Print this page
Monday, 13 March 2017 00:00

ከድርቅና ከረሃብ አዙሪት ለምን መውጣት አቃተን?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ፖሊሲ ይተቻሉ
            በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውና ወደ 6 ሚሊዮን ገደማ ህዝብን ለአደጋ ያጋለጠው ድርቅ፤ህፃናት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ያናጠበ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ሰዎችንም ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ይህን የድርቅ አደጋና ስጋት ማሸነፍና ማስወገድ ያልተቻለው ለምንድን ነው? ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ አገራዊ ችግር ላይ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳብ ሲያቀርቡ እምብዛም አይስተዋልም፡፡
በወቅታዊው የድርቅ አደጋና ስጋቱ እንዲሁም በዘላቂ መፍትሄዎች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል፡፡

              “መንግስት ስለ ድርቁ ትክክለኛ መረጃ ሊያቀርብልን ይገባል”
                                 አቶ የሸዋስ አሰፋ (የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

       መንግስት ለተፈጠረው ድርቅ የሰጠው ትኩረት በኛ ፓርቲ በኩል አነስተኛ ነው የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡ ከ800 በላይ ት/ቤቶች ተዘግተው፤ በርካቶች ተሰደዋል ግን ስለ ጉዳዩ ብዙ ሲባል አይሰማም፡፡ ይሄ መደባበቅ ነው፡፡ ያለፉ መንግስታት ሲተቹ የነበረውኮ በዚህ የተነሳ ነው፡፡ መንግስት ችግሩን በቅጡ እንድናውቀው አላደረገንም፡፡ አሁን እንደ መረጃ የምንጠቀመው አለማቀፍ ተቋማት የሚያወጡትን ሪፖርት ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ መንግስት ጉዳዩን ሁሉም አውቆት የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ አለበት፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በድርቅ በተጎዱ አካባቢ ያሉ ሰዎችን አነጋግሮ መረጃ ለማግኘት ሞክሮ ነበር፡፡ እንደተረዳነው፤ በጥቅምት መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ በውሃና በግጦሽ እጦት ከብቶቻቸው እንዳለቁባቸውና እነሱም ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ ነው፡፡ በፓርቲያችን እምነት፤ በተደጋጋሚ በድርቅ ለሚጠቁ መሰል አካባቢዎች የሚሆን ተስማሚ ፖሊሲ አለመቀመጡ አደጋውን እስከ ዛሬ ላለመሻገራችን ምክንያት ነው፡፡ 6 ሚሊዮን ህዝብ በድርቅ ተጎዳ ማለት፣ የአንድ ሀገር ህዝብ ያህል ነው፡፡ ይሄን እንኳ በአግባቡ መንግስት ሊገልፀው አልፈለገም፡፡ ተቃዋሚዎች በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርገን፣ መንግስት ላይ ጫና እንዳናሳድር በአሁኑ ወቅት  በብዙ ጉዳዮች ተጠምደናል፡፡ በዚህ ሳምንት እንኳ 12 ሰዎች ታስረውብናል፡፡ ግን ቀንና ቀጠሮ የማይጠይቀው ይሄ ጉዳይ በሚገባው መጠን ንቅናቄ አልተደረገበትም፡፡ ምናልባት መንግስትም ሀገርም በብዙ ችግር መዋጣቸው፣ለጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው ማድረጉን አምናለሁ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ የእነዚህ ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች በድርቅ የመጎዳት ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ ሊደረግበት ይገባል፡፡ አሁንም መንግስት ከምንም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ፓርቲያችን በአቋም መግለጫው አሳስቧል፡፡ መንግስት በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎቻችን ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ፣የመታደግ ስራ ላይ መረባረብ አለበት፡፡
ድርቁ ራሱ መኖሩ ችግር አይደለም፤ ድርቁ ረሃብ ሲፈጥር ግን በግልፅ የመንግስት ፖሊሲ ችግር እንዳለ ያስረዳል፡፡ ለፖሊሲ ውድቀት ከዚህ በላይ ማስረጃ አይገኝም፡፡ በየ10 ዓመቱ ድርቅ እንደሚመጣ ይታወቃል፤ ለምን በቂ ዝግጅት አይደረግም? ዛሬ ከ800 በላይ ት/ቤቶች ተዘግተው፣ እንዴት ችግር ሳይፈጥር ድርቁን እየተቋቋምኩ ነው የሚል ሪፖርት ይሰጣል? ይሄ በቂ የአደጋ መከላከል ዝግጅት እንዳልተደረገ ማሳያ ነው፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፓርቲያችን መደረግ ያለበት ብለን የምናምነው፣በተለይ በተደጋጋሚ በድርቅ በሚጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ውሃ ወዳለበት የሀገሪቱ አካባቢ ማሰባሰብ ነው፡፡ በቀጣይ አርብቶ አደሩ በአንድ ምቹ አካባቢ ተረጋግቶ በመቀመጥ ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲለወጥ ተከታታይ ስራዎች መሰራት አለባቸው የሚለው ነው፡፡ ከመፍትሄዎቹ መካከል እነዚህ እንደ አማራጭ የሚቀመጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ለአስቸኳዩ ችግር ሁሉም አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል፡፡ መንግስት ስለ ድርቁ ጉዳይ ትክክለኛ መረጃ ሊያቀርብልን ይገባል፡፡ ሀቆች መደበቅ የለባቸውም፡፡

