Monday, 06 March 2017 00:00

የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አይኮግ ላብስ የተባለውና በወጣቶች የተቋቋመው የሶፍትዌር አማካሪ ድርጅቶች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሮች ጋር በመተባበር፣ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ግቢ ውስጥ በመቀሌና በአራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩልቲ ዩኒቨርስቲዎች መካከል የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድር ያካሂዳል፡፡ ድርጅቱ ባለፉት አምስት አመታት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በሮቦቲክስ ቢዝነስ ላይ ሲሰራ መቆየቱን ሰሞኑን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ የሚሰራው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦቲክስ ቢዝነስ በአገራችንም ሆነ በአፍሪካ ያልተደፈረ ስራ በመሆኑ ከውጭ ድርጅቶች ጋር ሲሰራ እንደነበር አስታውሶ፣ ነገር ግን ቢዝነሱ በአገር ውስጥ መተግበር ቢጀምር ችግር ፈቺ ይሆናል በሚል ሃሳብ ያለፈውን አንድ አመት ከ22 የአገራችን ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረሙን የአይኮግ ላብስ መስራቾች ተናግረዋል፡፡
ሳይንሱን ከጨዋታና ከመዝናናት ለመጀመር ከዩኒቨርስቲው የተውጣጡ ሁለት ሁለት ተማሪዎች መርጦ ስልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ተማሪዎቹ ውድድሩን በሮቦቶች ለማድረግ፣ ሮቦቶቹን ከመገጣጠም ጀምሮ ወደ ተቃራኒ ጎል እንዴት መምታት እንዳለበት፣ እንዴት ጎል ማስገባትና ኳስ ለቡድኑ ተጫዋች ማቀበል እንደሚችል ----- ሮቦቶቹን ፕሮግራም በማድረግ አዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡ ለፍፃሜ ውድድር ያለፉት መቀሌ ዩኒቨርስቲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ፋኩልቲ እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡  
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤”ወጣቶቹ በአገራችን ብቸኛ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦቲክ ቢዝነስ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም ለሥራቸው ከፍተኛ እውቅና በመስጠት ከሚኒስቴሩ ጋር በጋራ እንዲሰሩ አድርገናል” ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለፈጠራ ስራ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት የፈጠራ ባለሙያዎችን  ለማበረታታት በየዓመቱ ሽልማት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ዘንድሮም ለሰባተኛ ጊዜ ይህ ሽልማት ለፈጠራ ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
አይኮግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሂደው ‹‹አይኮግ ሜከርስ ሮቦ ሶከር ካፕ›› በየአመቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሮቦት እግር ኳስ ውድድሩን ለመጫወት 3 ሜ. በ 2 ሜ የሆነ ሜዳና ከእያንዳንዱ ቡድን ሶስት ሶስት ሮቦት እንደሚያስፈልጉ የተገለጸ ሲሆን ለአሸናፊው ቡድን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሽልማት ይበረከታል ተብሏል፡፡

Read 990 times