Monday, 06 March 2017 00:00

የአዳም “የስንብት ቀለማት”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “--አሁን አሁን በፈረንጆች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ጭምር ስትዘወተር የምንሰማት            አንድ ጥያቄ አለች፡ “ሁሉን ነገር እኛ ጀመርነው ልትሉ ነው?” ሁሉን ነገር ባይሆንም አብዛኛው ነገር ሲጀመር፣          እኛም ከጀማሪዎቹ መካከል መሆናችንን የሚያስረዳ ረጅም ታሪካችንን “ደብተራ የጻፈው” እያሉ ማጣጣል           የምሁርነት ወፌ ቆመች ሆኗል፡፡---”
                       ሙሉጌታ አለባቸው

     (ካለፈው የቀጠለ)
ማርቆስ ረታ እና አዳም ረታ
“የስንብት ቀለማት”ን አንብቤ ስጨርስ ከጥቂት ዓመታት በፊት ያነበብኩት አንድ መጽሐፍ ትዝ አለኝ፡፡ መጽሐፉ በማርቆስ ረታ የተጻፈ ሲሆን ርዕሱ፡- “Organic Ethiopia: Reflections on its search, confusion and way-out” ይላል፡፡ ከርዕሱ እንደምንረዳው አዳም በልቦለድ ያሳየውን ማርቆስ በኢ-ልቦለድ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ማርቆስና አዳም በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ፡፡ (የአባታቸው ስም አንድ መሆኑ ግን ተራ አጋጣሚ ነው)፡፡
በጠቅላላው የሚያመሳስላቸው ሁለቱም አገር አቀፍ ችግር ውስጥ መሆናችንን ማመናቸው፣ የችግሩን ምንጭ ለመመርመር መሞከራቸውና መፍትሄ ለማመላከት ጥረት ማድረጋቸው ነው፡፡ ሁለቱን ማነጻጸር ሰፊ ጥናትን የሚጋብዝ ቢሆንም ለአሁኑ ግን በቀላሉ ከሚታዩ አንድነታቸው መካከል ምሳሌዎች እያነሳሁ ለማየት ልሞክር፡፡ የመጀመሪያው ተመሳስሎ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጉዳይ ነው፡፡ መያዶች በሁለቱም መጽሐፎች በሰፊው ተነቅፈዋል፡፡ የገንዘብ አቅማቸውን ተመክተው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰቦችን በመጨቆን፣ የራሳቸውን እምነትና ባሕል ለመጫን የሚሞክሩ የምዕራብ መሣሪያዎች ሆነው ቀርበዋል፡፡
“the once independent and proud citizens [Ethiopians] are being taught to look up to the same people – who have come to make a living out of the disaster they [NGOs] exaggerate and magnify through their subtle art of censoring our activities by offering and/or refusing sponsorship.”
ማርቆስ ይሄን የመያዶችን የ“ማሰልጠን” ተልዕኮ ሲተች፤ እነሱ ኋላ ቀር የሚሉት ጎጂ ልማድ በባሕላችን ግን ተወዳጅ እሴት ሊሆን እንደሚችል ለማስረዳት በአስራ ስድስት አመቷ የሃምሳ አመት ሰው ያገባች አክስቱን ምሳሌ ያመጣል፡፡ “…ሁለት ወንድና አንድ ሴት ልጅ ወልደዋል፡፡ በሙያ ዳኛ የነበረው ባለቤቷ ወደ ፍርድ ቤት ለሥራ ሲሄድ በጣም ቆንጆ ከመሆኗ የተነሳ ቤት ውስጥ ቆልፎባት ይሄድ እንደነበር ነግራኛለች፡፡ ይሄን እያስታወሰች ስትነግረኝ ፊቷ ላይ የማየው ፈገግታ እንጂ ሐዘን አለመሆኑ ያስገርማል፡፡ በዚህ የባሏ ድርጊት ውስጥ ለእሷ የሚታያት ቀናተኛ አፍቃሪ እንጂ ጨቋኝ ባል ስላልሆነ ደስ ተሰኘች (she felt flattered)!” ይላል፡፡ በስንብት ቀለማት ደግሞ ፊያሜታ የምታስተዳድረው ሴሕጤድ የሚባል አስቂኝ ስም ያለው መያድ፤ የሴቶች ግርዛትን የማስቆም አጀንዳ ይዞ ይሠራል፡፡ ፊያሜታ ለረጅም ጊዜ ውጪ አገር ቆይታ የመጣች ሴት ስለሆነች “ሰልጥናለች” (ገንዘብ የለኝም ለማለት “አምስት ሣንቲ የለኝም” ስትል ግን ሆን ብላ የድሮውን ብትረሳም ያደገችበትን ፍቃ ማጥፋት እንደሚሳናት ታጋልጣለች)፡፡ የልጅነት አፍቃሪዋ ሚኒሊክ ባዩ፣ አገር ቤት መምጣቷን ሰምቶ፣ ሰላምታ ሊያቀርብላት ሴቶችን ሰብስባ ስልጠና የምትሰጥበት ቦታ ድረስ ይሄዳል፡፡ አላውቅህም ብላ መካዷ ሳያንስ ከሩቅ ቆሞ እስክትጨርስ የሚጠብቃትን ሚኒሊክ፣ የፈረንጅ ሀሳብ ተውሳ “አይገርምም? ቬሪ ስትሬንጅ ዚስ ኢዝ ስቶኪንግ” ትላለች፡፡ ተራኪው ይቀጥላል… “ከአሜሪካ ለቃቅማ ያመጣቻትን ዝባዝንኬ ፅንሰ-ሀሳብ  እዚህ አገር ላይ ስትለጥፍብን፡፡ “ስትሄድ ስከተላት” የተባለ ዘፈን አልሰማችም? የሐበሻ ሴት ስቶክ ተደርጋ እንደምትበላ፤ ስቶክ ካላደረጓት ያልፈለጓት እንደሚመስላት አታውቅም? ረሳች?”