------------------

                        ‹‹ድርቅም ቢኖር ረሃብ ሊኖር አይገባም››
                        ዶ/ር ጫኔ ከበደ
                           (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

       በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ፓርቲዎች መንግስት ላይ ግፊት አላደረጉም፤ ነገር ግን በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል አጀንዳው ተነስቶ ውይይት ተደርጎበት ጥናት እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚመጣውን ውጤት እንጠብቃለን፡፡
በአቋም ደረጃ ግን ፓርቲያችን ከሚያራምደው ፕሮግራም አንፃር፣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንዲህ ያለው ድርቅ ሊያጠቃት የቻለው በአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ነገር ግን ድርቅም ቢኖር ረሃብ ሊኖር አይገባም የሚል አቋም ነው ያለን። ሌሎች ሃገሮች ከዚህም የከፋ ድርቅ ይመታቸዋል፤ ነገር ግን ዜጎቻቸው ሲራቡ አይተንም ሰምተንም አናውቅም፡፡ የፓርቲያችን ፕሮግራም በሊበራል የኢኮኖሚ ሲስተም የሚመራ እንደመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቋቋም ራስን በሚያስችል የመስኖ ልማት ውስጥ መገባት አለበት። ወንዞቻችን ከኛ አልፈው ለሌላው የሚተርፉ ናቸው።
ድርቅን ተከትለው የሚከሰቱ ችግሮችን መቋቋም አለመቻላችን የሚያሣየን፣ መንግስት በመስኖ ልማት የዚህችን ሃገር ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚገባው መጠን በቁርጠኝነት እየሰራ አለመሆኑን ነው፡፡ ድርቅን ተቋቁሞ ረሃብን ማጥፋት በሚቻልበት ዙሪያ ብዙ እንዳልተሰራ በየአመቱ ድርቅን ተከትሎ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች አስረጅ ናቸው፡፡
መንግስት ለሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደ ኢነርጂ ላሉት ትልቅ ትኩረት ሲሰጥ እናያለን፤ ነገር ግን በመስኖ ልማት ላይ የጠነከረ ስራ ሲሰራ አይታይም። ይህ መንግስት ከሚከተለው የልማት ፖሊሲ ደካማነት የመነጨ ነው፡፡ የሃገሪቱን ሃብቶች አሟጦ ከመጠቀምና ህዝቡን ከመሰል ችግሮች በዘላቂነት ከመታደግ አንፃር፣ አሁን መንግስት እየተከተለ ያለው ፖሊሲ የተሳሳተ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ለሃገሪቱ ጠቃሚ የሚሆነውና ህዝብን ከድርቅ አደጋ መታደግ የሚቻለው ለሌሎች ልማቶች የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለትላልቅ የመስኖ ልማቶች ሲሰጥ ብቻ ነው የሚል አቋም አለን፡፡ ይሄን ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ተፈጥሮ በየጊዜው እየተዛባ ባለበት ሁኔታ ህዝብን ከችግር መታደግ አይቻልም፡፡ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይም የራሱን አሉታዊ ተፅእኖ ያሳርፋል። ያለንበትን ጂኦግራፊያዊ ሁኔታ በሚገባ በጥናት በመለየት ለየዘርፉ ችግሮች ተመጣጣኝ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
ህዝቡ በመስኖ ልማት ውስጥ እንዲሳተፍ ሰፊ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ለምሳሌ በድርቅ ከተጎዱት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የሶማሌ ክልል ነው። ወደዚያ አካባቢ የሄደ ሰው በእጅጉ ያዝናል፡፡ ያንን የመሰለ ለም መሬት አቋርጠው ወደ ጎረቤት ሶማሊያ የሚፈሱ ወንዞችን ሲያይ በእጅጉ ይቆጫል፡፡ በጣም ነው የሚያስቆጨው፡፡
ወንዞቹ ያንን የመሰለ ለመስኖ ልማት ተስማሚ የሆነ ለም መሬት አቋርጠው ሶማሊያ ገብተው ጥቅም ሲሰጡ ለተመለከተ፣ በእርግጥስ ምንድን ነው ችግሩ የሚል ጥያቄ ያጭርበታል፡፡ ዛሬ ሶማሊያ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ የሙዝና የብርቱካን አቅራቢ የሆነችው፣ የኛን ለም መሬት አቋርጠው የሚሄዱ ወንዞችን ለመስኖ በመጠቀሟ ነው እንጂ ዝናብ የላትም፡፡ እኛ ከባሌ ተራራዎች እየፈለቁ ሶማሌ ክልልን እያቋረጡ የሚሄዱ ወንዞችን ሳንጠቀም፣ ሁልጊዜ የሶማሌ ክልል ህዝብ ተራበ የሚል ሪፖርት ነው የምንሰማው፡፡
ክልሉ ካለው ሰፊ የተፈጥሮ ፀጋ አንፃር እዚያው ሰብሉ ለምቶ፣ እዚያው በአግሮ ፕሮሰሲንግ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በማምረት ትልቅ የምግብ ምርት አካባቢ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ ግን በመንግስት የተሳሳተ ፖሊሲና ትኩረት ማነስ የተነሳ ይሄ እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ዛሬ በድርቅ አዙሪት ውስጥ ለመዳከራችንም ይሄው ነው ዋነኛ ምክንያቱ፡፡

