Monday, 06 March 2017 00:00

አድዋ እና የኢትዮጵያ የዕይታ ጥበባት ወዳጆች ማሕበር

Written by  ጥበቡ ዳዊት
Rate this item
(0 votes)

አድዋ በሁለት ይከፈላል፤ እንደ ሰሞንኛው አስተሳሰቤ፡፡ ሁለተኛው አድዋ እንደ ገደል ማሚቶ ዛሬ ድረስ የሚያስተጋባቸው ጥሪዎችን የሚያስተጋባው የአድዋ መንፈስ ነው፡፡ መቼም ሁለቱም ድንቅ ቅላጼ፡ ዜማና ምት ያላቸው ናቸው። በጋዜጣ የማመስገን እድሉን እስከዛሬ ስላላገኘሁ “ምስጋና ለነሱ ላድዋ ጀግኖች፣ ለዛሬ ነጻነት ላበቁን ወገኖች” እያልኩ፣ የአድዋ መንፈስ ከሚያናኛቸው የጀግንነት ጥሪዎች መሃከል የጥበብ ወዳጆችን ያሰባሰበ አንድ መርሃ ግብር፣ በእለተ አድዋ የካቲት 23 በታሪካዊው ጣይቱ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ እንዳስሰው፡፡
የዝግጅቱን መንፈስ በይበልጥ የሚገልጽልኝ የጃሉድ “ዘራፌዋ” የሚለው ዘፈን ውስጥ የተቀመጠው ሃሳብ ነው፡፡ ያለንን ማዋጣት፡፡ ትንሽ መስጠት፡፡ ከማንነት (ከበጎ) ቀንጨብ አድርገን የምንዘራው እንደሚበቅል፤ ልብ ለልብ ተግባብቶ መሄድ፣ በጥበብ ጎዳና ለመጓዝ ከምንም በላይ ታላቅ መዋጮ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ዝግጅት ነበር። ጉዳዩ የሚድህ ነገር ግን በሁለት እግሩ ለመቆም የሚሞክር፣ ሃሳብን የማበርታትና አቅጣጫዎችን የመጠቆም አላማ ነበረው፡፡ ማሕበር መመስረት። የኢትዮጵያ የዕይታ ጥበባት ወዳጆች ማሕበር የተሰኘ እጅግ የከበረ እሳቤን ያነገበ ማሕበር ለመመስረት የተደረገ የመስራቾች የጠቅላላ ጉባኤ ሸብ-እረብ ነበር፡፡ ታዲያ በቦታው የተገኘው ሰዉ ሁሉ ይህን ሎጋ እሳቤ ለመኮትኮት፣ ለማሳደግና ፍሬ ለማፍራት እንዲያስችል ለማድረግ ብቅ ያለና የቻለውን ለማዋጣት የተሰናዳ በመሆኑ የዕለተ ቀኑን አድዋነት ጨምራችሁ የነበረውን ድባብ ሳሉት። እንዲህ አይነቱ ሃሳብ እዚያው ጣይቱ ሆቴል በተሰበሰብነውና በዙሪያችን በምናውቃቸው ሰዎች አዕምሮና ሕሊና መቅረትና መሰራጨት ብቻ ሳይሆን ባደባባይ መውጣት ስላለበት ላካፍላችሁ፡፡
የዝግጅቱ የክብር እንግዳ በተለይ ቅርስን በማስጠበቅ ሠፊና ፋና ወጊ ሚና በመጫወት የሚታወቀው የሥነ-ጥበብ ወዳጅና አፍቃሪ የሆነው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ባደረገው የመክፈቻ ንግግር ነበር ዝግጅቱ የተጀመረው፡፡ እዚያው ዝግጅቱ ላይ የታደሙ ግለሰቦች ከኢንጂነር ታደለ ብጡል እስከ አርክቴክት ውሂብ ከበደ፣ እስከ ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ እስከ ራሱ ፋሲል ጊዮርጊስ፣ እስከ አርክቴክት ማኅደር ገብረመድኅን፣ እስከ ይህንን ተነሳሽነት እስከወሰደው አርክቴክት ፍጹም ጥላዬና ጓደኞቹ ድረስ ያሉ ታዳሚያን የሚወክሉትን ትውልድ በማውሳት፣ የአድዋን አይነት ተጋድሎ የተከፈለባቸው የተለያዩ ኢትዮጵያዊ ማንነቶችን፣ ከትውልድ ትውልድ የማስተላለፍና የማስቀጠል ችግር በሃገራችን ታሪክ በጉልህ እንደሚታይ ነበር የመክፈቻ ንግግሩ ያሰመረበት ነጥብ፡፡ ልብ ለልብ ተግባብቶ መሄድ ባለመቻሉ በስልሳዎቹና በሰባዎቹ ኢትዮጵያ ያጣችውንም ትውልድ አስታውሶ፣ ለዚህ ማሕበር ምስረታ እየተጉ ያሉ ባለሙያዎችና አላማውን ለመቀላቀል የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ሁሉ መቻቻልን ታሳቢ በማድረግ፣ ከግል አስተሳሰብ ይልቅ የጋራ አላማን ካስቀደሙ ማሕበሩ ዘመን ተሻጋሪ ስራ እንደሚከውን ያለውን እምነት በመግለጽ ነበር፣ አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ልባዊ የመክፈቻ ንግግሩን የቋጨው፡፡