ሁለቱ ጸሐፍት የሚመሳሰሉበት ሌላው ነጥብ ምሁሩንና አርቲስቱን የሚተቹበት መንገድ ነው፡፡ ለማርቆስ ያለንን ነገርና የጎደለንን ነገር ለይቶ ማሳየት የሚገባው አርቲስቱ ነው፡፡ “the crux of most of our confusion is our ignorance of what we have and what we have yet to seek, as well as the widespread cluelessness of Ethiopian virtues we have to retain” ካለ በኋላ ይሄንን ባለማድረጋቸው አርቲስቶቻችንን ይወቅሳል። አርቲስቶቻችን ታሪክና ቅርሳችንን የሚያጎላ፤ በአገራችን እንድንኮራ የሚያደርገን የጥበብ ስራ ከመሥራት ይልቅ ቀለብ የሚሰፍሩላቸው መያዶች (ምዕራባዊያን) ያስቀመጡትን አጀንዳ ለማሳካት ይለፋሉ ይላል፡፡ አዳም ደግሞ ምሁራኖቻችንን እንደዚህ ይተቻል፡- “የኢትዮጵያ ምሁራን ሲሰለጥኑና ዘሮቻቸውን ሊያሰለጥኑ ሲፈልጉ መጽሐፎች ይጽፋሉ፡፡ በነዚህ መፅሐፎች ውስጥ የሚጠይቁት አንድ ዋነኛ ጥያቄ እኔ ምን አለኝ? ሳይሆን እነሱ ምን አላቸው? ነው አሉ፡፡…ካላመናችሁ ጃፓን እንደምን ሰለጠነችን ያንብቡ… ”
የሁለቱ “ረታዎች” ተመሳስሎ ለማሳየት ከምሞክረው በላይ አስገራሚ ነው፡፡ አንዳንድ ነጥቦች ላይ ተመሳስሏቸው ቃል በቃል ወደሚመስል ደረጃ ይጠጋል፡፡ በሀሳብ ደረጃ ደግሞ አገራችን አሁን ለገባችበት አዘቅት ዋና ተጠያቂ ከሚያደርጉት አካል አንዱ፣ያ ትውልድ ነው፡፡ ለራሱ “ያ ትውልድ” የሚል መጠሪያ ያወጣው ትውልድ አባላት፤“ሁሉም ያለ ምህረት፣ ያለ በቂ ትንታኔ የዛሬውን ወጣት ያማሉ፡፡ … ወጣት ድሮ ቀረ አንዱ ወሬያቸው ነው፡፡ ድሮ ሲሉ እኛ ማለታቸው ነው” ይላል - “የስንብት ቀለማት”። Organic Ethiopia ደግሞ፡- “Whenever they make comparisons, they are likely to assert that the good old days, their days, were far more productive, the real times of the flourishing Ethiopian art [and by extension everything else!]” ይለናል፡፡
አዳምና ማርቆስን በሁለቱ መጻሕፍት እንመዝናቸው ብንል፣ ሁለቱም አገራቸውን የሚወዱ ብሔረተኞች እንደሆኑ መገመት የተለየ ጥበብ አይጠይቅም፡፡ ምዕራባዊያንን አስመልክቶ nearly xenophobic የሆነ አመለካከት አላቸው ለማለት ደግሞ የሁለቱን መጽሐፍት ይዘት መረዳት ብቻ ይበቃል፡፡ በስንብት ቀለማትም ሆነ በOrganic Ethiopia “ባዴ” (ባእድ ከሚለው የመጣ የአዳም ቃል) አይበጀንም፡፡  አስፈላጊነቱን ሳንመረምር የምናስገባው የባዴ ሀሳብና ቁስ ግን ልዩ ክብር ይሰጠዋል፡፡ አገር በቀል ከሆነ ተመሳሳይ ሀሳብና ቁስ ጋር ሲወዳደር የባእዱ ይሰገድለታል፡፡ ለዚህ አንዱ ማስረጃ “ከውጭ የመጣ ነው” በሚል አረፍተ ነገር ታጅቦ የሚቀርብ ማንኛውም ነገር የሚታይበት መንገድ ነው፡፡ አዲስ አሠራር፣ መድሃኒት፣ ልብስ፣ ስልጠና ወዘተ “ከውጭ የመጣ” ከተባለ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄ ሳይቀርብ ምርጥነቱ ይረጋገጣል። “ከሌላ ፕላኔት” እንደመጣ ሁሉ እንደ ተአምር ይታያል፡፡ በአዳም መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዘ ድሬክ የተባለ ሆቴል (ስሙ እንኳ ከውጭ የመጣ!) “…የተገነባባቸው እቃዎች ከድንጋዩ በስተቀር ሁሉም ከውጭ የመጡ ናቸው፡፡ ከውጭ ሀገር አይደለም። ከውጭ (ለብቻው ቃሉ ሲባል ሌላ ፕላኔትም ይመስላል)…” በማርቆስ መጽሐፍ ተመሳሳይ ሀሳብ በሌላ አገላለጽ እንዲህ ተቀምጧል፡-
“The operative parameter already established as an unquestionable truth is that whatever domestic is bad/ inferior and whatever comes from overseas good superior. Not just in goods, but in everything; the Ethiopian way of doing things is considered to be inferior, uncivilized.”
