Monday, 06 March 2017 00:00

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ያለውን ታሪክ ዘንድሮ ሊቀይር ይችላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  በኢትዮጵያ ውክልና የቀጠለው  ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ታሪክ ዘንድሮ ሊቀይር ይችላል፡፡  
በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  በቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ  የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦር 5ለ0 በመርታት ወደ አንደኛ ዙር ማጣርያ የገባ ሲሆን  በቀጣዩ የ1ኛ ዙር ማጣርያ የሚገናኘው ከኮንጎ ብራዛቪል ምርጥ ክለብ ጋር ነው፡፡ የኮንጎው ክለብ ኤሲ ሊዮፖርድስ ዲ ዶሊሴ ሲሆን በቅድመ ማጣርያው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከካሜሮኑ ዩኤምኤስ ዴ ሎውም ተገናኝቶ 2ለ2 አቻ ቢለያይም  ከሜዳ ውጭ ባስቆጠረ በሚለው ደንብ ወደ 1ኛ  ዙር ማጣርያ ገብቷል፡፡
በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  ቅዱስ ጊዮርጊስ የኮንጎውን ክለብ በደርሶ መልስ ጥሎ ማለፍ ከቻለ፤ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ አዲስ ምእራፍ በመክፈት ወደ ምድብ ፉክክር መሸጋገር ይችላል፡፡ በውድድሩ ከሚገኘው ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማትም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ቢበዛ ዋንጫውን በማሸንፍ  2.5 ሚሊዮን ቢያንስ በምድባቸው በመጨረሻ ደረጃ በመጨረስ 550ሺ ዶላር ማግኘት ስለሚቻል ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣርያዎች ላይ ውድድሩ በካፍ አዲስ መዋቅር መካሄድ ከጀመረበት ከ1997 እኤአ ወዲህ በነበረው ተሳትፎና አጠቃላይ ውጤቱ 61ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ለ8 ጊዜያት ቅድመ ማጣርያውን በማለፍ ለመጀመርያ ዙር ሲበቃ ለ4 ጊዜያት ከውድድሩ የተሰናበተው በቅድመ ማጣርያ ነበር፡፡
የኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፖርድስ ዲ ዶሊሴ በ1953 እኤአ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የኒያሪ ጭራቆች በሚል ቅፅል ስሙ ይጠራል፡፡ የክለቡ ስታድዬም በዶሊሴ ከተማ የሚገኘው ስታዴ ዴኒስ ሳሳዎ ኑጉዌሶ ሲሆን የክለቡ አሰልጣኝ ቤልጅማዊው ፓትሪክ አውሴመስ ናቸው፡፡ በኮንጎ ፕሪሚዬር ሊግ 3 ጊዜ፤ በጥሎ ማለፍ 5 ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ትልቁ ውጤቱ በ2012 እኤአ ላይ የኮንፌደሬሽን ካፕ ዋንጫን ማግኘቱ ነው፡፡ በካፍ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 22 ጨዋታዎችን አድርጎ 6 ጊዜ ድል፤ 5 ጊዜ አቻ እንዲሁም 7 ጊዜ ሽንፈት አስመዝግቦ በጠቅላላ ውጤት 28ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡፡

------------

               ቅዱስ ጊዮርጊስ - ኤሲ ሊዮፓርድስ (በትራንስፈርማርከት ድረገፅ) ንፅፅር

• የተጨዋቾች ብዛት 26 - 34
• አማካይ እድሜ 25.9 ዓመት - 26.8 ዓመት
• የውጭ ተጨዋቾች ብዛት 6 – 12
• የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ብዛት 9- 10 የግብ ጠባቂ አማካይ እድሜና የዝውውር ዋጋ ግምት
• 27.33 ዓመት እና 128ሺ ፓውንድ - 24.7 የተከላካዮች አማካይ እድሜና የዝውውር ዋጋ ግምት
• 26.22 ዓመት እና 298ሺ ፓውንድ - 28.9 ዓመት እና 935ሺ ፓውንድ የአማካዮች አማካይ እድሜና የዝውውር   ዋጋ ግምት
• 25.11 ዓመት 170ሺ ፓውንድ - 20.6 ዓመት እና 893ሺ ፓውንድ የአጥቂዎች አማካይ እድሜና የዝውውር ዋጋ ግምት
• 23.20 ዓመት 446ሺ ፓውንድ - 22.89 ዓመት እና 468ሺ ፓውንድ የሙሉ ቡድን የዝውውር ዋጋ ግምት
• 1.04 ሚሊዮን ፓውንድ - 2.30 ሚሊዮን ፓውንድ

--------------------------------------------------------

                   ‹‹የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስን በዓለም አቀፍ ካርታ አስገባለሁ››
                           - ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ

     ከ2 ወራት በፊት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ  ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስን በፕሬዝዳንትነት እንደሾመ ይታወቃል፡፡ የቀድሞው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ በስፖርቱ ላይ አዳዲስ ለውጦች እና ተስፋዎች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከሳምንታት በፊት ከዓለምአቀፉ የቅርጫ ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር FIBA ኦፊሴላዊ ድረገፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስን በዓለም አቀፍ ካርታ አስገባዋለሁ›› በማለት የተናገሩት ዶክተር አሸብር   ‹‹የቅርጫት ኳስ ስፖርት በአዲስ ምዕራፍ ለማንቀሳቀስና ለመምራት ዝግጁ ነኝ፡፡ የመጀመርያው እቅዴ ብሄራዊ ቡድኖችን ማቋቋም ነው›› ብለዋል፡፡ የFIBA አባል አገራት ብዛት 213 ሲሆን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ 124ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የቅርጫት ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን /FIBA/ በ1932 እ.ኤ.አ የተመሰረተ ሲሆን ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ፣ ሚተስ ከተማ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን በዓለም የቅርጫት ኳስ ስፖርት ያሉ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ክለቦች፣ ደጋፊዎች በድምሩ ከ450 ሚሊዮን  የቅርጫት ኳስ ባለድርሻ አካላትን እያስተደዳረ ይገኛል፡፡
ዶክተር አሸብር የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በማደራጀት መነሳቱ ከለውጦቹ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ስፖርት ቁልፍ ቦታ ያለው ናሽናል ባስኬት ቦል አሶሴሽን (ኤንቢኤ) በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
ስለሆነም የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ልዩ ልዩ የሥልጠናና ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎችን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያን ቅርጫት ኳስ በቀላል ወጪ ትልቅ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻልም የኤንቢኤ ዳይሬክተሩ ስምምነቱን ባደረጉበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
በቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ ውድድር ከ50 ዓመታት በፊት በFIBA የተካሄደው አፍሮ ባስኬት ቶርናመንት ነበር፡፡ በወንዶች ብሄራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ ተሳትፎ ነበር፡፡ በ1962 እ.ኤ.አ ላይ በአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮንና የወንዶች ብሔራዊ ቡድኑ ሲሳተፍ በ5ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰው፡፡  በኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የተመሰረተው በ1956 ዓ.ም ሲሆን በ1962 በተካሄደው የቅርጫት ኳስ አፍሪካ ካፕ በመሳተፍ የአህጉራዊው ኮንፌዴሬሽን አባል ሆኗል፡፡ የዓለም አቀፉ ቅርጫፍ ኳስ ማህበራት አባል ሆኖ የተመዘገበው ደግሞ በ1949 እ.ኤ.አ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቅርጫፍ ኳስ ብሄራዊ ቡድን በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ ከአፍሪካ 5 ምርጥ ቡድኖች አንዱ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በወንዶች  ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ሲያካሄድ የቆየ ቢሆንም ለአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች የነበረው ተሳትፎ ለረጅም ዓመታት የተዳከመ ሆኖ ቆይቷል፡፡

Read 2202 times