---------------

                        “በድርቅ ለተጎሳቆለ ህዝብ አስፋልት ቢዘረጋለት ምኑ ነው?”
                                ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ ሊቀመንበር)

        ድርቅ ስለመኖሩና በዚህ ምክንያት በህዝብ ላይ ጉዳት እየደረሰ ስለመሆኑ ይሄ መንግስት ለአለማቀፉ ማህበረሰብ መረጃ ለማድረስ ትንሽ ይተናነቀዋል፡፡ መጀመሪያ ምንም ጉዳት እንደሌለ ተገልፆ ነው፣ ቀስ በቀስ የጉዳቱ መጠን ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄደው። “ሀገሪቷ አድጋለች ብዙ ለውጠናታል፤እንዴት ስለ ድርቅ ይወራል” በሚል መንግስት እውነታውን ለመናገር ድፍረት ያንሰዋል፡፡ እውነቱ ግን ይህቺ ሀገር ከድርቅ ጉዳት ለመላቀቅ የሚያስችል ስራ አልተሰራባትም። መንግስት መረጃ አሰጣጡ ላይ መታረም አለበት፡፡ በየዓመቱ ተመላልሶ የሚመጣ እንደመሆኑ ድርቁ ተተንባይ ነው፡፡ በዚህ ተተንባይ በሆነና የራሱ የታወቀ ጊዜ ባለው የተፈጥሮ አደጋ፣ ለምን ዜጎቻችን ይጎዳሉ? የሚለው በእውነቱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ሁሉም ወገን ለዚህ ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት መስራት አለበት፡፡ ብዙ ገንዘብ በተለያዩ ብድሮችና እርዳታዎች እየመጣ፣ እዚያም እዚህም ሲበተን እናያለን፡፡
ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ከረሃብ ስጋት የሚያወጣ በቂ ስራ እስከዛሬ አለመሰራቱ በእውነት አስተዛዛቢ ነው። ለህዝቡና ለከብቶቹ በየቦታው ውሃ ማውጣት እንዴት ይከብዳል? ይሄ ከሁሉም መሰረት ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶት መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ለእነዚህ አይነት አካባቢዎች መሰረት ልማት ማለት በዋናነት መንገድ ብቻ አይደለም፤ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ውሃ ነው፡፡ የህዝቡ አኗኗር በእንስሳት ሃብት ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡ ለሱም ለከብቶቹም ውሃ ማግኘት አለበት፡፡ ይሄን መስራት እንዴት ይከብዳል? ውሃ ማቆር እየተባለ እንደ ፋሽን አንድ ሰሞን ይወራል፤ከዚያ እንደዘበት ይቀራል፡፡ አስፋልት ከሚለብሱ መንገዶች በፊት መጀመሪያ የሰው ህይወት መቅደም አለበት፡፡ ይሄንን ባለማድረግ መንግስት ትልቅ በደል እየፈፀመ ነው የሚል ነው የኛ አቋም፡፡
ውሃ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች ውሃ ማቅረብ ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለእንስሳትም ለሰውም ምግብ በበቂ ሁኔታ መድረስ አለበት፡፡ በቂ የእህል ክምችት አለን እየተባለ ነው፤ ታዲያ ለምን ህፃናት ተጎሣቁለው ትምህርት ያቋርጣሉ? ይሄ በእውነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከሁሉ በፊት ዜጎችን ከዚህ ጉስቁልና ማውጣት ያስፈልጋል። በድርቅ ለተጎሳቆለ ህዝብ ውሃ የመሰለ አስፓልት በአጠገቡ ቢዘረጋለት ምንም ስሜት አይሰጠውም፡፡ ለቪዲዮ ቀረፃ ብቻ የሚመቹ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የመኖር ዋስትና ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