በመጨረሻም ሁለቱ መጽሐፍት/ጸሐፊያን አገራችንን ከገባችበት ችግር ለማውጣት የሚያስቀምጡትን የመፍትሔ ሀሳብ አንስቼ ወደ ቀጣዩ ርዕስ ልሂድ፡፡
“Let’s drop all ‘-isms’… they blind most of us from seeing what really concerns us” የሚለው ማርቆስ፤ ያለንና የሌለንን ከለየን በኋላ የራሳችን የምንለው አገር በቀል የሆነ “ኢዝም”፤ አዲስ ሕልዮ ማፍለቅ ይቻለን ይሆናል ይላል፡፡ “…we may even come across with the notion of coining our own – home grown –ism.”
ይሄ ደግሞ በስንብት ቀለማት የተነሳው አብይ ጭብጥ ነው፡፡ “ተረት ይመስላል” በሚለው የመጨረሻው ምዕራፍ፤ ምትኬ በተባለች ልጃገረድና መንኮብያ በተባለ ልዕለ ሰብዕ (እርሱም የማንነታችን ሁሉ ወኪል የሆነ) ተራክቦ፣ የሰው ስጋ ለብሶ የሚወለድ ማኩታ፤ የራሳችን የምንለው አዲስ ሀሳብ አዲስ ማንነት ይወለዳልና!
ማንነት ምንድን ነው?
“…የመቃረን አለም ውስጥ እንዳለ ያውቃል፡፡ ወደ ኋላ መመለስ ʻማንነትʼ ከሆነ፤ ፒሳ ሳይሆን ማንነቱ ቂጣ ነው፤ ያውም ያረረ፡፡ ሀምበርገር አይደለም ማንነቱ፤ ጣቶቹ ላይ እየፈረሰ የሚያስቸግረው ዘንጋዳ እንጀራ ነው፡፡ ማንነት ከተባለ የሚለብሰው የካልቪን ክላይን ውስጥ ሱሪ አይደለም፤ በጠጡና ጉድፍ ሬንጅ ያስመሰላት ቁምጣው ወይ ንፍጡ ያጠቆራት ጥብቆ ናት፡፡ ብዙ ሳያስብ ያውቃል፤ ማንነቱ በየጎጆ ቤቱ በወባ ትንኝ ከነዘር ማንዘሩ መዘረር ነው። ማንነቱ ወደ ኋላ እየተገፋ ዝንጀሮ ጋ ባይደርስ እንኳን በልጅነቱ ቀን ከቀን በየሜዳው የነሰነሰው ኮሌራው ነው፡፡ ዘፈኑ ሮክ ኤንድ ሮል ሳይሆን ሆዱ በወስፋት ሲጮህ ነው፡፡ ማንነቱ ከአፍንጫው ላይ በእጁ ሲያባርር የገደላቸው የትንኝ ሞሳዎች ናቸው። ማንነቱ ሄኒኬን ቢራ ማንቃረር ሳይሆን በእንትን እንኩሮ የጠየመ አሰር ትፍ ማለት ነው፡፡ ማንነቱ መንገድ ዳር ቁጢጥ ብሎ ለበቆሎ ጠባሽ የተናገራት ‹ያቺኛዋን ስጠኝ› ዐማርኛ ናት፡፡ ማንነቱ በጥፍር የነገለ አውራ ጣቱን በቆሻሻ ጨርቅ መተኮስ ነው። አሸናፊ ባያወራውም፡፡ እነ ዶክተር ባያወሩትም። አናፍርበትም ብለው ግን ሌላ ሌላ ቢዘባርቁም……”
ከላይ የቀረበው ገለጻ በልቦለዱ ውስጥ የሚገኘው አሸናፊ የተባለ ሰው ማንነት ነው፡፡ አሸናፊ ግን ይሄን በአደባባይ ይክደዋል፡፡ ልክ እንደ አሸናፊ ሁሉ ብዙ ኢትዮጵያዊ የመቃረን ዓለም ውስጥ ነው፡፡ ፈረንጅ ለመምሰል ይለፋል፤ ግን እውነተኛ ማንነቱን የሚደብቅባት ትንሽ ልቡ እሺ አትለውም፡፡  በቅርብ ዘመን የተራቆተ ኪሱን እየጠቆሙ “ማንነት የለህም” ሲሉት የሚለግሱት ስንዴና ዘይት እንዳይቀርበት “አዎ የለኝም” ብሎ ምንም ይሆናል፡፡ ማንነቱ አባቶቹ በማለዳ መሠልጠናቸው፤ የዓለምን እውቀትና ምስጢር የተረዱ መሆናቸው መሆኑን ዘንግቷል (እንዲዘነጋ ተደርጓል)፡፡
አሁን አሁን በፈረንጆች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ጭምር ስትዘወተር የምንሰማት አንድ ጥያቄ አለች፡ “ሁሉን ነገር እኛ ጀመርነው ልትሉ ነው?” ሁሉን ነገር ባይሆንም አብዛኛው ነገር ሲጀመር፣ እኛም ከጀማሪዎቹ መካከል መሆናችንን የሚያስረዳ ረጅም ታሪካችንን “ደብተራ የጻፈው” እያሉ ማጣጣል የምሁርነት ወፌ ቆመች ሆኗል፡፡ እና ደብተራ የጻፈው እንደሆነስ? “የማንም አገር ታሪክ የተጻፈው በደብተራ ነው” (የስንብት ቀለማት)። ጅምር ምሁሬ ሆይ! የፈረንጅ ደብተራ የለውም መሰለህ? አለው! የማርቆስ ረታን አባባል ልጠቀምና እንዲህ “ክፍ” ልበላችሁ… Get off mom’s back!
