫት ኳስ በቀላል ወጪ ትልቅ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻልም የኤንቢኤ ዳይሬክተሩ ስምምነቱን ባደረጉበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
በቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ ውድድር ከ50 ዓመታት በፊት በFIBA የተካሄደው አፍሮ ባስኬት ቶርናመንት ነበር፡፡ በወንዶች ብሄራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ ተሳትፎ ነበር፡፡ በ1962 እ.ኤ.አ ላይ በአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮንና የወንዶች ብሔራዊ ቡድኑ ሲሳተፍ በ5ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰው፡፡  በኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የተመሰረተው በ1956 ዓ.ም ሲሆን በ1962 በተካሄደው የቅርጫት ኳስ አፍሪካ ካፕ በመሳተፍ የአህጉራዊው ኮንፌዴሬሽን አባል ሆኗል፡፡ የዓለም አቀፉ ቅርጫፍ ኳስ ማህበራት አባል ሆኖ የተመዘገበው ደግሞ በ1949 እ.ኤ.አ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቅርጫፍ ኳስ ብሄራዊ ቡድን በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ ከአፍሪካ 5 ምርጥ ቡድኖች አንዱ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በወንዶች  ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ሲያካሄድ የቆየ ቢሆንም ለአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች የነበረው ተሳትፎ ለረጅም ዓመታት የተዳከመ ሆኖ ቆይቷል፡፡

Read 3893 times