-----------------

                        “መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ አለበት”
                          ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት)

       በ1966 እና በ1977 በዚህች ሀገር ያጋጠመው ድርቅ፣ ዜጎችን ለከፋ ረሃብ ዳርጎ፣ የዓለም ህዝብ ታድጎናል፡፡ በ1966 ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ውድቀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረው ድርቁና ረሀቡ ነው፡፡ ደርግም በድርቅ ብዙ ተፈትኗል፡፡ ይሄም መንግስት እየተፈተነ ነው፡፡ ዜጎች ዛሬም የረሃብ ስጋት ላይ በመውደቃቸው የእርዳታ እጅ ተዘርግቷል፡፡ በሌላ በኩል ለፖለቲካ ተብሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚገባው ለድርቁ ነው፡፡ መንግስት አሁን እየተቸገሩ ላሉት 6 ሚሊዮን ገደማ ዜጎቻችን እርዳታ እያቀረብኩ ነው ይላል፤ህዝቡ ደግሞ እየተራብኩ ነው ሲል በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየሰማን ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ከፖለቲካውም ጉዳይ ይልቅ ቅድሚያ ሰጥቶ በዚህ ችግር ላይ ርብርብ ማድረግ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም ጭምር፡፡
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በሚመሩት አማራጭ ኃይሎች ፓርቲ ውስጥ በነበርኩ ጊዜ በወቅቱ በሀገሪቱ ተከስቶ ለነበረው ድርቅ፣ እርዳታ አሰባስበን ለማቅረብ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበን ነበር፤ሆኖም ከመንግስት ቀና ምላሽ አላገኘንም ነበር፡፡ ሁሉም ነገር በፖለቲካ አይን መታየት የለበትም፡፡ ሠብአዊ ድጋፍ የፖለቲካ አቋም አይወስነውም፡፡
መንግስት ከጊዜያዊ እርዳታ ባለፈ በዘላቂ መፍትሄዎች ዙሪያ አማራጭ ሃሳቦችን ከተቃዋሚዎች መቀበል አለበት፡፡ ለምሳሌ ለምንድን ነው ዝናብ ጠባቂ የምንሆነው? ለምን ሰፋፊ መስኖ አይሰራም? ከሁሉም መሰረት ልማቶች ይሄ መቅደም አለበት፡፡ የውሃ አቅማችን ከፍተኛ ነው፤ለምን ይሄን ሃብት ለህዝባችን ጥቅም አናውለውም? ይሄ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡
የዛሬ 40 ዓመት ሩሲያ ሃገር ተማሪ በነበርኩ ሰአት አንድ የሩሲያ ፀሃፊ ስለ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው መፅሃፍ ላይ፣ኢትዮጵያን የአፍሪካ ገነት ይላታል፡፡ “ሃገሪቱ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ራሷን ከመገበች በኋላ ለትላልቅ 6 መንግስታት ህዝቦች የሚበቃ የእርሻ ምርት የማቅረብ አቅም ያላት ናት” ሲል በሰፊው ተንትኖ ፅፏል፡፡ እንግዲህ ዋናው ችግራችን ጥሩና ተስማሚ የፖሊሲ አማራጮችን በሚገባ ፈትሾ በስራ ላይ አለማዋል ነው፡፡  