«የስንብት ቀለማት» እንዲህ ይላል… “[ፈረንጆች] የእኛን አንድ የአራዳውን ፈረሰኛ ግን እንድንጠላ ይገፋፉናል፣ እምቢ ስንል ደሞ ያጣጥሉታል፣ ማጣጣላቸው አልገባን ካለ በዓለም ያስቁብናል፣ ሳቂ ካጡ ታሪካችንን ይዘርፉናል፣ እሱም የእኛ ነው ብለን ከተሟዘዝን በተለይ ጥቋቁር ሽርኮቻቸውን (ሀበፈረንጃውያንን) ሰብስበው ወደ እኛ እየጠቆሙ የበለጠ ያስቁብናል፡፡ እንዲህም ይነዘንዙናል፡፡ አሁንስ በዛ (ባይበዛም) ሁሉን ነገር እኛ ጀመርነው ልትሉ ነው? (አልወጣንም)፡፡”
ቆይ ሁሉን ነገር ጀመርነው ብንልስ? ራሳቸው ያመጡትን ሳይንስ ምስክር ጠርተን የሰው ዘር የጀመረው እዚች አገር ላይ ነው ብንልስ? የሰጡንን መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰን አዳምና ሄዋን የኖሩት ኢትዮጵያ ነበር ብንልስ?
የመጣንበትን ግን ስለዘነጋነው የራሳችን ነው የምንለው ነገር እንዳልነበረን፣ ድርጊታችን ሁሉ በመቅዳት ላይ ተመስርቷል፡፡ ይሄን ምክንያታዊ አድርገን ለማስረዳት የምንጠቀመው አባባል ደሞ “ፈረንጆችኮ…” ብሎ የሚጀምር ፉርሽ ማነጻጸሪያ ነው፡፡ «የስንብት ቀለማት» ከውጪ አገር ስንወስድ ቢያንስ ወደ ራሳችን ሁኔታ እንዲስማማ እያደረግን መውሰድ እንዳለብን ለማስረዳት ፌብሩወሪ አስራ አራት የሚከበረውን ʻቫለንታይንስ ዴይʼ በአደይ ቀን ተክቷል፡፡ የበአሉ መገለጫ የሆነውን ቀይ ቀለምና ቀይ አበባ እኛን ወደሚገልጸው ቢጫ ቀለምና አደይ አበባ መልሷል፡፡
ሐበሻ (ሌሎች እሱን ለመስደብ ያወጡለትን ስም እንደ ምርቃት ቆጥሮ በኩራት ራሱን በዚህ ስም የሚጠራ አስገራሚ ሕዝብ) ሲቀዳ ሙልጭ አድርጎ ነው፡፡ አንድን ጸጉረ ልውጥ ሀሳብ ሲቀበል ከእነ እርግማኑ ነው፡፡ “ለወንድሞችህ የባሪያዎች ባሪያ ሁን” የሚል እርግማን በግልጽ የተጻፈባቸውን ቅዱሳን መጻሕፍት እንኳን አሜን ብሎ ተቀብሎ “ይንጀላጀላል”፡፡ ሳላይሽ እንዲህ ታብራራዋለች፡- “የምቀኝነቴ ትክክለኛነት የሚታወቀኝ አንዱ የካም መረገም ታሪክ ነው፡፡ ሁሉም ከኦርቶዶክስ እስከ ጴንጤ ያለ ሐበሻ የተሰደበበትን ቅዱስ መጽሐፍ ተሸክሞ ይንጀላጀላል፡፡ በውዳቂ ታሪክ የእናቱን ጡት ሳይጠግብ ከቄስ፣ ከክርስትና አባትና ከድፎ ዳቦ ጋር ተባብሮ ራሱን ይገድላል፡፡ እኔ ማሳበቢያ ሆንኩ እንጂ ሲፈጠር የተሰጠውን እርግማን ነው እንዳይረሳው የምሰጠው፡፡ ክርስቲያን ሐበሻ፣ እስላም ሐበሻ ሆይ፤ የካም እርግማንን አስብ፣ ለደይን ተመርጠሃል እላለሁ”
ለደይን የተመረጥንባቸውን መጻሕፍት እየገለጥንም ለልጆቻችን የአይሁድ ስም ማውጣት ልማድ ሆኗል። ምክንያታችን ሃይማኖታችንን መውደዳችን ወይስ የዝቅተኛነት ስሜት? «የስንብት ቀለማት» ይሄንንም ይጠይቃል፡፡ “ለምንድን ነው የዚህ አገር ሰው ልሳን እንደሌለው ሁሉ ለወለደው ልጁ ብቻ ሳይሆን ለውሻውም ስም ልመና ቁናውን ይዞ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሄደው? ሃይማኖቱን ስለሚወድ ነው ወይስ ዝቅተኛነትን ስለሚወድ?” መጠሪያ ስም ማንነት ነው፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ስያሜ ሲሰጡ እምነትና ተስፋቸውን እያስቀመጡ ነው፡፡ ማሕበረሰብ ልጆቹን ሲሰይም ማንነት ፍለጋ ባሕር ተሻግሮ ከሄደ ጤና ማጣቱን ሊያመላክት ይችላል፡፡ “…ለስም ለስምማ ዮሴፍ የይሁዳውያን ነው፡፡ ታዲያ ማንነቴን ለማግኘት እየሩሳሌም መሄድ አለብኝ?” ይላል ዶክተር ዮሴፍ፡፡ «ማሕሌት» ከተሰኘው የደራሲው የበኩር ሥራ ተጠልፋ «የስንበት ቀለማት» ውስጥ የተገኘችው ኤልዛቤልም ሌላ ምሳሌ መሆን ትችላለች፡፡ “ሰላማዊት”ን የመሰለ ሰላማዊ ስም እያላት በአመንዝራ ሴት ስም የምትጠራበት ኤልዛቤል የተባለ ስሟ መመረጡ በራሳችን ቋንቋ ከሚመርቁን፣ በባዕድ አፍ ቢረግሙን እንደምንመርጥ ያሳያል፡፡
«የስንብት ቀለማት» ለዚህ መፍትሔ የሚጠቁም ልቦለድ ነው፡፡ (ልቦለድ ስለው ቅር ይለኛል!) መፍትሔው ወደ ውስጣችን መመልከት ነው፡፡ እንደ ዮሐንስ ወላይሶ የራሳችንን ዐይኖች ማየት፡፡ ወይም ወደ ራሳችን መመልከት፡፡ እንደ እኔ እምነት፤ የመጽሐፉ ደራሲ ወደ ራሱ ተመልክቷል፡፡ የራሱን ዐይኖች አይቶ ያገኘው ደግሞ እስካሁን የሰጠንን መጽሐፍቱን ብቻ ሳይሆን “ሕጽናዊነት” የተባለ የአጻጻፍ ስልቱንም ነው፡፡