በመቀጠል የማሕበሩ ምስረታ አስተባባሪ በሚል መጠሪያና ከማሕበሩ ጥንስስ ሃሳብ እስከ አሁን ድረስ እየተጫወተ ያለውን ድርሻ ላለመናገር የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ራሱን ሁሌም ከኋላ ለማድረግ የሚጥረው አርክቴክት ፍጹም ጥላዬ ነበር መድረኩን የተረከበው፡፡ እርግጥ ነው ይህን ሃሳብ ማስቀጠልና ማሕበሩን መመስረት ከሁሉም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን አንድን አስፈላጊ ሃሳብ ከግብ ለማድረስ በሚደረግ ርብርብ ሃሳቡ የመነጨበትን ቦታ ማወቅና ያ ሃሳብ በጊዜ ሂደት እድገት እያሳየ በመጣ ቁጥር ሊዘክራቸው የሚገቡ ግለሰቦችን መርሳት የዝንጋኤ ልማድ ያደረግነው ይመስላል፡፡ ይህ እንዳይሆን አርክቴክት ፍጹም ጥላዬ ከሌሎች አራት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የዛሬ ሁለት አመት ተኩል ሃሳቡን እንደጀመሩት ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ማሕበሩን በመመስረት ሂደት አርክቴክት ፍጹም ያደረገውን ትግል በቅርበት ያየሁ እማኝ በመሆኔ፣ “የቄሳርን ለቄሳር” እንዲሉ አርክቴክቱ የተጫወተው ሚና ሊሰመርበት ብቻ ሳይሆን ሊደነቅ እንደሚገባ አምንበታለሁ፡፡ ያቀረበው ረዘም ያለ ንግግር የማሕበሩን ኅላዌ የሚዳስስ ነበር፡፡ የንግግሩ አንኳር ነጥቦች እኒህ ናቸው፡-
የዕይታ ጥበባት ዘርፎች የሚፈለግባቸውን ገንቢ አስተዋጽኦዎች እንዲያደርጉ ማገዝና ይህንን ለማቀድና ለመተግበር ባለሙያዎች፣ የሙያ ማሕበራትና ተቋማት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ተጋግዘው፣ ተባብረውና ተናበው እንዲሰሩ ብሎም ኅብረተሰባችን በሃገራችን የማሕበራዊና የባሕላዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ ግንዛቤው እንዲጨምር የዕይታ ጥበባት ያላቸውን ሚና ተደራሽ ለማድረግ፤ ከተለያዩ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ፈቃደኛ የዕይታ ጥበባት ወዳጆች፣ በሃገራቸው የዕይታ ጥበባት እድገት ዙሪያ ለውጥ ለማምጣትና በውስጣቸው ያለውን የዕይታ ጥበብ ፍላጎትና ጥሪ ለማርካት በበጎ ፈቃደኝነት በመደራጀት፣ የኢትዮጵያ የዕይታ ጥበባት ወዳጆች ማሕበር መመስረት አስፈላጊ የሆነባቸው ነጥቦችን አስረድቷል፡፡ ማሕበሩ ያካተታቸው ትርጓሜዎች፡- ሥነ-ጥበብ፣ ፎቶግራፊ፣ ፋሽን፣ እደ-ጥበብ፣ ዲጅታል ሕትመት፣ ላንድ አርት፣ ሥነ-ሕንጻ፣ ምሕንድስናና ከተማ ፕላን ሲሆኑ ባካተታቸውና ባገለላቸው ወይም ባላካተታቸው ትርጓሜዎቹ መሃል ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ፎቶግራፊን አካትቶ የፊልም ጥበብን አለማካተት ትንሽ ግር የሚያሰኝ ሆኖብኛል፡፡ የማሕበሩ ራዕይ ከፍተኛ የዕይታ ጥበባት ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡ ዓላማዎቹ በአጭሩ ሲቀመጡ ለትውልድ ጠቃሚ የሆኑ የዕይታ ጥበባት ውጤቶች ባግባቡ እንዲጠኑ፣  እንዲደራጁ፣ እንዲመዘገቡና እንዲሰራጩ ማድረግ፤ ባለሙያዎች፣ የሙያ ማሕበራትና ተቋማት የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍና ማበረታታት እንዲሁም የባሕል ማዕከል መገንባት ናቸው፡፡ ይህ ታላቅ ዓላማ ነው፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ በጣሙን የሚሻው፡፡ ግን ለትውልድ ጠቃሚ ያልሆኑ ወይም ጎጂ የዕይታ ጥበባት ውጤቶች አሉ እንዴ? ይታሰብበት እላለሁ። ከማሕበሩ ጋር በጋራ የሚሰሩ የሙያ ባለ ድርሻ ማሕበራትና ተቋማት ተዘርዝረዋል፡- የብልህ ምክር የታከለበት መሆኑን ያመላከተኝ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች አማተር ክበባትና ሚኒ ሚዲያዎች መኖራቸው ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴርም ሌላኛው ባለድርሻ መሆን አለበት፡፡ በተለይ በሥነ-ጥበባችን ላይ ለውጥ የሚመጣው ሕጻናት ላይ መስራት ሲቻል ይመስለኛል፡፡ ተባብሮ መስራት፣ መረዳዳት፣ ክብርና እውቅና መስጠት ከማሕበሩ እሴቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የዕይታ ጥበባትን ግንዛቤ የሚያሻሽል የጋራ መድረክ በየሶስት ወሩ ማመቻቸት፣ የኅበረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ መከታተል፤ በዕይታ ጥበባት ዙሪያ የበጎ አገልግሎት ስራዎችን መስራትና ማበረታታት፤ ከዓለም አቀፍ መሰል ማሕበራት ጋር የትብብር ስራ መስራት ---- ከማሕበሩ ተግባሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ዝግጅቱ የማሕበሩን መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ ያጸደቀው በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ወሳኝ ክርክሮችን ካደረገ በኋላ ነበር፡፡ በመቀጠልም የማሕበሩን የሶስት አመት የበጀት እቅድ አቅርቦ አስጸድቋል፡፡ በመጨረሻም እጩዎችን በማቅረብ የማሕበሩን ሰባት የስራ አመራር ቦርድ አባላት አስጸድቋል፡፡
በእንዲህ ያለ መሰረት ላይ እየተገነባ ያለ ማሕበር ሊጓዝ የሚችለውን ርቀት ሳስብ፣ ጉዞውን ብቻ ሳይሆን የተሸከመውን ክብደትም አያለሁ፡፡ ሆኖም የቱን ያህል ከባድ፡ የቱን ያህል ከአቅም በላይ የሚመስል ችግር ቢኖር፣ ሸክሙን በቅንነት መጋራት፣ በንጹህ ልብ፣ ልብ ለልብ ተግባብቶ መሄድ፣ ከራሳችን ላይ ትንሽ ማዋጣት ከቻልን የማንገፋው ተራራ፣ የማናሳካው ሃሳብ እንደሌለ ከአድዋ ድል በላይ የሚያመላክተን ያለ አይመስለኝም፡፡ እንደ ገደል ማሚቶ ዛሬ ድረስ የሚያስተጋባቸው ጥሪዎችን የሚያስተጋባው የአድዋ መንፈስም ይህ ነው፡፡
ጥበብን የሚወድና የሚያደንቅ ስለ ዕይታ ጥበባት ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር ብቻ ሳይሆን በዕይታ ጥበባት ዙሪያ ያዳበረውን ልምድና ዕውቀት ለማስተላለፍ የበኩሉን ለማበርከት የሚፈልግ ሁሉ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ከዚህ የተሻለ እድል የሚያገኝ አይመስለኝም፡፡ እያወቀ ችላ ያለ እንደቀረበት አምናለሁ፡፡ ከዚህ ተነሳሽነት መጠቀም እየቻለ እድሉን ያመከነ ብቻ ሳይሆን የዘገየን ሁሉ ሞኝ እንደሆነ እጠቁመዋለሁ፡፡ የአቅሙን ማዋጣት እየቻለ ራሱን የሚያገልልን ግን የአድዋን ገደል ማሚቶ ወደ ዝምታ ሳይሆን ወደ ጩኧት ቀይሮ፣ ጩኧቴን ቀሙኝ የሚል ቀጣፊ ነው እያልኩ፣ አድዋን ለማሰብ እንደማይችል እነግረዋለሁ፡፡ ይህ ቁጣ ማንም ላይ ያነጣጠረ ባይሆንም ለተጠቀምኩት የኃይለ-ቃል ውርጅብኝ፣ ውድ አንባቢዬን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ የዕይታ ጥበባት ወዳጆች ማሕበር፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ከኃይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ የሆነ የበጎ አድራጎት ማሕበር ነው፡፡ አባልነት ለማንኛውም ግለሰብ ክፍት ነው፡፡ ለመረጃ +251 911 634 134 አምብዬ ብለው ይደውሉ፡፡ ቸር እንሰንብት!!! 

Read 1170 times