----------------

                        “ከፖለቲካ በፊት የዜጎችን ህይወት መታደግ ይቀድማል”
                           አቶ ተሻለ ሰብሮ (የኢራፓ ፕሬዚዳንት)

       ከምንም በላይ የህዝብ አድን ስራዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል አቋም አለው፤ ፓርቲያችን፡፡ በየጊዜው ይህ ድርቅና ረሃብ መከሰቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ እስከዛሬም አለመቆሙ ሁነኛ መፍትሄ እንዳልተበጀለት አመላካች ነው፡፡ ድርቅን መቋቋም በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በቂ ልምድ እንዳልተቀሰመም መታዘብ ችለናል፡፡
ለምሳሌ እስራኤልና ግብፅ በረሃማ አካባቢን እንዴት ለሰው ልጆች እንዲመች አድርጎ መግራት እንደሚቻል ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ልምዶች በመቅሰም በሃገራችን ልንሰራበት ይገባ ነበር፡፡ ችግሩ በተፈጠረ ቁጥር የነፍስ አድን ስራ ላይ ብቻ መረባረብ ውጤት የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ የፖሊሲ ጥናት ተደርጎ፣ በልዩ ትኩረት አዋጭና ዘላቂ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ በፖለቲካ መጠላለፍና አተካሮ ሲኖር፣ እንዲህ ያሉ ወሳኝ የህዝብ ጉዳዮች ይዘነጋሉ፡፡ ዘንድሮ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በድርቅ አደጋ ላይ ሆኖ ትኩረት ያልተሰጠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡  
መንግስትም፣ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሄን በብሄራዊ መግባባት ማጤን አለባቸው። ከፖለቲካ በፊት የሰው ህይወትን መታደግና ዘላቂ ዋስትና ማስገኘት ይቀድማል፡፡ ተቃዋሚዎች ይሄን ጉዳይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት፣ህዝቡን እንዲታደግ ግፊት ማድረግ አለብን፡፡ አሁን እንኳ በተጀመረው ድርድር፣ ስለ ድርቅ አደጋ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት፣ በአጀንዳነት ለመወያየት ታስቦ እንደሆነ አናውቅም። ግን ይሄ የህዝባችን ዋነኛ ችግር ነው፡፡ ከፖለቲካም በላይ ነው፡፡ ይህ ተደጋጋሚ ችግር እንዴት እስከዛሬ ዘላቂ መፍትሄ አልተገኘለትም? ሰፊ ክርክርና ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በአባይ ጉዳይ ላይ ያለንን ሃገራዊ መግባባት በድርቅ ጉዳይ ላይ አናስተውልም፡፡
የዜጎችን ህይወት መታደግ ከአባይ ጉዳይም በላይ ነው፡፡ የተለያዩ ፖሊሲዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበው ሰፊ ክርክርና ውይይት ማድረግ አለብን፡፡ በብሄራዊ ደረጃ ይሄን የሚያስፈፅም ትልቅ ንቅናቄ ያስፈልጋል፡፡

Read 1860 times
Administrator

Latest from Administrator