ሕጽናዊነት በስንብት ቀለማት
ደራሲው እንጀራ ላይ ተመስርቶ የፈጠረውን ሕጽናዊነት የተባለ የአጻጻፍ ስልት ለማዳበር በታሪክ መንገድ ወደ ኋላ ተጉዞ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት 1500 ዓመት ላይ ያርፋል፡፡ ይህ ጊዜ ኢትኤል የተሰኘ ንጉሥ ገዢ የነበረበትና ለመጀመሪያ ጊዜ የጤፍ እንጀራ የተጋገረበት ዘመን ነው፡፡ “ጥንታዊያኑ ሰዎች በምግቦቻችንንና አመጋገባችን ጨምሮ በእያንዳንዱ ድርጊት ውስጥ ምስጢር የማስቀመጥ ጠባይ እንዳላቸው ይገባኛል፡፡ እንጀራን ሲፈጥሩት፤ ያወረሱን ምግብን ብቻ አይደለም፡፡ በሙለኩለኤው፣ በአገራችንና በግለሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነትም ጭምር እንጂ” ይላል ደራሲው፡፡
በቅርጽ ረገድ ሕጽናዊነት ከእንጀራ የቀዳው ዋና ጸባይ አንዱ፣ ታሪክ ከሌላው ታሪክ ጋር በቀጫጭን የትረካ መስመሮች መገናኘቱ ነው፡፡ የእንጀራ ዐይኖች ከላይ ስናያቸው ራሳቸውን ችለው የቆሙ ቢመስሉም ከስር ግን ይገናኛሉ፡፡ በሕጽናዊነት ሰዎችና ነገሮች የማይገናኙ ቢመስሉም እንደ ደሴት ብቻውን የሚቆም አካል የለም፡፡ በሚዘረጋው የግንኙነት መረብ ውስጥ ሁሉም ገጸ-ባሕሪ ከሌላው ጋር በሆነ ዐይነት የሚታወቅም ሆነ የማይታወቅ መንገድ አንዱ ከሌላው ይያያዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሕጽናዊነት አንድ ንዑስ ገጽታ ተጨማሪ ታሪኮችን በሕዳግ ማስታወሻ መተረኩ ነው፡፡
ሕጽናዊነት የቅርጽና የይዘት ብልህ ውህደት ነው፡፡ አንዱ ያለ ሌላኛው መቆም አይችልም፡፡ ደራሲው በታሪክ መንገድ ላይ የኋሊት ተጉዞ እንጀራ ላይ ሲያርፍ፣ ጥረቱ አዲስ ቅርጽ የመፍጠር ብቻ አለመሆኑን ከድርሰቶቹ ይዘት ማየት ይቻላል፡፡ ሙሉ ሂደቱ ማንነትን  ፍለጋና ወደ ማንነት መመለስ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር “የስንብት ቀለማት”ን ሳየው… I just love how meticulous and intricate the whole book is! ረቂቅና እንከን የለሽ የታሪክና የሀሳብ አወቃቀሩ አጀብ የሚያስብል ነው፡፡ ሕጽናዊነት ከዚህ በላይ ሊሻሻል አይችልም፡፡ ፍጽምና ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የጎመራ ሕጽናዊነት ልበለው?
ደራሲው ከዚህ በፊት ሕዳግ ማስታወሻዎችን እንዴት በጥንቃቄ እንደሚያዋቅር ያየሁት “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” በተባለው መጽሐፉ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “ዱለት፣ ጎሬና ጎሮ” በተሰኘው ታሪክ፤“ስልጣኔ እና ምቀኝነት” የተባለ ምናባዊ ማጣቀሻ መጽሐፍ ይገኛል፡፡ በሰሌዳ ጎማ ወርቅ በተባሉ ጸሐፊ በ1900 ዓ.ም እንደተጻፈ የተነገረን ይሄው መጽሐፍ፣ የታተመው ሁመራ ማተሚያ ቤት እንደሆነም ተገልጾልናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ሁመራ ማተሚያ ቤት መታተሙ ነው፡፡ ለምን ሁመራ? የዚህ መልስ በዚያው ታሪክ ውስጥ በሌላ የሕዳግ ማስታወሻ ተቀምጦልናል። ምክንያቱ “የመግለጥ ቅጣት” ነው፡፡ ቅጣቱ እንደ ሕገ የተደነገገው እንዲህ ነው፡ “አንድ ደራሲ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከተወሰኑ ገጾች በላይ እንዲጽፍ አይፈለግም፡፡ ምክንያቱም ጥራት እንዳይወድቅ ነው ይባላል፡፡ ይሄን ለማበረታታት የቀለም ራሽን ተወስኗል፡፡ ይሄን ድንጋጌ የጣሰ ደራሲ እንደ ጥፋቱ መጠን መጽሐፍ እንዳያነብ ይከለከላል፡፡… ይህ ʻየመግለፅ ቅጣትʼ ይባላል፡፡ … ሳይገባቸው ወይም ሕጉን ሳይረዱት የነዚህን ደራሲያን ግጥሞች ያተሙ ማተሚያ ቤቶች ካሉበት ቦታ ተነቅለው በረሃ መሐል እንዲተከሉ ይደረጋል”
ሁመራ ማተሚያ ቤት የተባለውም ደራሲው/ዋ በሰሌዳ ጎማወርቅ የዚህ ቅጣት ሰለባ በመሆኑ/ኗ መጽሐፉ የታተመው ሕጉን ሳይረዳ የነዚህ ዐይነት ደራሲን መጽሐፍት ስለሚያትም ሁመራ በረሃ መሐል እንዲተከል በተደረገ ማተሚያ ቤት በመሆኑ ነው፡፡ በሕጽናዊነት ሆን ተብሎ እንጂ እንዲሁ የሚጨመር መረጃ አለመኖሩን ልብ ይሏል!
በስንብት ቀለማት ደግሞ በሕዳግ ማስታወሻ የተቀመጡት ብዙዎቹ ቀያይ መረጃዎች ደረቅ እውነቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ከዋናው ትረካ ተገንጥለው የተቀመጡ አይደሉም፤ እንዲያውም በዋናው ትረካ ውስጥ በገጸ ባሕሪያቱ ንግግር ውስጥ እዚህና እዚያ ተበትነው እናገኛቸዋለን፡፡ ዮሐንስ ወላይሶ ስለ ስንዝሮ ኮምፕሌክስ እና ስለ ማሞ ኮምፕሌክስ በሕዳግ ማስታወሻ ላይ አስረድተውን ያልፋሉ፡፡ ሀሳቡ ግን ትረካው ውስጥ እነ ፊያሜታ ከእነ ዶክተር አሳምነውና ከእነ ዶክተር ዮሴፍ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጠባይ ሆኖ ይመጣል፡፡ አቶ ዮሐንስ አሁንም በሕዳግ ማስታወሻ ስለ ሰዎች ድአ መለያየት (የአፍ እና የድርጊት መለያየት) ሲያነሱ ዋናው ትረካ ውስጥ ድአቸው የተለያየ ነው እንባላለን፡፡ “ለምን ይሆን ድርጊታቸውና አፋቸው የማይመሳሰለው? ለምንድን ድአቸው ከአንድ ፍጡር የመጣ አልመስል አለ? … ሰዎች በድርጊት እየቀረቡ በአፍ እንዴት ይርቃሉ? በአፍ እየቀረቡ እንዴት በድርጊት ይርቃሉ?…” በተጨማሪም አቶ ዮሐንስ ስለ ሃቅላዊያን በሰንጠረዥ ጭምር ካስረዱን በኋላ ምትኬ እንዲህ ትለናለች፡- “…ዕድሜ ልኬን የጎደለብኝ እኔ፡፡ የሃቅላዊያን ሊቀመንበር ነኝ…”
ሕጽናዊነት እንጀራ ላይ መመሥረቱን ያወደሱ እንደ ስንዱ/ሰነዱ ኬ. ገብረ ማሪያም አይነት ጸሐፍት፤ “እንጀራ የጋራ ስነ ልቦናችን ነው” ይላሉ። የደራሲው ሙከራም “እንጀራ በወል ልቦናችን ውስጥ የሚሰጠውን ሰፊ ቦታ ማሳየት መሆኑን እንጂ እንጀራን እንደ ስነ-ጽሑፋዊ ቅርጽ መጠቀም ብቻ አይደለም” ሲሉ ይመሰክራሉ፡፡ Adam’s experimentation with injera does not stop at the solid injera and its form. He also played with the place injera occupies in our collective psyche (so to speak)”. (An Ethiopian Life without Adam: 7-Kilo መጽሄት)
በዚህም ሕጽናዊነት የቅርጽ እና የይዘት ግሩም ውህደት ሆኗል፡፡ ቅርጹ ያለ ይዘቱ መቆም አይችልም። ይዘቱም እንደዛው፡፡ ደራሲው ታሪክን ሲቆፍር የአጻጻፍ ስልቱን ከማሻሻልም በላይ አገራዊ ማንነትን እያሰሰ እንደሆነ ከበርካታ መጻሕፍቱ እንረዳለን። ጠቅላላ ሂደቱም ወደዘነጋነው/እንድንዘነጋው ወደተደረገው ማንነታችን መመለስ ነው፡፡ በስንብት ቀለማት እንደታየው ደግሞ በዛሬ ዘመን ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያስጨንቁንን አገራዊ ችግሮች የሚያስወግድልን ምኞታዊ መፍትሄ  ማመላከት ነው፡፡
ሕጽናዊነትን የመሠረተው ከአገሪቷ ዕድሜ ጋር አቻ ሊሆን በሚችለው በእንጀራ ላይ መሆኑና አባቶቻችን የተዉልንን ምስጢራት ፈልፍሎ በማውጣት ላይ መጠመዱ አዳም ከተራ ደራሲነት በላይ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ለዚህ ነው «የስንብት ቀለማት» የአዲስ ርእይ፣ የአዲስ ርእዮትና የአዲስ አገር ምሥረታ መድበል ነው የተባለው፡፡ (ቴዎድሮስ ገብሬ፡ ድህረ ቃል)፡፡ ስንዱ ደግሞ “መረቅ ሁላችንንም የሚጠይቀን ታሪካችንን እንድናይና ነገ-አችንን አጥርተን እንድንስል ነው” ብላለች፡፡ ስንዱን በድጋሚ ለመጥቀስ “ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን አዳም የሌለበት ሕይወት ማለት ትንሣዔ የሌለው ሕይወት ነው” ስትል ጽፋለች፡፡
“…የማይቀር ትንሣኤሽን ሳልም…”
ቢነጋም ባይነጋም
የተፈቀረ አይዘነጋም፡፡
ከመቶ ዓመት በፊት ተወልደሽ ከመቶ ዓመት በፊት ብትሞቺም
እንደ ጉም እኖራለሁ ሳልተኛ፣ የማይቀር ትንሣኤሽን ሳልም፡፡
ያልተፈጠረ ጉንጭሽን
እንደ ሰማያዊ ስጦታ ስስም፡፡
(ሰዓሊና ገጣሚ ወርቁ ዕንቁባሕሪ)
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን የኖረችበት የሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥትን አውታርና ካስማ ሆኖ ያቆመው የሰሎሞን-ሳባ-ምንይልክ ተረክ ነው፡፡ የ1953ቱን የንዋይ ወንድማማቾች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ የተነሳው የተማሪዎች ንቅናቄ ግን ይሄን ሚት ፈተና ውስጥ ከተተው፡፡ “ክፋቱ ንቅናቄው ፍጹም ከመጽሃፉ የተነሳ የየሰውን ልብ በአናርኪዝምና በኒሂሊዝም መንፈስ ሞላ፡፡ ማፍረስ ብቻ፤ መንቀል ብቻ ግቡ ሆነ፡፡ ነፍስ ያላወቀው [ያ]ትውልድ፣ በነቀለው እሴት ፋንታ አዲስ አልተከለም። ባለፈው ሮማንስ ምትክ ሌላ ሮማንስ አላበጀም፡፡ (ማርክሲዝምና ሌኒኒዝም አዲሱ ሮማንስ ነው ካላልን በቀር)” (ቴዎድሮስ ገብሬ፡ ድህረ ቃል)፡፡  
የንቅናቄው ፋና ወጊዎች እነ ዋለልኝ መኮንን “ብሔራዊ ቀሚስ ብሎ ነገር የለም” ባሉበት ጽሑፋቸው (1969)፤ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት የሀሰት ነው ሲሉ ካዱ፡፡ “There is of course the fake Ethiopian Nationalism advanced by the ruling class and unwillingly accepted and even propagated by innocent fellow travellers”. ከዚያም ሰለሞናዊው ዙፋን ተሰበረ፡፡ ተረኩም ከአጼው መንግሥት ጋር ተቀበረ፡፡ በምትኩ ምን አመጡ? ሶሻሊስታዊ የእንጀራ አባቶቻቸውን እነ ሌኒንን እያጣቀሱ፤ “እውነተኛ nation state እንገንባ” አሉን፡፡ ይሄ እውነተኛ የተባለውስ ምንድር ነው ያልን እንደሆነ፤ It is a state in which all nationalities participate equally in state affairs, it is a state where every nationality is given equal opportunity to preserve and develop its language, its music and its history ይሉናል፡፡ ሁሉም ብሄረሰብ እየተነሳ ልገንጠል ቢልስ? ለሚለው ስጋታችን የሰጡን ምላሽ ደግሞ “ሶሻሊዝም’ኮ መጨረሻው አለም አቀፋዊነት ነው፤ ብንገነጣጠልም ተመልሰን አንድ እንሆናለን” የሚል ነበር፡፡ ይሄው ኤርትራ የራሷን ዕድል በራሷ ወስና ከተገነጠለች ሀያ አራት አመታት አለፉ፡፡ “ብንገነጣጠልም ተመልሰን አንድ እንሆናለን” ያሉን ተስፋ ግን ጉም እንደመዝገን ሆኖብናል፡፡
ዋለልኝ ስለ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት የሰበኩት ሶሻሊስት “ወንድሞቹ” በቆዳው ጥቁረት እየተሳለቁ በንቀት እንደሚያዩት ሳያውቅ ያለፈ “ነፍስ ያላወቀው ትውልድ” አባል ነበር፡፡ በማርቆስ ረታ አባባል፤ “አብዮታቸው አገራቸውንና ባሕሏን መረዳት ሳይሆን ስር ነቀል ለውጥ ማምጣትና ልክ እንደ ባእዳን አይነት ማድረግ ላይ ተጠምዶ ነበር” (Not to retain, not to comprehend the nation and its culture, but to change it, to do everything to make it look like the foreigners!) ሶሻሊዝም እና ዋለልኝ ሞተዋል፡፡ አገራችን ግን በዚያ ዘመን ጦስ ምክንያት ያለ ብሔራዊ ተረክ ቀርታለች፡፡ አገር አቀፍ ተረት አለመኖሩ ደግሞ አንድ ማህበረሰብ ትርጉም እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ “Myths are supposed to provide a dependable structure and sense of certainty, a firm foundation for a society’s sense of meaning.” (Mythic America)
አንድ አገር ያለ ብሔራዊ ተረክ፤ ያለ ሚት ቀረች ማለት አገሪቷ ነፍስ አልባ የመሆኗ ትእምርት ነው። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊያን የተዘፈቅንበት የነፍስ ዝቅጠት፤ የባህል መጥፋት፤ የማንነት ቀውስና ሐሲር፣ ያለ ሚት የመቅረታችን መዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡ (ቴዎድሮስ ገብሬ፡ ድህረ ቃል) ዛሬ በሃይማኖትና በዘር ተከፋፍለናል፡፡ ሁላችንንም የሚያግባባ፣ ሁላችንም በጋራ ልንቆምለት የምንችለው አንድም የወል ዓላማ የለንም፡፡ አገር ያለ ብሄራዊ ተረክ ቀርታለች፡፡
በሐሲር ጎዳና ሰከም ሰከም ከምትሉ የተማራችሁና ያልተማራችሁ ወገኖቼ መካከል ግን፤ እነሆ አዲስ አገራዊ ተረክ ለመፍጠር በነፍስ ወከፍ ተጋድሎ ያደረገ አንድ ደራሲ አገኘሁ፡፡ እውነት ግን በስንብት ቀለማት እንደሆነው ሁሉ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር፤ ዘየአትት ኃጢያተ ዓለም” ተብሎ የሚያድነን፤ ቤዛ ክሊኒክ ውስጥ የሚወለድ ማኩታ ይመጣልን ይሆን? ይፈጠርልን ይሆን ጠይም ክርስቶስ? “ዮም ተወለደ ቤዛ ኩሉ ዓለም” የሚል አምባር የሚያስርልን? ለአገራችን መድኃኒት የሆነ ዳግማዊ መልከ-ጸዴቅ ይወለድልን ይሆን?
እውነትም እንዲህ በመለኮታዊ ተዓምር ካልሆነ ከአገራዊ ዝቅጠታችን መውጣት የሚቻለን አይመስልም፡፡ ደራሲው ግን “There is no longer any religion of state… Religion has become something individual and concerns the conscience of each… it has nearly nothing to do with the reasons that determine the limits of various peoples” ከሚሉት ከእነ Ernest Renan ጋር የተስማማ ይመስላል፤ የሰሎሞን-ሳባ-ምንይልክን ተረክ የሚተካውን አዲሱን የስንዝሮ-ምትኬ-ማኩታ ሚት የሠራው ከሃይማኖት ነጻ አውጥቶ ነው፡፡ ወይም Edith Hamilton እውነተኛ ሚት ከሃይማኖት ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም (A real myth has nothing to do with religion) ባለችው ይስማማል፡፡
ደራሲው ይሄን መስመር ለማስያዝ በውብ ቋንቋ ብዙ ደክሟል፡፡ “ይህ ሁሉ የኪነት ድካም አዲስ ብሔራዊ ምንነት የመገንባት፣ አዲስ አገር የመመስረት ጣጣ ነው፡፡ እናም ድርሰቱን እንደ ብሔርተኛ ሐቲት (as a national discourse) ልንቆጥረው እንችላለን” የሚለው ቴዎድሮስ ገብሬ፤ ለመሆኑ አንድ ደራሲ ስለ አገር ምሥረታ ምን አገባው? ሲል ይጠይቃል። መልሱም “ምን ጥያቄ አለው” የሚል ነው፡፡ ቴዎድሮስ አስተያየቱን ሲያጠቃልልም፤“እንዲያውም ዓበይት ከያኒያን--ሜጀር አርቲስት--የኪነታቸውና የተውሀቧቸው ዳርቻ ላይ መድረሳቸው የሚረጋገጠው በእንዲህ ያለው ተግባር መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ” ይላል፡፡
በ“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ውስጥ ተነካነኪ የሚባል ጽንሰ ሀሳብ አለ፡፡ “በምትችለው መጠን ለአገርህ መልካም ነገር ለመሥራት መሳተፍ፡፡ አገርህን በተመለከተ ስለ ሁሉ ነገር ለማወቅ መጣር” ማለት ነው፡፡ “የስንብት ቀለማት” ደራሲ እንደ አንድ ብሔረተኛ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም እንደ ደራሲ ማድረግ የሚገባውን ከፍ ባለ ደረጃ አድርጎታል፡፡ ሰብእናውና ደራሲነቱ ሲጨመቅ ዶፍ ሆኖ የወረደው “መረቅ” ደግሞ እነሆ የስንብት ቀለማት ነው፡፡ አዳም የለየለት ተነካናኪ ሆኗል፡፡
ከጥቂት ጊዜ በፊት ከአንድ የአዳም ክሪቲክ ጋር ስንጨዋወት ለምን እንደምንወደው ጠይቆኝ ነበር፡፡ ያኔ ገና “መረቅ” እንኳን አልወጣም ነበር፡፡ የመለስኩለት መልስ ግን “የስንብት ቀለማት”ን ካነበብኩ በኋላ ይመስላል፡፡ ደራሲው ምን ሊሠራ እንደሚችል ቀድመን ገምተናል መሰለኝ (አንባቢዎቹ ነቢይ ሳንሆን አንቀርም) “አዳምን የምወደው የገባንበትን አገር አቀፍ ችግር ከስሩ መርምሮ ምንጩን ስለሚጠቁመኝ፤ መውጫውንም ስለሚያመላክተኝ ነው…” አልኩ፡፡ ይሄ እውነተኛ ፍፃሜውን ያገኘው አሁን ነው፡፡
አዳም የኢትዮጵያን ልብ በፊደል ሥሎ እንካችሁ ብሏል፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙ “በአገርኛ ቋንቋም እንደዚህ መጻፍ ይቻላል እንዴ?” የሚያስብል ነው፡፡ ዐማርኛን ሰልጥኖባታል! ድርሰቱ በርካታ የእውቀት ዘርፎች በተራቀቀ ስልት ጥቅም ላይ ውለው በልዩ ኪናዊ አቀራረብ ተቀርፀውበታል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በተለየ መንገድ እንድናይ ያደርገናል። “የስንብት ቀለማት” ልቦለድ ብቻ ሳይሆን፤ ደራሲው የአገራችንን “የማይቀር ትንሣዔ” ያለመበት ታላቅ አገራዊ የኪነት፣ የእውነትና የእውቀት ሰነድ ነው፡፡ ይሄም ስለ መጽሐፉ ሊባልለት ከሚችለው ሲሶውን እንኳን አይሆንም፡፡

Read 5537 times